1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአገር ዐቀፍ ፓርቲዎች አካታችነት ጉዳይ! 

ዓርብ፣ የካቲት 26 2013

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጥያቄ ውስጥ የአካታችነት ጥያቄ ትልቁና ዋነኛው ጉዳይ ነው። የማንነት ጥያቄ፣ የፆታ እኩልነት ጥያቄ፣ የብሔር ጥያቄ እየተባለ በተለያየ ሥም ቢመጣም ቅሉ ዞሮ ዞሮ የአካታችነት ጥያቄ ነው። 

https://p.dw.com/p/3qGw7
180621 Kolumne BefeQadu Z Hailu

የአገር ዐቀፍ ፓርቲዎች አካታችነት ጉዳይ! 

በፍቃዱ ኃይሉ 

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጥያቄ ውስጥ የአካታችነት ጥያቄ ትልቁና ዋነኛው ጉዳይ ነው። የማንነት ጥያቄ፣ የፆታ እኩልነት ጥያቄ፣ የብሔር ጥያቄ እየተባለ በተለያየ ሥም ቢመጣም ቅሉ ዞሮ ዞሮ የአካታችነት ጥያቄ ነው። 

አንዳንዴ ጥያቄው የአንድ ብሔር ብቻ መሥሎ ሲቀርብ ይታያል። አንዳንዱ ብሔረሰብ ከማዕከላዊ መንግሥቱ ተገልያለሁ የሚል ጥያቄ ሲሰነዝር፣ የብሔር ጥያቄ ለመመለስ በሚል የተመሠረተው  ስርዓት እኔን ማግለያ ሆኗል የሚል ጥያቄም ተነስቷል። ለዚህ አንዱ ምክንያት ማግለልን ለመመከት የተመሠረቱት የፖለቲካ ንቅናቄዎች መገለልን ለአግላይነት ሰበብ መጠቀማቸው ነው። 

የሆነው ሆኖ የአካታችነትን ጉዳይ ከምርጫ ተፎካካሪዎች አንፃር መመልከት ስላለፈው ብቻ ሳይሆን ስለመጪው ጊዜም እንድንረዳ ያደርገናል። ለመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ምን ያህል አካታች ናቸው? 

የብሔር አገር ዐቀፍ ፓርቲዎች 

ታዋቂዎቹ የብሔር ፓርቲዎች በተለምዶ ክልላዊ ፓርቲ ተደርገው ነው የሚታሰቡት። ምዝገባቸው ግን አገር ዐቀፍ ነው። ለምሳሌ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፣ የኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ (ኦነን) እንዲሁም ራያ ራዩማ በብሔር ፓርቲነታቸው ይታወቁ እንጂ በመዝገብ ላይ አገር ዐቀፍ በመሆናቸው አቅማቸው ከፈቀደ በሁሉም ክልሎች ተንቀሳቅሰው፣ አባላት አደራጅተው፣ ተወዳድረው መመረጥ ከቻሉ በፌዴራልም ይሁን በሁሉም ክልሎች ውስጥ መንግሥት መመሥረት ይችላሉ። ነገር ግን ይህንን ፓርቲዎቹ ራሳቸው የሚያስቡት አይመስለኝም። ምክንያቱም መርሐቸው ሌላ ነው። 

የብሔር ፓርቲዎች ምንም እንኳን መነሻቸው "የብሔር ጭቆና" ወይም "የብሔር መገለል" ቢሆንም ቅሉ፥ እንኳን ብዝኃነትን ሊያገናዝቡ፣ በውስጣቸው ያለውን ልዩነት እንኳን ለማስተናገድ ብዙም ፍላጎት አያሳዩም። በዚህም ሳቢያ ፓርቲዎቹ አንድን ብሔር እንወክላለን ቢሉም ማኅበራዊ መሠረታቸው ብዙ ጊዜ ከሊቀ መንበራቸው ወይም መሥራቾቻቸው የትውልድ ሥፍራ አይርቅም። የብሔር ፓርቲዎች አገር ዐቀፍ ፓርቲ ሆነው የሚመዘገቡት ምክንያት "ከክልላቸው ውጪ" ያሉትን የብሔሮቻቸውን ተወላጆች ዒላማ በማድረግ እንጂ ሁሉን ዐቀፍ ፓርቲ የመመሥረት ዓላማ ስላነገቡ አይደለም። ይህ ምክንያት ነው እነዚህ ፓርቲዎች "ሌሎች ክልሎች" ውስጥም ተወዳድረን መንግሥት መመሥረት እንችላለን ብለው የሚያስቡ አይመስለኝም ያስባለኝ። 

የብሔር ፓርቲዎች "ከክልላቸው ውጪ" የብሔሮቻቸው ተወላጆች ዒላማ በማድረግ አገር ዐቀፍ ሆነው ሲመሠረቱ፣ በሌላ በኩል "የክልላቸው" ብሔር ተወላጆች "ሌሎች" ክልሎች ውስጥ በቂ ወይም ትክክለኛ ውክልና አያገኙም የሚል ቅድመ ግምት አሳድረዋል ማለት ይቻላል። ነገር ግን "በክልላቸው" ውስጥ ያሉ የሌላ ብሔር ተወላጆችን በቂ ወይም ትክክለኛ ውክልና በመስጠት የሌሎችን ስህተት ሲያርሙ አይስተዋልም። 

