1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአያያዝ ጥበብ የሚያሻው የተፈጥሮ ሃብት

ማክሰኞ፣ መስከረም 12 2013

በ2012ዓ,ም የክረምት ወቅት ጨምሮ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሚባል ዝናብ ያገኘችበት እንደሆነ ይነገራል። መጠኑ ከፍተኛ መሆኑን ካመላከቱት አንዱ በዚሁ ዓመት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተከሰተው የወንዝ ሙላትና ጎርፍን መጥቀስ ይቻላል። አጋጣሚውም የጠፉ የውኃ አካላት መልሰው እንዲከሰቱ ዕድል ፈጥሯል። በዘላቂነት ለመጠቀም የሚያስችል ስልት ይሆን?

https://p.dw.com/p/3ir4S
Äthiopien Haramaya See
ምስል DW/Mesaye Tekelu

የአያያዝ ጥበብ የሚያሻው የተፈጥሮ ሃብት

የዘንድሮው ክረምት በአንድ በኩል ወገኖቻችንን ከቤት ንብረታቸው የሚያፈናቅልና በእርሻቸው ላይም ጉዳት ያስከተለ ጎርፍ ቢያመጣም ደርቀው የከረሙ ስፍራዎችን አረስርሶ ጠፉ የተባሉ የውኃ አካላትን ዳግሞ በጠለ በረከት ሞልቷል። ኢትዮጵያ ውኃን ጨምሮ በተፈጥሮ ሀብቶች የታደለች ሀገር መሆኗ ብዙም አያነጋግርም፤ ሆኖም ከባለሙያዎች ምክረ ሃሳብ ይልቅ በፖለቲካው ዘዋሪዎች ሚና የአያያዝ ጥበቡ እንደራቃት የሚናገሩ ጥቂት አይደሉም። በኢትዮጵያ የወራት ስሌት መሠረት በያዝነው መስከረም ወር ማለቂያ ግድም በሚጠናቀቀው የክረምት ወቅት ከዝናብ የተገኘውን ውኃ በዘላቂነት መጠቀም ይቻል ይሆን? 

ከሁለት ዓመታት በፊት ለንባብ የበቃ አንድ ጥናት ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከከርሰ ምድር በላይ 123 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር እንዲሁም ከከርሰ ምድር 2,6 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ እንደምታገኝ ያመለክታል። ሆኖም ግን የአፍሪቃ የውኃ ማማ እየተባለች የሚትወደሰው ኢትዮጵያ  ያለአግባብ ጥቅም ላይ በመዋሉ እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሀገሪቱ ሊጠፉ የተቃረቡ ሐይቆች እንዳሏት ይገልጻል። ይህን መሰሉን ጥናት የሚያጠናክሩ ሌሎች መረጃዎችም በየጊዜው ሲነገሩ ቆይተዋል። በዋናነትም የሃረማያ ሐይቅ እንዲሁም በስምጥ ሸለቆው አካባቢ የሚገኙ ጥቂት የማይባሉ ሐይቆች ውኃቸው እያነሰ ብሎም እየተመረዘ እነሱን መኖሪያ መገኛቸው አድርገው ተጠግተውባቸው የነበሩ አእዋፍ መጥፋት የመጀመራቸው ዜናም በዚሁ መሰናዶ የቀረቡበት አጋጣሚ ይታወሳል። ጎርፍ ያስከተለው የ2012 ዓ,ም ዝናብ በዙሪያው በሚከናወን የመስኖ ግብርና ሰበብና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ጠፍቶ የከረመውን የሃረማያ ሐይቅ ውኃ መመለሱ ተነግሯል። እርግጥ ነው ሐይቁ ቦታው ላይ ተገኝቷል፤ ሲመለስም የመጀመሪያው አይደለም። ይሰነብታል ብሎ በሙሉ አፍ መናገርም አይቻልም። በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር አስፋው ከበደ።

 «ካለፈው እንዳየነው በዚህ ክረምት ላይ የተሻለ ውኃ ገብቶበታል ወደሐይቁ። ካልተለካ በስተቀር ይሄን ያህል ውኃ ገብቶበታል ብሎ መናገሩ ትንሽ ያስቸግራል፤ ምናልባት ላይቆይ ይችላል በሚለው ላይ እኔም ሼር የማደርገው ሃሳብ ነው። ምንድነው እኛ አካባቢ እዚህ ሐይቁ ዙሪያ የሚኖሩ ገበሬዎች በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ይሄ ካሽ ክሮፕን ያመርታሉ፤ አትክልቶች(ቬጂቴብልስ) እንደጫት የመሳሰሉትን ማለት ነው። እናም ለመስኖ ከፍተኛ ውኃ ስለሚጠቀሙ እዚያ ላይ ሥራ ካልተሠራ በስተቀር የመቆየት ዕድሉ ያጠራጥራል።»

