1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ መሪዎች የዕርቅ ጥረት ለምን?

ቅዳሜ፣ ሰኔ 17 2015

"ጦርነቱ በአፍሪካ አገሮች ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል ። በመሆኑም የአፍሪካ ሃገሮች ወደ ሰላም ጥረቱ የገቡት ጦርነቱ እንዲያበቃ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ነው። ይህም በጦርነቱ ምክንያት የተጎዳውን ኢኮኖሚ ለማንሰራራት ይረዳቸዋል። ። "

https://p.dw.com/p/4SzkK
Afrikanische Delegation zu Besuch in Russland
ምስል Evgeny Biatov/RIA Novosti/picture alliance

ትኩረት በአፍሪቃ

የአፍሪቃ መሪዎች የዕርቅ ጥረት

በሩሲያና በዩክሬን መካከል ያለውን ግጭት ለማስቆም የሚሞክሩት ስድስት የአፍሪካ መሪዎች ባሳለፍነው ሳምንት በኪይቭ እና በሞስኮ ተገኝተው ፕረዚደንት ዘለንስኪን እና ፕረዚደንት ፑቲንን አነጋግረው ተመልሰዋል። የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ የአፍሪካን የሰላም ልዑክ የመሩት ሲሆን ደቡብ አፍሪካ ፣ ሴኔጋል ፣ ኡጋንዳ ፣ ዛምቢያና ኮንጎ ሪፑብሊክ በልዑኩ ከተካተቱ ሃገሮች ይገኙበታል። 
የደህንነት ባለሙያ ዶክተር ካቢር አዳሙ ለDW የእንግሊዝኛ ክፍል በሰጡት አስተያየት
"የአፍሪካ አገሮች በገለልተኝነት አቋማቸው የቀጠሉ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሩሲያና ዩክሬን ወደ አፍሪካ አገሮች ትኩረታቸውን ያዞሩ ይመስላሉ።  በጉዳዩ የመሳተፍና የመካተት ፍላጎትም አለ ፤ ይህ ማለት ሰላምን ለማምጣት ለማደራደር የሚያስችሉ ዲፕሎማሲያዊ ዕድሎች እንዲኖሩ ያደርጋል።“

የአፍሪካ የሰላም ጥረት ዕውን የሆነው ዩናይትድ ስቴትስ  ደቡብ አፍሪካ ለሩሲያ የጦር መሣሪያ ታቀርባለች በማለት ከሰሰች በኋላ ነው ። ፕሪቶሪያ በበኩሏ ውንጀላውን በማስተባበል በሩስያና ዩክሬይን ጦርነት የገለልተኛነትን መርህ እንደምትከተል አጥብቃ ገልጻለች ።

አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች የተባበሩት መንግሥታት በጦርነቱ ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ ድምጻቸውን ማቀባቸው ይታወቃል። የአፍሪካ የገለልተኝነት አቋም በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን በዩናይትድ ስቴትስና በሶቪየት ኅብረት መካከል ለሁለት ተከፍሎ ነበር።

የደህንነት ባለሙያው ዶክተር ካቢር ወደኋላ መለስ ብለው የአፍሪካ ሃገሮች እንደየ ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ሁኔታ ይወስዱት የነበረውን አቋም እንዲህ ያስታውሳሉ።
"የአፍሪካን አገሮች ታሪክና የቀዝቃዛው ጦርነት ታሪክ መለስ ብለን ማየት ያስፈልገናል። በዕውነቱ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች የገለልተኝነት አቋማቸውን ጠብቀው በቆዩበት ቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ከኔቶም ሆነ ከዋርሶ ጋር ግንኙነት የነበራቸው እንዴት እንደሆነ መለስ ብለን መመልከትና ማስታወስ ይኖርብናል ። ዛሬ እያየን ያለነውም ይህንኑ ነው ። ሶቪየት ኅብረት ከፈራረሰች በኋላም ቢሆን የአፍሪካ አገሮች ከኔቶም ሆነ  ከሩሲያ እንዲሁም  ከቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ከወጣችው ከዩክሬን ጋር የነበራቸውን ግንኙነት አስጠብቀው እየሄዱ ነው ። "

