1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአንጎላ ምርጫ፣ የአፍሪቃ ሴቶች አበሳ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 21 2014

ሁለቱም አንጎላን ከፖርቱጋል ቅኝ አገዛዝ ነፃ ለማዉጣት ይዋጉ የነበሩ ግን ተቃራኒ ርዕዮተ ዓለም የሚያቀነቅኑ ነበሩ።በ1975 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) አንጎላ ከፖርቱጋል ቅኝ አገዛዝ ነፃ ስትወጣ፣ ከሁለቱ አማፂያን ጠንከር፣ፈርጠም ያለዉ ማርክሲስቱ፣ ሕዝባዊ ንቅናቄ ለአንጎላ ነፃነት (MPLA) የሉዋንዳን ቤተ-መንግስት ተቆጣጠረ

https://p.dw.com/p/4G7OR
Wahlen in Angola
ምስል AP Photo/picture alliance

ትኩረት በአፍሪቃ፦ የአንጎላ ምርጫ ዉጤት፣ የአፍሪቃ ሴቶች መከራ

                                                                      የአንጎላ ምርጫና ወጣቱ

አንጎላ ዉስጥ ባለፈዉ ሮብ በተደረገዉ ምርጫ በስልጣን ላይ ያለዉ ሕዝባዊ ንቅናቄ ለአንጎላ ነፃነት (በፖርቱጋልኛ ምሕፃረ ቃሉ MPLA) እየመራ ነዉ።ይሁንና በነዳጅ ዘይት የበለፀገችዉ አፍሪቃዊት ሐገር ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ የሚገዛዉ ፓርቲ ያገኘዉ ድምፅ ከዚሕ ቀደም በነበሩት ምርጫዎች ካገኘዉ ሁሉ እጅግ ዝቅተኛ ነዉ።ዋነኛዉ ተቃዋሚ የአንጎላ ሙሉ ነፃነት ብሔራዊ አንድነት (UNITA) ባንፃሩ ከፍተኛ ድጋፍ አግኝቷል።የUNITA መሪዎች አሸንፈናል እስከማለት ደርሰዋልም።ነጋሽ መሐመድ የምርጫዉን ዉጤትና የአንጎላ ሕዝብን በጣሙን የወጣቱን ስሜት ባጭሩ ይቃኛልናል።

ሁለቱም አንጎላን ከፖርቱጋል ቅኝ አገዛዝ ነፃ ለማዉጣት ይዋጉ የነበሩ ግን ተቃራኒ ርዕዮተ ዓለም የሚያቀነቅኑ፣ በሶሻሊስት-ካፒታሊስቶች ኃያላን የሚደገፉ አማፂያን ነበሩ። በ1975 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) አንጎላ ከፖርቱጋል ቅኝ አገዛዝ ነፃ ስትወጣ፣ ከሁለቱ አማፂያን ጠንከር፣ፈርጠም ያለዉ ማርክሲስቱ፣ ሕዝባዊ ንቅናቄ ለአንጎላ ነፃነት (MPLA) የሉዋንዳን ቤተ-መንግስት ተቆጣጠረ።
በምዕራባዉያን የሚደገፈዉ ብሔራዊ አንድነት ለአንጎላ ሙሉ ነፃነት (UNITA) ጫካ ቀረ።የነፃነት ተፋላሚዎቹ ከነፃነት በኋላ አንዳቸዉ ሌላቸዉን ለማጥፋት ይፋለሙ ያዙ።
እስከ 1979 ድረስ አጉስቲኖ ኔቶ፣ ከ1979 በኋላ  ኤድዋርዶ ዶ ሻንቶስ የመሩት MPLA በበሶቭየት ሕብረት ጦር መሳሪያ፣ በኩባ ወታደሮችና በመላዉ ሶሻሊስት ዓለም የቁስና የሞራል ድጋፍ፣ UNITA ባንፃሩ በደቡብ አፍሪቃ የአፓርታይድ ስርዓት ስልጠና፣ የዉጊያ ስልት፣ በዩናይትድ ስቴትስና በአዉሮጳ ተባባሪዎችዋ ገንዘብና ጦር መሳሪያ እየተረዱ  ያገጠሙት ጦርነት መቶ ሺዎችን አርግፏል።ሚሊዮኖችን አፈናቅሏል።የነዳጅ ሐብታሚቱን ሐገር ሐብት ንብረት አዉድሟል።

