1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ ህብረት እና የቱርክ ውል 

ማክሰኞ፣ መጋቢት 12 2009

የቱርክ ፖለቲከኞች በአንዳንድ የአውሮጳ ከተሞች ለቱርክ ህገ መንግሥት ማሻሻያ ህዝበ ውሳኔ ፣ሊያካሂዱ ያቀዷቸው የህዝብ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ዘመቻዎች መከልከላቸው በህብረቱ እና በቱርክ የስደተኞች ውል ላይ ጥላ አጥልቷል ። የቱርክ ፕሬዝዳንት ዘመቻው የተከለከለባቸውን ሀገራት መሪዎች ናዚ እያሉ ከመዝለፋቸው በላይ ውሉን እንደሚያፈርሱም እየዛቱ ነው ።

https://p.dw.com/p/2ZdEY
EU Türkei Migration Flüchtlingsabkommen
ምስል DW/D. Cupolo

የአውሮጳ ህብረት እና የቱርክ የስደተኞች ውል

የአውሮጳ ህብረት እና ቱርክ ህገ ወጥ የሚሉትን ስደት ለመከላከል የተፈራረሙት ውል ባለፈው ሳምንት አንድ ዓመት ሞልቶታል።ውሉ ወደ አውሮጳ የሚገቡ ስደተኞች እና ተገን ፈላጊዎች ቁጥር እንዲቀንስ በማድረግ በአውሮጳው መንግሥታት ይወደሳል።የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ግን ስደተኞችን ለተለያዩ አደጋዎች የሚያጋልጥ ነው ሲሉ ውሉን መቃወማቸውን ቀጥለዋል።የዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን ውሉ አምጥቷል የሚባለውን ውጤት ስጋቶቹን እና ተቃውሞዎቹን ያስቃኘናል። 
የአውሮጳ ህብረት እና ቱርክ ህገ ወጥ የሚሏቸው ስደተኞች ወደ አውሮጳ እንዳይሻገሩ ለመከላከል የተፈራረሙት ውል  ግቡን መምታቱን ውጤትም ማስገኘቱን የአውሮጳ ህብረት ይናገራል። ህብረቱ እንደሚለው ባለፈው አንድ ዓመት ከቱርክ ወደ ግሪክ ከዚያም በባልካን ሀገራት አቋራርጠው ወደ አውሮጳ የሚገቡ ስደተኞችን ማስቆም ተችሏል ።  የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ቃል አቀባይ አሌክሳንደር ቪንተርሽታይን ባለፈው ሳምንት አርብ ውሉን በገመገሙበት መግለጫቸው ከስምምነቱ በኋላ እንዳለፈው ዓመት አንድ ሚሊዮን ሰዎች በአደገኛው ጉዞ ወደ አውሮፓ ለመግባት አልሞከሩም ፤ ገንዘባቸውም የሰው አሻጋሪ ደላሎች ኪስ አልገባም ብለዋል ። የህብረቱ ኮሚሽን ስታትስቲካዊ  ዘገባ እንደሚያመለክተው ከአንድ ዓመት ወዲህ ግሪክ የገቡት ስደተኞች ቁጥር 27,711 ነው ።ወደ ግሪክ ለመሻገር ሲሞክሩ የሞቱት ቁጥር ደግሞ 80 ነው ። ከውሉ በፊት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ቁጥራቸው አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ስደተኞች ናቸው አውሮጳ የገቡት ።የባህር ሲሳይ የሆኑት ቁጥር ደግሞ 1145 ነበር ። ቃል አቀባዩ ውሉ በጉዞ ላይ የሚሞቱ ሰዎችን ህይወት ማትረፍ ማስቻሉንም ጠቁመዋል።እርሳቸው የሰዎችን ህይወት ማትረፍ የሚሉት ስደተኞች ቱርክን ለቀው መውጣታቸውን ማስቆሙን እና  እዚያው ቱርክ ውስጥ  በአውሮጳ ህብረት እርዳታ በተሰሩ የስደተኞች መጠለያዎች መቆየታቸውን ነው ። ዶክተር ሊዊጂ ያኪሊ ፍሎሬንስ ኢጣልያ በሚገኘው የስደተኞች ፖሊሲ ጥናት ማዕከል ረዳት ተመራማሪ ናቸው ። ዶክተር ያኪሊ ውሉ የአውሮጳ መንግሥታት የፈለጉትን አሳክቷል ቢባልም የስኬቱ ምክንያት ግን ውሉ ብቻ አይደለም ይላሉ ።