Afrikanische Delegation zu Besuch in Russland
ምስል AP

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር የካቲት 24, 2022 ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ወዲህ በርካታ ምዕራባውያን አገሮች ጣልቃ ለመግባት ሞክረዋል ። ታዲያ አፍሪካ ይህን ጦርነት እንዲቆም የምትፈልገው ለምንድን ነው? ዶክተር ካቢር
"ጦርነቱ በአፍሪካ አገሮች ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል ። ጦርነቱ እንዲቀጥል ከተደረገ ደግሞ ይህ ሁኔታ ተባብሶ ይቀጥላል። እንዲሁም በበርካታ የአፍሪካ አገሮች የኢኮኖሚ መፈራረስ ሊያስከትል ይችላል ። በመሆኑም የአፍሪካ ሃገሮች ወደ ሰላም ጥረቱ የገቡት ጦርነቱ እንዲያበቃ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ነው። ይህም በጦርነቱ ምክንያት የተጎዳውን  ኢኮኖሚ ለማንሰራራት ይረዳቸዋል። ። "

የማሊ ሕዝበ ውሳኔ
በአለፈው እሁድ በማሊ በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መራጮች የማሊ የወደፊት ረቂቅ ሕገ መንግሥት ለመወሰን  ድምጻቸውን ሰጥተዋል። ሂደቱ በሚቀጥለው ዓመት ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ መንገድ ይከፍታል ተብሎ ይጠበቃል ።
ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው ሕዝበ ውሳኔ ማሊ ከሦስት ዓመት ወታደራዊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር ለመውሰድ  አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ተብሎለታል ።
እ.ኤ.አ ከነሐሴ 2020 ጀምሮ በአጭር ወራት ልዩነት በተፈጸሙ ሁለት  መፈንቅለ መንግስቶች በስልጣን ላይ ያለው ወታደራዊ ጁንታ እ.ኤ.አ በየካቲት 2024 ምርጫ እንደሚካሄድ ቃል ገብቷል ። ለዚህ ምርጫ የሚያግዝ ነው የተባለለት እና በሃገሪቱ ህገ መንግስት ላይ የሚደረጉ ማሻሻያዎች ያካተተ ህዝበ ውሳኔ ነበር በአለፈው እሁድ የተካሄደው።

የምርጫ ታዛቢዎች በመጀመሪያው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ለአብዛኛው ድምጽ ሰጪዎች የቅድመ ምርጫ ትምህርት አለመሰጠቱን ገልጸዋል። ቅንጅት ለዜግነት ምርጫ የተባለ የታዛቢዎች ቡድን፤  ታዛቢዎቹ ጋኦና ቲምቡክቱ ውስጥ እንዳይገቡ መከልከላቸውን ገልጿል ። በተጨማሪም ቡድኑ በምርጫ ጣቢያዎች የምርጫውን ሂደት የሚያመላክቱ ዝርዝር ነገሮች እና ለምርጫው የሚያስፈልጉ ሰነዶች በግልጽ ታትመው እንዲታዩ አለመደረጉን ጠቅሷል።
ቁልፍ ሕገ መንግሥታዊ ለውጦች

ለሕዝበ ውሳኔ የቀረበው ረቂቁ ህገመንግስት ካካተታቸው ለውጦች ፕሬዚዳንቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ሚኒስትሮችን የመሾም ወይም የመሻር እንዲሁም  ፓርላማን የመበተን ሥልጣንን ያጠናክራል ። በተጨማሪም የማሊ የሥራ ቋንቋ ፈረንሳይኛ እንደሆነ በቀድሞው ህገመንግስት የተደነገገውን  ለመፋቅ የሚያስችል ዕድል እንዳለው ታውቋል።
አዲሱ ህገ መንግስት ማሊን "ገለልተኛ ፣ ሉአላዊ ፣ አሃዳዊ ፣ ዲሞክራሲያዊ ፣ ሃይማኖት በመንግስት ጉዳይ መንግስትም በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ የማይገባባት ማኅበራዊ ሪፑብሊክ" ብሎ በመግለጹ በሃይማኖት መሪዎች መካከል ውዝግብ አስነስቷል ።