Angola | Präsident Joao Lourenco MPLA
ምስል Stringer/REUTERS

የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ሮናልድ ሬገን ባንድ ወቅት ለታማኛቸዉ ክብር የUNITAን መሪ ዮናስ ሳቪምቢን «የዛንቤዚዉ አንበሳ» እያሉ አንቆለጳጵሰዋቸዉም ነበር።የካቲት 2002 ግን የዛምቤዚዉ አንበሳ በአንጎላ መንግስት ጦር ተገደሉ።የሳቪምቢ መገደል ለአንጎላ ሕዝብ የሰላም ጭላንጭል ፈንጣቂ፣ ለደቡባዊ አፍሪቃዊቱ ሐገር የአዲስ ስርዓት ጅምር ሆነ።
UNITA አለቃዉ ከተገደሉ በኋላ ሰላማዊዉን ትግል ሲቀየጥ፣ በ1992 ከተለወጠዉ ዓለም ጋር መለወጧን ለማሳየት የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ያወጀችዉ አንጎላ በየአምስት ዓመቱ አንዴ ጠንካራ የፖለቲካ ማሕበራት የሚፎካከሩበት ምርጫ ማስተናገድ ጀመረች።በየምርጫዉ የሚሻንፈዉ ግን ከ1975 ጀምሮ ስልጣን የያዘዉ MPLA ነዉ።

                                          የገዢዉ ፓርቲ ቃል

ፓርቲዉ የዛሬ አምስት ዓመት በተደረገዉ ምርጫ ከአጠቃላዩ ድምፅ 61 ከመቶዉን አሸንፎ ነበር።በያኔዉ ምርጫ የፓርቲዉ መሪዎች የስራ አጡን ቁጥር ለመቀነስ ቃል ገብተዉ ነዳጅ አምራቺቱን ሐገር እንደ ካሊፎርኒያ እናደርጋታለን ብለዉ ነበር።እሱ የመሪዎቹን ቃል አልረሳም።
                                   
«ለ500 ሺሕ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንሰጣለን በማለት የገቡት ቃል ዉሸት ነዉ።ምንም ያገኘነዉ ነገር የለም።ቃል የገቡልን ካሊፎርኒያ የታለች?ካሊፎርኒያ እዚሕ የለችም።ወጣቱ ለዉጥ ይሻል።ዝባንዝኬ ማዉራቱ ይብቃ፣ዉሸት በቃ።»
UNITAም ከሁለት አነስተኛ ፓርቲዎች ጋር ግንባር ፈጥሮ ለዘንድሮዉ ምርጫ በቅጡ ተዘጋጅቷል።የወጣቱን ልብ የሚያማልሉ፣ ደሐዉን የሚስቡ፣የMPLA ሹማምንታትን ሙስና የሚያጋልጡ ርዕሶችን እያነሳ መራጩን በመቀስቀሱ በምርጫዉ ሙሉ በሙሉ ባያሸንፍ እንኳን እስካሁን ከነበረዉ የተሻለ ድምፅ እንደሚያገኝ ተገምቶ ነበር።ግምቱ በርግጥ የያዘ መስሏል።
የአስመራጭ ኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ሉካስ ቁለንዶ ባለፈዉ ሐሙስ ማምሻ እንዳስታወቁት እስከዚያ ጊዜ ድረስ ከተቆጠረዉ ድምፅ MPLA 52.08 ከመቶ፣ UNITA  42.98 ከመቶ ማግኘታቸዉን አዉጀዉ ነበር።
                                        
