1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃዉ ቀንድ ሃገራት እና አሜሪካ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 5 2015

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶዮ ብሊንከን ጉብኝት በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ሻክሮ የቆየውን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ትብብር ሊመልስ ይችላል የሚል ተስፋ አሳድሯል። አሜሪካ የትም ትሂድ የትም ቅድሚያ ከተቀናቃኞቿ እና የውስጥ ፍላጎቷ መነሻ ጥቅሟን ታራምዳለች ሲሉ የፖለቲካ ተንታኞች ሃሳብ ይሰጣሉ።

https://p.dw.com/p/4Of5K
Gipfeltreffen der Frontstaaten Somalias in Mogadischu
የአፍሪቃዉ ቀንድ ሃገራት ከፍተኛ አመራሮች ምስል Ethiopian PM Office

የሀገራቱ መሪዎች ሰሞነኛ ግንኙነት "የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በኃያላኑ ፍትጊያ ተጠልፎ እንዳይወድቅ የወሰዱት የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃ ሊሆን ይችላል"

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶዮ ብሊንከን ጉብኝት በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ሻክሮ የቆየውን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ትብብር ሊመልስ ይችላል የሚል ተስፋ አሳድሯል። አንድ የፖለቲካ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያ አሜሪካ የትም ትሂድ የትም ቅድሚያ ከተቀናቃኞቿ እና የውስጥ ፍላጎቷ መነሻ ጥቅሟን ታራምዳለች በማለት የብሊንከንን ጉብኝት ራሺያ እና ቻይና በአፍሪካ ቀንድ እየያዙት ካለው እያደገ የመጣ የፓለቲካ ኢኮኖሚ እርምጃ እና ጫና አንፃር ይተነትናሉ። 

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በደቡብ ሱዳን፣ የሱዳን እና የሶማሊያ መሪዎች ደግሞ በኤርትራ እያደረጉት ያለውን ሰሞነኛ ጉብኝት በአንድ በኩል የየሀገራቱን የውስጥ ፍላጎት ለማሟላት እየተደረገ ያለ መሳሳብ አድርገው ሲያቀርቡት ፣ በሌላ ጎኑ ደግሞ በምዕራባዊያን እና በቻይና - ራሺያ እሽቅድድም የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ተጠልፎ እንዳይወድቅ የወሰዱት የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃ ሊሆን እንደሚችል ይገልፃሉ። 

Äthiopien Premierminister Treffen mit Führern von Tigray
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ እና የህወሓት ባለስልጣናት ምስል Ethiopian Broadcasting Corporation

የዓለም ከፍተኛ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ትኩረት ማረፊያ እና የኃያላን ሀገራት ፍላጎት ቁልፍ ማራመጃ የሆነው የአፍሪካ ቀንድ የማይፈታ ድህነት እና የማያባራ የእርስ በርስ ግጭት ማዕከል ፣ የሰዎች ፍልሰት መተላለፊያ ብሎም የድርቅ ሰለባ ሆኖ የቀጠለ ክፍለ ዓለም ነው።
በሌላ በኩል የራሺያ እና የቻይና በአፍሪካ ቀንድ ያላቸው ፍላጎት እንዲሁም ኢትዮጵያ በዚህ ቀጣና የነበራት ተጽእኖ ብሎም የሚኖራት ሚና ለአሜሪካ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ነገ በኢትዮጵያ የሚያደርጉት የሥራ ጉብኝት ምእራቡ አለም በጥቅሉ ከዚህ በፊት ይዘውት ከቆዩት ግትር አቋም መለስ የማለታቸው ማሳያ ሊሆን እንደሚችል ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የዓለም አቀፍ ሕግ እና የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ገልፀዋል።
"ኃያላን ሀገራት የአፍሪካ ሀገራትን የጉዳይ አስፈፃሚዎቻቸው ብቻ አድርጎ የማየት ፣ ፍፁም ሕልውና እንዳላቸው፣ ከምእራባዊያን ሀገራት ጋር አቻ መቆም የሚችሉ ሉዓላዊ ሀገራት መሆናቸውን ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ የገዢነት መንፈስ የተጠናወተውና ከእኛ ጋር ብቻ ቁሙ የሚል አሰላለፍን መከተላቸው ብዙ ነገርን አሳጥቷቸዋል። ራሳቸውን የመገምገም እድል አግኝተው መጥተው ሊሆን ይችላል"። 

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ብሊንከን ነገ ከቀትር በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ ለጋዛጠኞች በሚሰጡት መግለጫ የጉዟቸው ግብ በተወሰነ ደረጃ ሊታወቅ ይችል ይሆናል።
በኢትዮጵያ ደረጃ ግን የመምጣቻቸው ዓላም በውጭ ገዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በኩል በሳምንቱ ማብቂያ ቀናት ተገልጾ ነበር።
የምእራቡን አለም ከፍተኛ ጫና ተሸክማ ያለችው ኤርትራ በዚሁ የአፍሪካ ቀንድ ከባቢ ቁልፍ ተዋናይ እየሆነች መምጣቷን እና ይህም ምዕራባውያን በቀጣናው የሚያርራምዱት ፖሊሲ ውድቀት ማሳያ ሲያደርጉት ይታያል።
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሱዳን እና የሶማሊያ መሪዎችን በዚሁ ሳምንት ማነጋገራቸው ተዘግቧል።
ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ተንታኝ የሀገራቱ መሪዎች ሰሞነኛ ግንኙነት "የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በኃያላኑ ፍትጊያ ተጠልፎ እንዳይወድቅ የወሰዱት የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃ ሊሆን ይችላል"
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ደቡብ ሱዳን ተጉዘው "ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳንን መረጋጋት እና ሰላም ለመደገፍ ያላትን ቁርጠኝነት" መግለፃቸውን ተናግረዋል። የጉዟቸው አላማ ምን እንደሆነ ግን ይህ ነው ያሉት ነገር የለም። የፖለቲካ ትንታኙ እንደሚሉት ግን ከጉዟቸው ምክንያት በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ እስከ 200 ኪሎ ሜትር ወደ ኢትዮጵያ ዘልቀው እየገቡ ያሉ የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎችን ጥቃት ለማስቆም ሊሆን ይችላል።
"በተደጋጋሚ ከደቡብ ሱዳን እየተነሱ በጋምቤላ የተወሰኑ ክፍሎች ላይ ጥቃት በማድረስ ላይ ያሉ ጎሳዎች እንዳሉ እናውቃለን። ለረጅም ጊዜ የቆየ ነው በቅርቡም በተደጋጋሚ መሰል ጉዳዮች ተፈጥረዋል። ምናልባት በአንድ በኩል እሱን የማስታመም አላማ ሊኖረው ይችላል። ከዚያ ውጪ ግን ደቡብ ሱዳን ያለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ደግሞ መንግሥት እያለ መንግሥት የሌለ በሚመስልበት ቁመና ላይ የምትግፕኝ ሀገር ነች። ስለዚህ ዘላቂ የሆነ ሰላም የማምጣት ፍላጎት እንዳለም ይታወቃል"።
የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን በየ ጊዜው የሚቀያየሩ የኃያላን ሀገራት ባለስልጣናት የጉብኝት መዳረሻቸው ያደርጉታል። አካባቢው ግን መሠረታዊ ተብለው የሚታወቁ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ  ውስብስብ ችግሮቹ መፍትሔ አልባ ሆነው ባሉበት ሲቀጥሉ ይታያል።

Indien | G20 Antony Blinken
የአሜሪካዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ምስል Olivier Douliery/AP Photo/picture alliance


ሰለሞን ሙጬ


ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
አዜብ ታደሰ