1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአንጋፋው ጋዜጠኛ ጎይቶም ቢሆን አስክሬን ሽኝት ተደርጎለታል

ሰኞ፣ መስከረም 2 2015

በኢትዮጵያ ራድዮና በጀርመን ድምጽ ዶይቸ ቨለ "DW" ከ 30 ዓመታት በላይ በጋዜጠኝነት ሙያ ያገለገለው አንጋፋው ጋዜጠኛ ጎይቶም የአስክሬን ሽኝት እና የፍትሃተ ጸሎት መርሃግብር ቤተሰቦቹ የሙያ አጋሮቹ እንዲሁም ኤርትራውያን እና ኢትዮጵያውያን በተገኙበት ዛሬ ከቀትር በኋላ በጀርመን ማይንታል ከተማ ተከናውኗል::

https://p.dw.com/p/4GkaD
DW Asmera-Korrespondent Goytom Bihon verstorben
ምስል Endalkachew Fekade/DW

የአንጋፋው ጋዜጠኛ ጎይቶም ቢሆን አስክሬን ተሸኘ

የአንጋፋው ጋዜጠኛ ጎይቶም ቢሆን ዜና እረፍት

ለበርካታ ዓመታት በአስመራ የዶይቼ ቨለ ራድዮ የአማርኛ ፕሮግራም ክፍል ዘጋቢ የነበረው ጋዜጠኛ ጎይቶም ቢሆን በሚኖርበት የጀርመን ሆፍሃይም ከተማ በድንገት አርፏል:: በኢትዮጵያ ራድዮና በጀርመን ድምጽ ዶይቸ ቨለ "DW" ከ 30 ዓመታት በላይ በጋዜጠኝነት ሙያ ያገለገለው አንጋፋው ጋዜጠኛ ጎይቶም የአስክሬን ሽኝት እና የፍትሃተ ጸሎት መርሃግብር ቤተሰቦቹ የሙያ አጋሮቹ እንዲሁም ኤርትራውያን እና ኢትዮጵያውያን በተገኙበት ዛሬ ከቀትር በኋላ በጀርመን ማይንታል ከተማ ተከናውኗል:: 

DW Asmera-Korrespondent Goytom Bihon verstorben
ምስል Endalkachew Fekade/DW

እንደ ጎርጎሪዮሳዊው አቆጣጠር ከ 2000 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ከኤርትራ ወደ ጀርመን በማቅናት ፍራንክፈርት አቅራቢያ በምትገኘው የሆፍሃይም ከተማ ኑሮውን መስርቶ የነበረው የቀድሞ የዶይቼ ቨለ ራድዮ የአስመራ ዘጋቢ አንጋፋው ጋዜጠኛ ጎይቶም ቢሆን በድንገት ነበር በቅርቡ በመኖሪያ ቤቱ ማለፉ የተሰማው:: ከወላጅ እናቱ ወይዘሮ ዘውዴ ወልደ ግብሬል እና ከቀድሞ የኮሪያ ሰላም አስከባሪ ዘማች አባቱ ወታደር ቢሆን ገብረ ኢየሰስ ወሎ ደሴ ከተማ የተወለደው ጎይቶም ትምህርቱን በዛው በደሴ ዙሪያ የተከታተለ ሲሆን እንደ ጎርጎሪዮሳዊው አቆጣጠር በግንቦት ወር 1991 ዓ.ም ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተለይታ ነጻ ሃገር ከመሆኗ አስቀድሞ በጅማ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም በአጠቃላይ የመምህርነት ስልጠና ከተመረቀ በኋላ በጅማና በተለያዩ አካባቢዎች በመምህርነት ሙያ አገልግሏል::

DW Asmera-Korrespondent Goytom Bihon verstorben
ምስል Endalkachew Fekade/DW

ለጋዜጠኝነት ሙያ ከፍተኛ ፍቅር ስለነበረውም በቀድሞ የደርግ ወታደራዊ አስተዳደር ዘመን በቀይ ኮከብ ዘመቻ ወቅት በማስታወቂያ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ራድዮ የአስመራ ቅርንጫፍ ጣቢያ ውስጥ በአማርኛ ፕሮግራም ክፍል በጋዜጠኝነት ተቀጥሮ ማገልገል መጀመሩን የሙያ ባልደረቦቹ ይገልጻሉ:: በኋላም በሙያ ብቃቱ በተግባቢነቱና በስራ ትጋቱ በዛው በአስመራ ጣቢያ የአማርኛ ፕሮግራም ክፍል ኃላፊ ሆኖ ተሹሞ ከ 10 ዓመታት በላይ አገልግሏል:: ደርግ መራሹ ሥርዓት ከወደቀ በኋላ ግን የኤርትራ ነጻነት ግንባር የኢትዮጵያ ራዲዮ የአስመራ ቅርንጫፍ ጣቢያን በመዝጋቱ ጎይቶም በዛው በአስመራ በሚኒስትር መስሪያቤቶች እና በተለያዩ ድርጅቶች ተቀጥሮ መስራቱ ይነገራል::

ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም ልክ የዛሬ 33 ዓመት የቀድሞ ወታደራዊ መሪ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ለስራ ጉብኝት ወደ ምሥራቅ ጀርመን በሄዱበት ዕለት በሃገሪቱ ከፍተኛ የጦር ጄነራሎች የተጠነሰሰው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መክሸፉን ከአስመራ ራዲዮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጋዜጠኛ ሙሉብርሃን ሰይፉ ጋር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይፋ ማድረጋቸውና ከ 1998-2000 ዓ.ም በተካሄደው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅትም ከአስመራ ያቀርባቸው የነበሩ ልዩ ልዩ ወቅታዊ ዘገባዎቹ በፈታኝ ወቅት ሙያዊ ብቃቱን ያስመሰከረባቸው ክስተቶች ሲሆኑ ከራዲዮ አድማጮችም ጋር የበለጠ አስተዋውቀውታል::

DW Asmera-Korrespondent Goytom Bihon verstorben
ምስል Endalkachew Fekade/DW

ዛሬ ከቀትር በኋላ ፍራንክፈርት አቅራቢያ በምትገኘው በማይንታል ከተማ ዶይቼ ቨለ ባዘጋጀው የአንጋፋውን ጋዜጠኛ ጎይቶም ቢሆን ዝክር ፍትሃተ ጸሎት እና የአስክሬን ሽኝት የስንብት መርሃግብር ቤተሰቦቹ፣ ወዳጆቹ፣ የሙያ አጋሮቹ፣ ኤርትራውያን እና /የኤርትራ ኮሚኒቲ አባላት እና/ ኢትዮጵያውያን ተካፋይ ሆነዋል:: እህቱ ዓለም ቢሆን ወንድሟ ቤተሰቡን አክባሪ ,ትሁትና ተወዳጅ ሰው እንደነበር ገልጻልናለች:: የዶይቼ ቨለ "DW" የአማርኛ ፕሮግራም ክፍል ምክትል ሃላፊ ነጋሽ መሃመድ ጎይቶም የራዲዮ ጣቢያው የአስመራ ወኪል ሆኖ ባገለገለባቸው ጊዜያት የሙያ ኃላፊነቱን በአግባቡ የተወጣ፣ ስራውን አክባሪ እና ትሁት እንደነበር በመግለጽ ለቤተሰቦቹና ወዳጅ ዘመዶቹ መጽናናትን በመላው የጣቢያው ባልደረቦች ስም ተመኝቷል::

"ጎይቶም ብዙ ጦርነቶችን አይቷል:: ከብዙ ውጣ ውረዶችም ተርፏል የሌሎችንም ሕይወት አትርፏል:: ዛሬ ግን እሱ እራሱ ከድካም አርፏል እናም እየተሰናበትነው ነው:: እንደ ጋዜጠኛ ሙያዊ ብቃቱን ያስመሰከረ ተጫዋችና ትሁት ሰው ነበር ጎይቶም" ብሏል ባልደረባውና አለቃው ነጋሽ መሃመድ:: ሌላው የሙያው ባልደረባ ሂሩት መለስም "ጎይቶም በጋዜጠኝነት ለበርካታ ዓመታት ሙያዊ ልምድን ያካበተ ተጫዋችና ተግባቢ ነበር:: በሕልፈተ ህይወቱ እጅግ በጣም አዝኛለሁ" ብላለች:: በፍራንክፈርት የኤርትራ ኮሚኒቲ አባላትም ዶይቼ ቨለ የጎይቶም ህልፈተ ህይወት ከተሰማበት ዕለት ጀምሮ ለሽኝት መርሃግብሩ አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ በማድረጉ ምስጋናችን የላቀ ነው ብለዋል:: በአስክሬን ሽኝት መርሃግብሩ የተሳተፉ ኤርትራውያን እና ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ወዳጅና አድናቂዎቹም ስለ ጎይቶም የሙያ ብቃት ቅንነትና መልካም ሰብዕና ገልጸዋል::

DW Asmera-Korrespondent Goytom Bihon verstorben
ምስል Endalkachew Fekade/DW

ጋዜጠኛ ጎይቶም የአንድ ሴት ልጅ አባት ነበር:: ሥርዓተ ቀብሩ በሃገሩ ኤርትራ እንደሚፈጸም ከመርሃግብሩ ለመረዳት ችለናል:: ዶይቼ ቨለ በቀድሞው የአማርኛ ፕሮግራም ክፍል ባልደረባ ጎይቶም ቢሆን ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለጸ ለቤተሰቦቹና ለወዳጅ ዘመዶቹ መጽናናትን ይመኛል::

እንዳልካቸው ፈቃደ 

ታምራት ዲንሳ 

ኂሩት መለሰ