«ከተቆጠረዉ 86.41 ከመቶ ድምፅ ዉስጥ MPLA 52.08 ከመቶ፣ UNITA ደግሞ 42.98 ከመቶዉን ድምፅ ማግኘታቸዉን መናገር እንችላለን።»
አብዛኛዉ የአንጎላ ወጣት በተለይ ከዝቅተኛ መደብ የሚወለደዉ ለዉጥ ይፈልጋል።የሮቡ ምርጫም 46 ዘመን ያስቆጠረዉ የMPLA አገዛዝ የሚያበቃበት እንዲሆን ብዙ ተጣጥሯል።UNITAም በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መሪዉን የወደፊቱ ፕሬዝደንት እያለ ሲያስተዋዉቅ ነበር።በአንጎላ ሕግ መሰረት አሸናፊዉ ፓርቲ የሐገሪቱን መሪ ይሰይማል።
ይሁንና ትናንት ማምሻ ድረስ ከተቆጠረዉ 97 ከመቶ ድምፅ ገዢዉ ፓርቲ MPLA 51.07 ድምፅ በማግኘት በቀን 1.16 ሚሊዮን በርሚል ነዳጅ የሚዛቅባትን ሐገር የመሪነት ሥልጣን እንደጨበጠ ነዉ።UNITA ከ44 ከመቶ በላይ ድምፅ አግኝቷል።

Angola Adalberto Costa Junior
ምስል Lee Bogota/REUTERS

          
                                                             የአፍሪቃ ሴቶች አበሳ
አፍሪቃዉያን ሴቶች እቤት ዉስጥ የሚደርስባቸዉ በደል ከብዙዉ ዓለም አቻዎቻቸዉ በጅጉ የከፋ እንደሆነ ጥናቶች መስክረዋል።የሴቶች መብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ባሎች ወይም አፍሪቂ ወንዶች በሴቶች ላይ የሚያደርሱትን ድብደባ፣ስድብና ዘለፋ እንዳይናገሩ የማሕበረሰቡ ባሕልና አስተዳደብ ያግዳቸዋል።አንዳድ ሐገራት ደግሞ መንግስታትም ጭምር በሴቶች ላይ የሚደርሰዉን ጥቃት የሚያበረታት ደንብ እስከ ማዉጣት ደርሰዋል።የዚሕንም ዝርዝር ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

Afrika | Sudanesische Frau - Opfer von sexueller Gewalt
ምስል Ben Curtis/AP/picture alliance


ጥቂቶች፣ ምናልባት ዘመን የራቃቸዉ አስተባሰብ ያረጀባቸዉ፣ እጅግ በጣም ጥቂቶች ወንድ አፍቃሪ ሴት ተፈቃሪዉን መምታቱን «የፍቅር ነዉ» ባዮች አይጥፉም።ወዳጅ ዉዱን መደብደብ በርግጥ እንዴት «ፍቅር» ሊሆን ይችላል?ጥቃት እንጂ-ያምናሉ ብዙዎች።የብዙዎቹ እምነት፣የአዋቂዎች ምክር፣ የዘመኑ አስተሳሰብም ለዘመናዊቱ አፍሪቃ አሁንም ሩቅ መሆኑ ነዉ-እንቆቅልሹ።
የካተሪን መጥፎ ገጠመኝ ለአፍሪቃ ሴቶች ጥሩ አብነት ነዉ።ማላዊቷ ወጣት ፍቅረኛዋን ሳታስፈቅድ ፀጉሯን ተቆረጠች።አጅሬዉ ይነርታት ገባ።«እንዲያዉ በትንሹም በትልቁም ስንቴ እንደደበደበኝ አላዉቅ» ትላለች ካተሪን።«ደግሞ በደበደበኝ ማግስት ይመጣና ይቅርታ ይለኛል።»አለች-ምርር፣ግርም፣ንድድም እያላት።በደበደባት ቁጥር ልትለየዉ ትወስንና ይቅርታ ሲጠይቃት ዉሳኔዋን ታፈርሳለች።የአፍቃሪ ልብ።የኋላ ኋላ ግን ጨከነች።ለትዳር የታሰበዉ ግንኙነት ፈረሰ።ተወችዉ።