DW Videostill | Wahl Mali für neue Vefassung
ምስል DW

በሕዝበ ውሳኔው ላይ የታዩ የደህንነት ስጋቶች

እንደ ሲ ኦሲ ኤም የምርጫ ታዛቢ  ከሆነ በቀድሞው የቱዋሬግ አማጺያን በቁጥጥር ሥር የዋሉትን ኪዳል የተባለ ክልልን ጨምሮ በሰሜናዊ ማሊ አንዳንድ አካባቢዎች ድምፅ የመስጠት ሥራ አልተከናወነም ብሏል። አያይዞም ከድምጽ አሰጣጥ ስነስርዓቱ አስቀድሞ በአካባቢው የጸጥታ ስጋት እንዳለ ሲያሳስብ ነበር።
እሁድ ዕለት ድምፅ የመስጠት ሂደት በኪዳል ውስጥ አልተካሄደም ያሉት የታዛቢ ቡድኑ አባል የሆኑት ሳሊያ ካሪቡ ለDW ተከታዩን ብለዋል።
"ከምርጫ ታዛቢዎቻችን አንዱ ወደ ምርጫ ጣቢያው ሲሄድ እዛ ምንም ድምጽ እንዳልተሰጠ ተነግሮታል። ይህ የሆነውም ምርጫው በኪዳል ክልል እንዳልተካሄደ ካረጋገጥን በኋላ ነበር ። ይህን ተከትሎ ሌላ ተግባራዊ ምልከታም አድርገናል። በምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ዝርዝር ሰነዶች አለመታየታቸው እንዲሁም በጽሑፍ የታተሙ የምዝገባ ሰነዶች አለመኖራቸው ለማረጋገጥ ችለናል። ይህም ድምጽ ሰጪው በትክክል የዚያ አካባቢ ሰው መሆኑን እና ስሙ ማን እንደሆነ ለማወቅ የሚያስችሉ ሰነዶች ናቸው፤ እነዚህ ሰነዶች አልነበሩም። በጋኦና ቲምቡክቱ ታዛቢዎቻችን እንዲወጡ መደረጉን በጣም አሳስቦናል።"

Mali Bamako | Abstimmung über Verfassungsänderung
ምስል AFP

እ.ኤ.አ በ2015  ከመንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት የተፈራረመው የማሊ መንግሥትን ለዓመታት ሲዋጋ የነበረው  በእንግሊዘኛ ምህጻሩ CMA የተባለ የአማጺዎች ቡድን የኪዳል ክልል የጸጥታ የጥበቃ ኃላፊነት የተሰጠው ነው ።
በአልጀርስ የሰላም ስምምነት መሠረት የቀድሞ ተዋጊዎች የተወሰነ የራስ ገዝ አስተዳደር እንዲያገኙና በሰሜን በኩል የደኅንነት ጥበቃ እንዲደረግላቸው እንዲሁም  በማሊ እንደገና በተዋቀረ ሠራዊት ውስጥ እንዲካተቱ ዕድል ተሰጥቷቸው ነበር ።የሰላም ስምምነቱ በቀድሞ ተዋጊዎችና በባማኮ መንግሥት መካከል የተፈጠረው ውጥረት ሙሉ በሙሉ ለማርገብ ተግባራዊ የሚሆን ነው የተባለለት ነበረ።

Mali Bamako | Abstimmung über Verfassungsänderung
ምስል AFP

የሰላም ስምምነቱ ምን ያህል ውጤታማ ነው?

በሳሄል የደህንነት እና ስትራቴጂካዊ ጥናቶች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አል ቱንካራ  ለፀጥታ ኃይሎች አስቀድሞ እንደጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በሰኔ 11 በኪዳል  ክልል የተካሄደው  የድምፅ አሰጣጥ   የማሊን ጁንታ ሥጋት ላይ እንደሚጥል ይታሰባል ይላሉ።
“በኪዳል የምርጫ ጣቢያ አስቀድሞ በጸጥታ እና የደህንነት ሃይሎች የተካሄደው የሕዝበ ውሳኔ የማሊ ማዕከላዊ መንግስት በግዛቲቱ ያለውን የማስተዳደር አቅም ከቁጥጥር ውጭ እየሄደ መሆኑን ግልጽ ማሳያ ነው። በአንጻሩ ደግሞ የሰላም ስምምነቱና የብሔራዊ እርቁ ውጤታማነትም ማሳያ ነው። እንዲሁም ከቀድሞ አማጺያን አንጻር ሲታይ ደግሞ ከመገንጠል ፍላጎታቸው ጋር የሚስማማ ነው።“ በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ይሁን እና ይላሉ ታንካራይሁን እና  በኪዳል ውስጥ አሁን እየታየ ያለው ተግዳሮት "ለሰላምና ለብሔራዊ እርቅ ስምምነቱ ውጤታማነት ጥያቄ ያስነሳል" በማለት አስረድተዋል።


ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

እሸቴ በቀለ