«በርግጥም ውሉ  ከምሥራቅ ሜዲትራንያን ወደ ምዕራባዊ ባልካን ሀገሮች ይካሄድ የነበረውን የሰዎች ስደት አስቁሟል ። አሁን በዚህ የጉዞ መስመር ወደ አውሮጳ የሚሻገሩት በቀደመው ዓመት ይሄዱ ከነበሩት ሰዎች ቁጥር ጋር ሲነፃጸር 4 ወይም 5 በመቶ ያህል የሚሆኑት ብቻ ናቸው ።ሆኖም ውሉ ብቻውን የሰዎችን ፍልሰት አላስቆመም የግሪክ ድንበሮች መዘጋት ጭምር ነው ቁጥሩ እንዲቀንስ ያደረገው ።»   
ውሉ ከተፈረመበት ጊዜ አንስቶ ተቃውሞአቸን በመግለፅ ላይ የሚገኙት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ከስኬቱ ይልቅ አሁንም በውሉ ምክንያት በስደተኞች ላይ የሚደርሱ  የመብት ጥሰቶችን ነው የሚያጎሉት ። ዶክተር ያኪሊም አንድ ዓመት ያለፈው የአውሮጳ ህብረት እና የቱርክ ውል ከአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚገመገም አይደለም ይላሉ። ዓላማውን አሳክቷል ቢባልም ይላሉ ያኪሊ ፍፁም ሊፈታው ያልቻለ ችግር አለ። 
« እንጊዲህ የአውሮፓ ህብረት እና የቱርክ ስምምነት ዓላማ ስደተኞች አውሮጳ እንዳይገቡ መከላከል ከሆነ ተሳክቷል ሆኖም ግቡ ስደተኞቹን መርዳት ፣የድንበር አሻጋሪ ደላሎች ሰለባ እንዳይሆኑ መከላከል እና መደገፍ ቢሆን ኖሮ ውሉ ከፍተኛ ጉዳት ነው ያደረሰው ።ምክንያቱም የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እንደሚሉት እና እኔም እንደማስበው ስደተኞቹ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ነው ያሉት ። ይህ የሚሆነው በግሪክ ብቻ ሳይሆን በቱርክም ጭምር ነው ። ከሰብዓዊነት አንጻር ውሉ ፈጽሞ ያልተሳካ ነው ። አብዛኛዎቹ ተገን ጠያቂዎች ከቱርክ ወደ ግሪክ መሄድ አልቻሉም ። በቱርክም ሆነ በግሪክ የሚኖሩበት ሁኔታ እጅግ አስከፊ ነው ። ስለዚህ ሰብዓዊ ጎኑን ስናየው ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ። »
ህጻናት አድን የተባለው የብሪታንያ ግብረ ሰናይ ድርጅት በቅርቡ ያወጣው ዘገባ ለዚህ እንደ አብነት ሊወሰድ ይችላል ። በድርጅቱ ዘገባ እንደተጠቀሰው ከግሪክ ደሴቶች መውጣት ያልቻሉ ህጻናት ስደተኞች የኑሮ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው ። ከ5 ሺህ በላይ የሚሆኑት እነዚህ ስደተኞች ማመልከቻቸው ታይቶ መልስ እስኪያገኙ ድረስ ከደሴቶቹ መውጣት አይፈቀድላቸውም ። ይህም እንደ ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ዘገባ ወላጅ አልባ የሆኑትን የአብዛኛዎቹ ህጻናት ስነ ልቦና እየጎዳ ነው ። በመጠለያ ውስጥ ብቻቸውን መቆየታቸው ለደህንነት