የዜግነት አገር ዐቀፍ ፓርቲዎች 

ከብሔር ፓርቲዎች ትይዩ የሚቀመጡት የመደራጃ መሥፈርታቸውን ዜግነት ብቻ አድርገው በርዕዮተ ዓለም ወይም በሥም ብቻ የተለያዩትን ፓርቲዎች ናቸው። እነዚህ ውስጥ ገዢው ብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ)፣ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ፣ መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) እና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት (ኢዲዩ) የመሳሰሉት ይገኙበታል። 

የዜግነት አገር ዐቀፍ ፓርቲዎች በመርሕ ደረጃ በራቸው ለሁሉም ክፍት ቢሆንም፣ በርዕዮተ ዓለማቸው፣ ወይም ሁሉን ዐቀፍ ለመሆን የሚያስፈልገውን ተጨማሪ እርምጃ ለመራመድ በመስነፍ ወይም ባለመፈለግ ብዙውን ግዜ የቢጤዎች ጉባዔ ሆነው ይታያሉ። ብልፅግና ፓርቲ ከሌሎቹ የተሻለ የሀብት እና ደኅንነት ዋስትና ስላለው ብዙዎችን መሳብ የሚችል ቢሆንም፣ ውስጣዊ የርዕይ አንድነት ማጣቱ "ቅርንጫፍ" በሚባሉት ክልላዊ አመራሮች ተከፋፍሎ እርስ በርስ የሚወነጃጀልበትም ጊዜ አለ። ሆኖም ከየትኛውም ፓርቲ የተሻለ ብዝኃነት በጠቀስናቸው ዕድሎቹ ተጎናፅፏል። ሆኖም ሴቶችን፣ የተለያዩ እምነት ተከታዮችን በአባልነት እና አመራርነት በማቀፍ ማኅበራዊ መሠረታችን ከሚሉት ማኅበረሰብ ጋር ማመሳሰል ተስኗቸዋል። 

እንደ ኢዜማ ያሉ ፓርቲዎች ደግሞ አደረጃጀታቸው ለአካታችነት ምቹ ቢሆንም "የብሔር ፖለቲካ" አራማጆች የሚሰነዝሩባቸውን ትችቶች እና ፍረጃዎች ባግባቡ መመከት ባለመቻላቸው በተግባር በብዝኃነት የተገነባ አካታችነታችነት አይታይባቸውም። ከዚያም በላይ ሴቶችን እና አካል ጉዳተኞችን ለማካተት የተለያዩ ጥረቶችን ያደረጉትን ያክል ኅብረ ብሔራዊ ለመሆን ወይም ለመምሰል ጥረት ሲያደርጉ አልታዩም። 

በዜግነት የተሰባሰቡት የአገር ዐቀፍ ፓርቲዎች በበቂ ሁኔታ አካታች ሆኖ አለመገኘት ወይም አለመታየት ለምሳሌ በኦሮሚያ እንደታየው የብሔር ፓርቲዎች ምርጫውን አቋርጠን እንወጣለን ሲሉ፣ አማራጭ ተቃዋሚ ፓርቲ እንደሌለ ለመታሰቡ አስተዋፅዖ አድርጓል። 

ስውር ብሔርተኝነት 

ሌላኛው የብሔር አገር ዐቀፍ ፓርቲዎች በይፋ የሚናገሩትና የዜግነት አገር ዐቀፍ ፓርቲዎች የሚታሙበት ጉዳይ ብሔርተኝነት ነው፤ የኋለኛውን ስውር ብሔርተኝነት ይሉታል። የዜግነት አገር ዐቀፍ ፓርቲዎች ብቸኛ መስፈርታቸው መሆን ያለበት ዜግነት እና ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለማቸው ቢሆንም የታሪክ አረዳዳቸው እና ትርክታቸው ከአንድ ብሔር ጋር የሚሰምርበት ጊዜ ብዙ በመሆኑ ስውር ብሔርተኝነት ይከተላሉ በሚል ይታማሉ። በዚህም ምክንያት የሚገፏቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች በመኖራቸው ብዝኃነትን ማስተናገድ አይቻላቸውም። 

በመነሻችን እንዳነሳነው የአካታችነት ጥያቄ ላለፉት አምስት ምዕተ ዓመታት ጎልቶ የሚሰማ ጥያቄ ቢሆንም፥ ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ ቁመና እንደምንረዳው ደግሞ መጪው ጊዜም ብዙ ተስፋ አይሰጥም።

በፍቃዱ ኃይሉ

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሐፊው እንጂ የዶይቸ ቬለ (DW)ን አቋም አያንጸባርቅም!