                                                         የጓዳ ዉስጥ ጥቃት

የፆታ ጥቃት። ባል ወይ ፍቅረኛ ሚስት ወይም ተፈቃሪዉን ብዙ ጊዜ በር ዘግቶ እቤት ዉስጥ የሚያደርሰዉ ጉዳት ነዉ።ዓይነቱ አዋቂዎች እንደሚሉት ብዙ ነዉ።በሶስት ይጠቃለላል።የአካል ድብደባ፣ ያለፍላጎት ወሲብ፣ልብ  ሰባሪ ስድብ ወይም ዘለፋ---ይሉታል።

44 ከመቶ አፍሪቃዉያን ሴቶች የዚሕ ጥቃት ሰለቦች ናቸዉ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለዉ በዓለም የሚፈፀመዉ ጥቃት በአማካይ በ30 ከመቶ ሴቶች ላይ ነዉ።የአፍሪቃዉያኑ የከፋ ነዉ።ይበልጥ የሚከፋዉ ደግሞ አፍሪቃዉያን ሴቶች በየሳሎን፣ መኝታ ቤታቸዉ የሚፈፀምባቸዉን ጥቃት ባደባባይ እንዳይናገሩ በልምድ፣ ባሕል፣አስተሳሰብ አንዳዴም በእምነት መሸበባቸዉ ነዉ-ይላሉ ቹዝ ዩርሰልፍ-የተሰኘዉ የሴቶች መብት ተሟጋች ድርጅት ኃላፊ ጁዲኬሌ ኢራኮዚ
                                           
«ሴቶች እንደሚበደሉ እናዉቃለን።ግን ማንም ስለበደሉ መናገር አይፈልግም።በደሉ የሴትነት ኑሮ አካል ተደርጎ ይታያል።የሚደርሰዉ አካላዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊ፣እና መንፈሳዊ ጥቃት ሴት ከመሆን ጋር የተያያዘ ነዉ (ተብሎ ይታሰባል።)በአብዛኛዉ የአፍሪቃ ማሕበረሰብና ባሕል እንዲሕ ዓይነቱን በደል ማጋለጥ ነዉር ነዉ።ሴትነት ዝምታ ነዉ፤ ትንሽ መናገር፣ ትንሽ ማድረግ፣ትንሽ መንቀሳቀስ ነዉ።የሴትነት ወጉ ከንግግርም፣ ከድርጊትም ቆጠብ ማለት ነዉ።»
ስሜትን አመቅ፣ ቆጠብ፣ጠንቀቅ፣ፀዳ፣ አፈር፣አንገትን ደግሞ ደፋ----ለብዙዉ ዓለም የሴትነት መግነጢሳዊ ዉበት፣ኩራት፣ ክብር መሰረት ተደርጎ ይታያል።የዉበት፣ኩራት ክብሩ መሰረት-የሆኑትን አካልና መንፈስ በዱላ-ዘለፋ የመስበሩ ጥቃት ነዉ ግራዉ።ደግሞ ለወንዱ ልጅም፣እሕትም፣እናትም የምትሆነዉ ሴት ሚስት ወይም ፍቅረኛ ስትሆን ጥቃትን እንድትቀበል ማሕበረሰቡ መፍረዱ ነዉ እንቆቅልሹ።
ብሩንዲያዊቱ የመብት ተሟጋች ኢራኮዚ እንደሚሉት በብዙ አፍሪቃዉያን ዘንድ «በደልን መናገር አሳፋሪም ነዉ።» «ነዉር ነዉ።ሴቲቱ የደረሰባትን በደል እንዴት ደፍራ ትናገራለች።በደሉን መቋቋም እንዴት አቃተሽ? የጓዳ ሚስጥርሽን እንዴት ለጎረቤት ወይም ለእግዳ ትናገሪያለሽ? ርዳታ ፈልገሽ ብትጠይቂ እንኳ ሊረዱሽ የሚገባቸዉ ሰዎች መልሰዉ አንቺኑ ይወቅሳሉ።ሚስጥርሽን ለሌላ ለምን ትናገሪያለሽ እያሉ።»
ዩጋንዳዊቱ የሴቶች መብት ተሟጋች ሳፊና ቪራኒ «ተበዳይ ላይ መፍረድ» ትለዋለች።በትዉልድ ሐገሯ ዩጋንዳ  በሴቶች ላይ ለሚደርሰዉ በደል ተጠያቂዉ  ግለሰቡ፣ ባሕሉ ፣ማሕበረሰቡ ወይም አስተሳሰቡ ብቻ አይደለም ባይ ናት።መንግስትም ጭምር እንጂ።ቪራኒ የዩጋንዳ መንግስት እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር በ2014 ያወጣዉን የአለባበስ ደንብን አብነት ትጠቅሳለች።
«መንግስት ራሱ ተበዳዮችን የሚከሱና የሚወቅሱ ተቋማትን ይመሰርታል።ሕግም ያወጣል።እስኪ የ2014ቱን የሚኒስከርት ደንብ እንደምሳሌ እንጥቀስ።ሴቶች አካልን የሚጋልጥ ወይም ወሲብ ቀስቃሽ ልብስ መልበስ የለባቸዉም ብለዉ ሚኒስከርትን የመሰሉ ልብሶችን የሚያግድ ሕግ ለማፅደቅ ሞክረዉ ነበር።የሰጡት ምክንያት ሴቶችን እነዚሕ ልብሶች በመልበሳቸዉ የሚደፈሩ ሴቶችን ቁጥር አንሮታል የሚል ነበር።ብዙ ወንዶች ሴቶችን የሚደፍሩት በሴቶቹ አለባበስ እየተነሳሱ ነዉ ባዮች ነበሩ።»