በሃራማያ ሐይቅ አካባቢ ከሚካሄደው ግብርና በከፊል
ምስል DW/M. Teklu

እሳቸው እንደሚሉት ከዚህ ቀደም ደህና ክረምት በነበረበት አጋጣሚ እንደዘንድሮው ባይሆንም የተወሰነ ውኃ ሃረማያ ሐይቅ ውስጥ ገብቶ ነበር። ሆኖም በአካባቢው የተለያዩ አትክልቶችና ጫትን ጭምር ለማብቀል በሚከናወነው የእርሻ እንቅስቃሴ ከአቅሙ በላይ ለመስኖ በመዋሉ ተመልሶ ጠፍቷል። ለእነዚህ ወገኖች አማራጭ የውኃ አቅርቦትም ሆነ አጠቃቀሙ ላይ ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄ እስካልተደረገ ድረስ አሁን የሚታየው የሐይቁ ውኃም ዕጣው ተመሳሳይ መሆኑ የሚያሻማ አይደለም እንደባለሙያው።  

በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር  የሆኑት ዶክተር አስፋው ለሃረማያ ሐይቅ ውኃ መድረቅ ዋናው መነሻ ምክንያት ወደሐይቁ የሚገባው እና ለመጠጥም ሆነ ለእርሻ የሚወጣው ውኃ ብዛት አለመመጣጠኑ ነው። በዚያም ላይ ሃረማያ ሐይቅ ለከተማዋ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ላሉ እና እስከ ሐረር ድረስ ለሚገኙ ከተሞች የመጠጥ ውኃ ምንጭ በመሆን የኖረ ሐይቅ ቢሆንም አፈርና ውኃን ለመቆጣጠር የሚሠሩ ሥራዎች አልተሠሩለትም። ከዚህም ሌላ ባለሙያው እንደሚሉት በሃረማያ ሐይቅ አካባቢው ትናንሽ ሐይቆች ያሉ ሲሆን፣ የእነዚያ ሐይቆች ሞልተው በመፍሳቸው ለሃረማያ በረከታቸው ተርፏል። የደንና ተፈጥሮ ሃብት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ሙሉጌታ ልመንህ ባለሙያዎች በተለያዩ ጊዜያት የሚያቀርቧቸው ጥናቶችም ሆኑ የሚሰጧቸው ምክረ ሃሳቦች ተግባራዊ ባለመሆናቸው የሚታይ መሻሻል አለመኖሩን ከታዘቡ ምሁራን አንዱ ናቸው። የተፈጥሮ ሀብት ችግር የለባትም በሚሏት ኢትዮጵያ የአያያዝ ችግር መኖሩን አፅንኦት ይሰጣሉ። በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር አስፋው ከበደም የተፈጥሮ ሃብት አጠቃም ችግር በሀገሪቱ አለ የሚለውን የባለሙያውን ሃሳብ ይጋራሉ። በሌላ በኩል ጠፍቶ የከረመው የሃረማያ ሐይቅ ተመልሷል ለማለት ጥቂት ዓመታት መቆየት እና በቅርበትም ውኃው እንዲመለስ ያስቻለውን የተፈጥሮ ሀብት መጠበቂያ ስልት መርምሮ በመረጃ ማስደገፍ እንደሚጠይቅ ነው የደንና ተፈጥሮ ሃብት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ሙሉጌታ ያመለከቱት።
ዘንድሮ በርከት ያለ ዝናብ ኢትዮጵያ ማግኘቷን የተከሰቱት የጎርፍ አደጋዎች ሁሉ ያመላክታሉ። እንደው ይህን ውኃ አጠራቅሞ ለረዥም ጊዜ መጠቀም የሚቻልበት መንገድ ይኖር ይሆን? የሃረማያ ሐይቅን በተመለከተ ዶክተር አስፋው ከበደ የአካባቢው ኅብረተሰብ ያመነበት ውኃውን በዘላቂነት ለመጠቀም የሚያስችል ስልት መከተል እንደሚቻል ይናገራሉ። እንዲህ ባለ አጋጣሚ የተገኘን በርከት ያለ ውኃ ግድብ ሠርቶ በደረቁ ወቅት ለልማት ማዋል እንደሚቻል ዶክተር ሙሉጌታም ይመክራሉ። በነገራችን ላይ ሃረማያ ሐይቅ ደርቆ በነበረበት ወቅት በአካባቢው የግብርና ሥራ የሚያከናውኑ ወገኖች ውኃ ለማግኘት የሐይቁን ዙሪያ እየቆፈሩ በከርሰምድር ውኃ ይጠቀሙ እንደነበር ነው ለመረዳት የቻልነው። አሁን ውኃው በመሙላቱ ወደቀደመው የመስኖ አጠቃቀም ከተመለሱ የመድረቁ አዙሪት መመለሱ የሚቀር አይመስልም። እናም አሁን አጠቃቀሙ ብክነትን መቀነስ ላይ ማተኮር እንዳለበት በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር አስፋው ከበደ አመልክተዋል። ለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ ምሁራኑን እናመሰግናለን።

በሃራማያ ሐይቅ አካባቢ ከሚካሄደው ግብርና በከፊ
ምስል DW/M. Teklu

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