ስጋት ካጋለጣቸው ህጻናት አንዳንዶቹ ህይወታቸውን እስከ ማጥፋት ደርሰዋል ። በውሉ መሠረት የተገን ጥያቄአቸው ተቀባይነት ያላገኘ አመልካቾች ከግሪክ ወደ ቱርክ የመባረር እጣም ሊገጥማቸው ይችላል ። የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ቃል አቀባይ ቪንተርሽታይን እንደሚሉት ቱርክ ውስጥ ሊካሄዱ የታቀዱ የ39 ፕሮጀክቶች ስምምነቶች አልቀዋል ። ከመካከላቸው ለግማሽ ሚሊዮን የሶሪያ ስደተኞች የታሰበው ትምህርት ትምህርት ቤቶች የተካተቱባቸው ፕሮጀክቶች ይገኝበታል  ። ይሁን እና ባለፉት ሳምንታት የቱርክ ፖለቲከኞች በአንዳንድ የአውሮጳ ከተሞች ለቱርክ ህገ መንግሥት ማሻሻያ ህዝበ ውሳኔ ፣ሊያካሂዱ ያቀዷቸው የህዝብ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ዘመቻዎች መከልከላቸው በህብረቱ እና በቱርክ የስደተኞች ውል ላይ ጥላ አጥልቷል ። በእርምጃው በእጅጉ የተበሳጩት የቱርክ ፕሬዝዳንት ጠይብ ሬቼፕ ኤርዶሀን ዘመቻውን የከለከሉትን የጀርመን እና የኔዘርላንድስን  መንግሥታት እና መሪዎች ናዚ እና ፋሺሽት እያሉ ከመዝለፋቸው በተጨማሪ አንድ ዓመት የሞላውን ውል እንደሚያፈርሱም እየዛቱ ነው ። ዛቻው የውሉ እጣ ፈንታ አሳሳቢ አድርጎታል ። ዶክተር ያኪሊ ግን ዛቻው ተግባራዊ ይሆናል ብለው አያምኑም። 
«የኤርዶሀን ዛቻ ባዶ ዛቻ ሊሆን ይችላል ። ምክንያቱም ቱርክ ድንበሯን ከከፈተች አዲስ የስደተኞች ማዕበል ወደ አውሮፓ መግባቱ አይቀርም ። በነገራችን ላይ ውሉ ዓላማውን ሊያሳካ የቻለው ምዕራባዊ ባልካን ውስጥ ያሉት በርካታ ሀገራት ድንበራቸው ለመዝጋት ውሳኔ ላይ በመድረሳቸው ጭምር ነው ። በዚህ ረገድ መቄዶንያ ድንበሯን መዝጋቷ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል ። በርካታ ስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች ቱርክ እና ግሪክን የሚያገናኘውን ጠባብ የውሀ ክልል ማቋረጥ አይችሉም ። ። ምክንያቱም ግሪክ ከሄዱ ከዚያ ማለፍ አይችሉም ። እዚያው ነው የሚቀሩት ። ስለዚህ የኤርዶጋን  ዛቻ ባዶ ዛቻ ብቻ ነው ። በዛም ሆነ በዚህ ስደተኞች መንቀሳቀስ አይችሉም ። ግሪክም ቢሄዱ የተሻለ ነገር እንደማያገኙ ያውቃሉ ። »
ዶክተር ያኪሊ የምዕራብ ባልካን  መስመር መዘጋት እና የቱርክ እና የአውሮጳ ህብረት ውል የህገ ወጥ አሻጋሪዎች ቁጥር እንዲያድግና ህገ ወጥ ስደት እንዲባባስ ማድረጉን የአውሮጳ ድንበር ጠባቂ ድርጅት  ፍሮንቴክስ ዘገባ ጠቅሰው ተናግረዋል  ። በርሳቸው አስተያየት ብዙ ስደተኞች ህገ ወጥ የሚባለውን ስደት የሚመርጡት ህጋዊው መንገድ ስለተዘጋባቸው ነው ። በዮርዳኖስ ሊባኖስ እና በግሪክ ጥናቶችን ያካሄዱት ዶክተር ያኪሊ እንደሚሉት ስደተኞች ወደ ሌላ ሦስተኛ አገር እንዲዛወሩ ቢያመለክቱም በአመዛኙ አይሳካላቸውም ።በዚህ የተነሳም ህገ ወጥ የሚባለውን አማራጭ ይሞክራሉ ። በርሳቸው አስተያየት ድንበር መዝጋት የችግሩ መፍትሄ አይደለም ። ተገን ፈላጊዎች ወደ አውሮጳ እንይገቡ ይሄ ሁሉ ገደብ መደረጉም ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶችን ይጋፋል ።