Uruguay Gender Marsch gegen Gewalt
ምስል Matilde Campodonico/AP/picture alliance
BG Internationaler Frauentag 2022
ምስል Monicah Mwangi/REUTERS

                                                                         መፍትሔና ተስፋ

አፍሪቃ ዉስጥ ከባሕል እስከ ፖለቲካ፣ ከግለሰብ እስከ ማሕበረሰብ ያበሩበት የሚመስለዉን በሴቶች ላይ የሚደርስ በደልን ለማቃለል አብነቱ፣ የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት የራሳቸዉ የተበዳዮቹ ትግል ነዉ።የሚደርስባቸዉን በደል ማጋለጥ፣ፍትሕ መጠየቅ፣ አንቃፊ አስተሰሰብ፣ደንብና ሕጎችን ማስለወጥ።ዩጋንዳዊቷ ወጣት የሴቶች መብት ተሟጋች «የተስፋ ጭላንጭል እየታየ ነዉ» ትላለች።ብዙ ወጣት አፍሪቃዉያን የሚደርስባቸዉን በደል  እያጋላጡ፣የመብት ተሟጋች ማሕበራትን እየተቀየጡ፣ አዳዲስ ማሕበራትንም እየመሰረቱ ነዉ»-እንደ ቪራኒ።ማላዊቷ ወጣት ካተሪን በየሰበብ አስባቡ ከሚደበድባት ፍቅረኛዋ መለያዩቷን «በጣም ከባድ» ትለዋለች።ግን «ተገቢ ዉሳኔ።» ለሌሎች ምክር ብጤም አላት።«በዳይ ወንድ አሳሳች ነዉ።ዛሬ ደብድቦሽ ነገ ስጦታ ያመጣልሻል። ስጦታዉ ግን አካል ወይም መንፈስሽን አይተካም። ሰዉዬዉን ተዬዉ።»

ነጋሽ መሐመድ