1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ዕዳና ዓለም አቀፍ አበዳሪዎች ውዝግብ

ሰኞ፣ ነሐሴ 18 2012

ዓለምን ያዳረሰው የኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ በኤኮኖሚ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ አፍሪቃውያን ወትሮም የሚጋሩትን ስሜት ዳግም ቀስቅሷል። የወረርሽኙ ተፅዕኖ እንዳይበቃ በዓለም አቀፍ ገንዘብ አበዳሪ ተቋማት ዘንድ በአዳጊ ሃገራት መካከል የዕዳ አከፋፈል መድሎ የአህጉሪቱን እድገት መግታቱ ነው የሚነገረው።

https://p.dw.com/p/3hRAZ
Äthiopien Addis Abeba Gipfeltreffen der Staatschefs der Afrikanischen Union
ምስል picture-alliance/AA/Palestinian Prime Ministry Office

«የአፍሪቃ ዕዳ»

 

ዓለምን ያዳረሰው የኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ በኤኮኖሚ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ አፍሪቃውያን ወትሮም የሚጋሩትን ስሜት ዳግም ቀስቅሷል። የወረርሽኙ ተፅዕኖ እንዳይበቃ በዓለም አቀፍ ገንዘብ አበዳሪ ተቋማት ዘንድ በአዳጊ ሃገራት መካከል የዕዳ አከፋፈል መድሎ የአህጉሪቱን እድገት መግታቱ ነው የሚነገረው። የአፍሪቃ መሪዎች በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋምና የዓለም ባንክ በኩልም ብድር ለማግኘት የሚያደርጉት ጥረት ማብራሪያ ባልቀረበበት መንገድ ከፍተኛ ወለድ እንዲከፍሉ መተመኑ ጥያቄ አስነስቷል።  
ተሐዋሲው የየአገሩን ኤኮኖሚ አላላውስ ብሎ የመንግሥትን በጀት ግራ ባጋባበት በዚህ ወቅት የአፍሪቃ ሃገራት አቅማቸውን ያላገናዘበ የብድር ክፍያ እንዲያደርጉ መገደዳቸው ትኩረት ስቧል። የአፍሪቃ ሃገራት በአማካኝ ለህክምና ባለሙያዎችና ለህክምና ተቋማት ከሚያወጡት ይልቅ ለብድር ወለድ የሚከፍሉት እንደሚበልጥ ይነገራል። ለምሳሌ ጋና ለጤና ዘርፍ የምታውለውን በጀት ለዕዳ የምታወጣው በአምስት እጅ ይበልጣል። ከአፍሪቃ ግንባር ቀደሟ ነዳጅ አምራች ናይጀሪያም በያዝነው ዓመት የመጀመሪያ ሦስት ወራት እንደታየው ከቀረጥ ምትሰበስበው የዕዳዋን ወጪ የሚሸፍን ያህል ብቻ ነው። አሁን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ያስከተለው የኤኮኖሚ ጫና በሚታየበት ወቅት የአፍሪቃ መሪዎችና የኤኮኖሚ ባለሙያዎች አህጉሪቱ ለውስጥ ጉዳይዋ ከምታወጣው ይልቅ ከመሰል አዳጊ ሃገራት ጋር ሲነጻጸር ለዕዳ የምትገፈግፈው  መብለጡ ፍትሃዊ አይደለም በሚል ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።  አፍሪቃ የራሷ የሆኑ እንደ ግጭት፣ የፖለቲካ አለመረጋጋትና በአንዳንድ ሃገራትም አስከፊ ሙስና እንዲሁም የመሠረተ ልማት እጥረ፣ የማያላውስ ቢሮክራሲና መመሪያዎች የመሳሰሉ ችግሮች እንዳለባት ይታወቃል። ያም ሆኖ ግን የጋናው የፋይናንስ ሚኒስትር እንደተናገሩት ሌሎች አዳጊ ሃገራት በዝቅተኛ ወለድ ብድር እየተሰጣቸው አፍሪቃ ከስድስት እስከ ስምንት በመቶ እንድትከፍል መደረጉ አሳማኝ መነሻ የለውም። እሳቸው ላሉት ማሳያ አርጀንቲናና አንጎላን የሚያነጻጽሩ አሉ። ላቲን አሜሪካዊቱ አርጀንቲና በ100 ዓመት እንድትመልስ የተሰጣት ብድር ወለዱ 7 በመቶ ብቻ ነው። በተቃራኒው ከእርስበርስ ጦርነት በጎርጎሪዮሳዊው 2002 ዓ,ም የወጣችው አንጎላ ከ9 በመቶ በላይ ወለድ ያውም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንድትከፍል መደረጉን ምክንያት አልባ ይሉታል። በተመሳሳይ ደቡብ አፍሪቃ ከብራዚል፤ ኬንያም ከቦሊቪያ የበለጠ የብድር ወለድ ከፋዮች ናቸው። ቀደም ሲል የላይቤሪያ የሥራ ጉዳይ ሚኒስቴር የነበሩትና አሁን የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ጥናት ማዕከል የፖሊሲ ከፍተኛ ተመራማሪው ጋዩዴ ሞሬ ለላቲን አሜሪካ ሃገራት የተሰጠው ዝቅተኛ የወለድ መጠንን መመልከቱ ለአፍሪቃ ሃገራትም ተመሳሳይ አካሄድ መከተል ይገባል የሚል መከራከሪያ እንዲነሳ ዕድል አመቻችቷል ይላሉ። 