«ግቡ ሰዎቹን አለማስገባት ነው ። ሊሰራ ይችል ይሆናል ።ግን ሰዎች እንዳይገቡ በመከልከል ለስደተኞች እና ለተገን ጠያቂዎች ከለላ እንዲሰጥ የሚጠይቀውን በጄኔቫውን ስምምነት የተቀመጠውን ሃላፊነታችንን አልተወጣንም ። የቀውሱን ሰብዓዊ ጎን ሙሉ በሙሉ ጆሮ ዳባ ልበስ እያልን ነው ። ከዚህ ሌላ ድንበር መዝጋት የህገ ወጥ አሻጋሪዎችን እንቅስቃሴ አልገታም ። እንዲያውም እንዲብስ ነው ያደረገው ።»
ዶክተር አኪሊ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄዎች ከሚሏቸው አንዱ የሰፈራ መርሃ ግብር ነው  ።ሰብዓዊ መተላለፊያ መፍቀድም ሌላው አማራጭ ነው ። 
«  ከእርምጃዎቹ አንዱ ህጋዊ የሰፈራ መርሃ ግብሮችን በማጠናከር ሰዎች በህጋዊ መንገድ ወደ አውሮፓ የሚገቡበትን መንገድ ማመቻቸት ነው ። የስደተኞችን ደህንነት ለማስጠበቅ ወንጀለኞች እጅ እንዳይወድቁ ለመከላከል ደግሞ ሰብዓዊ መተላለፊያዎችን መፍቀድ ነው ። የድንበር ጥበቃ መደረግ አለበት ። ግን የድንበር ቁጥጥርን ማጥበቅ ብቻ መፍትሄ አይሆንም ። አብዛኛዎቹ የኤኮኖሚ ስደተኞች ሳይሆኑ ተገን ፈላጊዎች ናቸው ። በኔ እምነት ተገን ፈላጊዎች የሚሰፍሩበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት ።» 
የሰብዓዊ መብት እና የግብረ ሰናይ ድርጅቶችም ጥያቄ ይሄው ነው ። የቱርክ እና የአውሮጳ ህብረትን ውል  አጥብቀው የሚቃወሙት እነዚህ ወገኖች ስደተኞች ግሪክ እና ቱርክ  የሚደርስባቸው ስቃይ መፍትሄ እንዲያገኝ ጥሪአቸውን ማቅረብ ቀጥለዋል ። ዶክተር አኪል ግን ጥሪው በአጭር ጊዜ ውስጥ መልስ ማግኘቱን ይጠራጠራሉ ። 
« ጨለምተኛ ልሆን እችላለሁ ። በቅርብ ጊዜ ውስጥ መፍትሄ ይገኛል የሚል እምነት የለኝም ። የአሁኑ ቀውስ ሰብዓዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ቀውስ ነው ።የፖለቲካ ፓርቲዎች በመራጮቻቸው ታግተዋል ። በአሁኑ ጊዜ ማንም ድንበር ይከፈት፣ ህጋዊ ስደት ይፈቀድ ለማለት አይደፍርም ። በመሠረቱ አሁን የምንነጋገረው አውሮጳ ለመግባት ስለሚሞክሩ ጥቂት ቁጥር ስላላቸው ስደተኞች ነው ። ደካማ የሚባሉት እንደ ሊባኖስ ያሉ ሀገራት መላው አውሮጳ ካስጠለለው እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛ ነው ያላቸው ።»  
ኂሩት መለሰ

EU Türkei Migration Flüchtlingsabkommen
ምስል DW/D. Cupolo
Türkei Tayyip Erdogan in Istanbul
ምስል Reuters/M. Sezer
Griechenland Flüchtlinge Fähre Nacht
ምስል Reuters/M. Karagiannis
Griechenland Flüchtlingslager in Moria auf Lesbos
ምስል picture alliance/dpa/T. Stavrakis/AP

አርያም ተክሌ