1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃውያን ስደት እና አውሮጳ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 14 2010

ምዕራባውያን ለአፍሪቃ የሚሰጡት የልማት እርዳታ በአብዛኛዎቹ ሀገራት ይህን ነው የሚባል ለውጥ ባለማሳየት ተደጋጋሚ ትችት ይቀርብበታል። እንደተቺዎቹ ዋነኛው ችግር «እርዳታዎቹ ለታሰበላቸው ዓላማ ሳይሆን ለአምባገነን መሪዎች ኪስ ማደለቢያ መዋላቸው» ነው። ይህም በእነርሱ አስተያየት የአፍሪቃውያንን ስደት ካባባሱት ምክንያቶች አንዱ ነው።

https://p.dw.com/p/2mR40
Flüchtlinge auf Mittelmeer
ምስል picture-alliance/Bundeswehr/S. Hoder

የአፍሪቃውያን ስደት

ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ከመጡባቸው የአውሮጳ ሀገራት አብዛኛዎቹ አሁን ድንበራቸው ዘግተዋል። የስደተኞች መተላለፊያ የሆኑ የአፍሪቃ ሀገራት በአደገኛ የበረሃ እና የባህር ጉዞ  ወደ አውሮጳ ለመሻገር የሚሞክሩ ስደተኞችን እንዳያሳልፉባቸው  የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ እየሰጧቸው ነው። አውሮጳውያን በባህር እና በየብስ ወደ አውሮጳ የሚደረግ ስደትን ለመግታት እነዚህን እና ሌሎችንም ጠንካራ እርምጃዎች በመወሰድ ላይ ናቸው።

ዓለም አቀፉ የፍልሰት ጉዳዮች ድርጅት በምህጻሩ አይ ኦ ኤም እንዳስታወቀው ባለፉት 9 ወራት ብቻ ከ 131 ሺህ በላይ ስደተኞች የሜዴትራንያንን ባህር አቋርጠው አውሮጳ ገብተዋል። እንደ ድርጅቱ በዚህ ጊዜ የሜዴትራንያንን ባህር አቋርጠው የኢጣልያ የባህር ዳርቻዎች የደረሱት ከ102 ሺህ በላይ ሲሆኑ የተቀሩት ደግሞ ግሪክ ቆጵሮስ እና ስፓኝ ነው የገቡት። አይ ኦኤም እንደሚለው በጎርጎሮሳዊው 2017 አውሮጳ የገቡት ስደተኞች ቁጥር ከቀደመው ከ2016 ዓም ጋር ሲነጻጸር በ56 በመቶ ቀንሷል። በ2016 ፣ አውሮጳ መግባት የቻሉት ስደተኞች ቁጥር 300,076 ነበር። ይሁን እና በዓመቱ ወደ አውሮጳ ጉዞ ከጀመሩት መካከል 2556 ቱ በሜዴትራንያን ባህር ላይ ህይወታቸው አልፏል። ይህም ከእስከዛሬው ከፍተኛው ሞት መሆኑን አይ ኦኤም አስታውቋል።

Asfa-Wossen - deutschsprachiger Autor und Unternehmensberater
ዶክተር ልጅ አስፋወሰን አሥራተምስል picture-alliance/dpa/E. Elsner

ምንም እንኳን አውሮጳውያን ስደተኞችን ለማስቆም አለያም ለመቀነስ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ በወሰዷቸው እርምጃዎች አውሮጳ መድረስ የቻሉ ስደተኞች ቁጥር መቀነሱ ቢታይም አይዘልቅም ባዮች ጥቂት አይደሉም። እነዚህ ወገኖች ይልቁንም እርምጃዎቹ ለህገ ወጥ የሰዎች አሸጋጋሪዎች በር ይከፍታሉ አስከፊውም ስደት መልኩን ቀይሮ መባባሱ  ይላሉ።

ዶክተር ልጅ አስፋወሰን አሥራተ ጀርመን የተማሩት እና የሚሰሩ የአፍሪቃ እና የመካከለኛው ምሥራቅ የንግድ አማካሪ ደራሲ እና የፖለቲካ ተንታኝ ናቸው። «አዲሱ የህዝቦች ስደት ፣አውሮጳን እንዳለች ለመጠበቅ አፍሪቃን ማዳን» የሚል ርዕስ በሰጡት እና ከአንድ ዓመት በፊት በጀርመንኛ ባሳተሙት መፀሐፋቸው እንዳሉት አውሮጳውያን በተለይ ለአፍሪቃ ችግር መፍትሄ ካልፈለጉ በስተቀር  ከአፍሪቃ ወደ አውሮጳ የሚካሄደው ስደት ተባብሶ ይቀጥላል እንጂ አይቆምም። በርሳቸው አባባል ከክፍለ ዓለሙ ህዝቡ ለመሰደዱ ምክንያቶቹ አምባገነን መንግሥታት ናቸው። ምዕራቡ ዓለምም ለነዚህ መንግሥታት የሚሰጠው የልማታ እርዳታን የመሳሰለው ድጋፍ ለታሰበለት ዓላማ ሊውል አልቻለም።ይህን ለማስተካከል የአውሮጳ ሀገራት ያለፉትን 50 ዓመታት የአፍሪቃ መርሃቸውን መቀየር  አለባቸው እንደ ዶክተር አስፋወሰን። ከአሁን በኋላም የሚወስዱት እርምጃ የተናጠል ሳይሆን አንድ ወጥ መሆን ይገባዋል ይላሉ።

Bildergalerie Rettung von Flüchtlingen durch deutsche Cargo schiffe im Mittelmeer
ምስል OOC Opielok Offshore Carriers

ከዚህ ሌላ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ምሥረታ 50 ኛ ዓመት የዛሬ 4 ዓመት ሲከበር የአፍሪቃ መንግሥታት ያፀደቁት የክፍለ ዓለሙን ራዕይ በግልጽ አስቀምጧል የሚባለው አጀንዳ 2063 የችግሩ መፍቻ ቁልፍ ተደርጎ ሊወሰድ  እንደሚገባ ዶክተር አስፋወሰን ያሳስባሉ። በርሳቸው አስተያየት አጀንዳው የወደፊቱ የአውሮጳ እና የአፍሪቃ ግንኙነት መሠረት ሊሆን ይገባል።ዶክተር ልጅ አስፋወሰን አሥራተ እንደሚሉት የአውሮጳ ሀገራት የእስከዛሬውን የአፍሪቃ መርሃቸውን ካልቀየሩ የክፍለ ዓለሙ መጨረሻ አያምርም።

ኂሩት መለሰ

አርያም ክሌ