«አርጀንቲና ብድሯን ወደሌላ የማዞር ታሪክ ያላት ሀገር ናት፤ ይህቺው ሀገር ናት የብድር ጫና እያለባት ተጨማሪ 2 ቢሊየን ዶላር እንዲሰጣት የሚጠየቀው፤ በዚያም ላይ እስከ 100 ዓመት ድረስ መክፈል አይጠበቅባትም። እንዲህ ያለው አሠራር ነው በአፍሪቃ ሃገራት በኩል ተመሳሳይ አካሄድ መከተል ይገባል የሚለውን ጥያቄ ለማንሳት ምክንያት የሆነው።»
በዚሁ ማዕከል ተባባሪ ተመራማሪዋ ማአ አማራ ደግሞ እንዲህ ያለው ማበላለጥ የአፍሪቃ ሃገራት ለብድር ፊታቸውን ወደቻይና እንዲያዞሩ ካደረጋቸው ምክንያት አንዱ ነው ባይ ናቸው። እንደውም እንደየዓለም የገንዘብ ተቋም ያሉት ከሚጠይቁት የወለድ መጠንና ጠንካራ ቅድመ ሁኔታዎች የቻይና የብድር መስፈርት የተሻለ መሆኑንም ያመለክታሉ። ባለሙያዎቹ እንደሚሉት የአፍሪቃ ሃገራት አሁን ለሚያሰሙት ቅሬታ መነሻ የሆነው ሌላው ጉዳይ ውሱን የሆነው የብድር ታሪካቸው ነው። ይህም ቢሆን በዕዳ ቅነሳ፣ በድርድርና የዕዳ መጠንን በመገደብ የታጀበ ነው። የሚሰጡ ብድሮችን በተሳሳተ አቅጣጫ የማዋል ወይም ከታሰቡበት ፕሮጀክት ወደሌላ የማዛወር፣ የበጀትን ሚዛ ማስተካከያ ማድረግ ለምሳሌ ለመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች መደጎሚያ ማዋል አንዳንዴም የመገበያያ ሸርፍን መደጎም ችግር የሚያስከትል አሠራር መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ። የዓለም የገንዘብ ድርጅት ግን ከሚሰጠው ብድር ከአራቱ አንዱ ብቻ ለመረሠተ ልማት ማስፋፊያ ቢውል ነው ባይ ነው። እንደባለሙያዎቹ ማብራሪያም የአፍሪቃ ሃገራት የሚጣልባቸውን የብድር ወለድ የሚመጥኑ ተቋማት የጉዳዩ ተጠያቂዎች ይመስላሉ። ሞሬ እንደሚሉትም እነዚህ ተቋማት አህጉር አፍሪቃን በደንብ የሚያውቁ አለመሆናቸው ለችግሩ አስተዋጾኦ አለው። 
«ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ጽሕፈት ቤት ያላቸው ሦስቱ ገማች ተቋማት በመላ አህጉሪቱ ለሚሆነው ኃላፊነት አለባቸው። ነገር ግን ምን ያህል ያውቃሉ? በተቃራኒው አንድ ጽሕፈት ቤት ሜክሲኮ፣ አንድ ብራዚል እንዲሁም አንድ ሌላ ጽሕፈት ቤት ቺሌ ላይ አለ።»
በዚያም ላይ ወለዱን ለመወሰን የሚያስችለው ተአማኒነት ያለው መረጃ እጥረት ምዕራባውያን መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች መላ አፍሪቃን በተመሳሳይ ቀለም እንዲመለከቱ አድርጓል። ለዚህ ደግሞ አፍሪቃውያን በውሳኔ ሰጪነት ደረጃ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋም ውስጥ አለመካተታቸው አንዱ ነው የሚሉም አሉ። ሞሬ ግን በተቋማቱ ውስጥ የአፍሪቃውያን አለመኖር ሳይሆን ችግሩን ከሥር መሠረቱ የሚገዘቡት ተቋማቱ በተዋቀሩበት አስተሳሰብ ስለሆነ ነው በማለት ይሞግታሉ። ስለዚህም የአፍሪቃ ሃገራት ይህን የተዛባ አመለካከት ለመለወጥ ተባብረው በመሥራት ዓለም አቀፍ ተቋማቱም ሆኑ የወለድ መጠኑን የሚወስኑት ድርጅቶች ማብራሪያ እንዲሰጧቸው መጠየቅ እንዳለባቸው ያሳስባሉ። 

Gipfel Afrikanische Union Addis Abeba
ምስል dapd
USA Wirtschaft Washington DC Zentrale der Weltbank Gebäude Logo
ምስል ullstein bild - Fotoagentur imo

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