1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአንበጣ መንጋ ወቅታዊ ይዞታ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 8 2013

ኢትዮጵያ ውስጥ ከ25 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ እጅግ ተበራክቶ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ አሁን በተወሰኑ አካባቢዎች መጠኑም በጣም ቀንሶ መታየቱ ተሰምቷል። የአንበጣ መንጋውን ለማጥፋትና ለመከላከል የተደረገው ርብርብ አዎንታዊ ውጤት አስገኝቷል ተሏል። በምሥራቅ አፍሪቃ አሁንም የአንበጣ ሥጋት መኖሩን የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ጠቁሟል።

https://p.dw.com/p/3lRZ0
Äthiopien | Heuschrecken in der Hareri Region
ምስል Mesay Tekelu/DW

የአንበጣ መንጋ ወቅታዊ ይዞታ

የአንበጣ መንጋ ከ2011 ዓ,ም ሰኔ ጀምሮ በተደጋጋሚ በርከት ብሎ ሲከሰትና የተለያዩ አካባቢዎችን ሲያዳርስ መክረሙ ይታወሳል። በተለይ ካለፈው ነሐሴ ወር አንስቶ በትግራይ፤ በአፋር፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎችና በድሬደዋ ከተማ መስተዳደር በብዛት የተከሰተው የአንበጣ መንጋ የተዘራው ሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል የሚል ስጋት አሳድሯል። ይህ ከ25 ዓመታት ወዲህ እንደታየ የሚነገረው የአንበጣ መንጋ በሰብል ያደረሰው የጉዳት መጠን ገና ተጠንቶ ባይቀርብም ለማጥፋትም ሆነ ለመከላከል የተደረገው ጥረት ግን አዎንታዊ ውጤት አስገኝቷል ይላሉ  በግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ በላይነህ ንጉሤ።

የአንበጣው መንጋ ተስፋቶ በነበረባቸው አካባቢዎች በማሳ ላይ ያደረሰውን ጉዳት የሚያጠና ከተለያዩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች የተውጣጣ የባለሙያዎች ቡድን ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ወደመስክ ወጥቶ ጥናቱን ለማካሄድ መዘጋቱንም ነው የተናገሩት። በሀገረማያ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑትና የነፍሳት ባህሪ ተመራማሪው ዶክተር ሙሉቀን ጎፍትሹም እሳቸው በቅርበት በተመለከቱት አካባቢ አንበጣው ጠፍቷል ነው የሚሉት።

የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት በእንግሊዝኛ ምህጻሩ FAO ባለፈው ሳምንት ባወጣው ጥቆማ በአፋር መጠነኛ፤ በሶማሌ ክልል ግን በጅግጅጋ እና ደግሀቡር ላይ በርከት ያለ ያላደገ የአንበጣ መንጋ፣ በኦጋዴ በዋርዴት አካባቢ ደግሞ ያደረገ እንዲሁም ቀብሪ ደሀር አቅራቢያ ቢያንስ አንድ መንጋ የሚሆነው እንቁላል ሳይጥል እንዳልቀረ አሳስቧል። እንዲህ ያለውን መረጃ FAO ከእነሱ እንደሚያገኝ ያመለከቱት በግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አፋርን በተመለከተ ያለው እውነታ ከተባለው ይለያል ነው የሚሉት።

እናም በቦታው አስፈላጊው ነገር በበቂ  መልኩ በመኖሩን ባለሙያዎችም በመሠማራታቸው ሁኔታው ተገቢው ቁጥጥር በአግባቡ እየተከናወነ ነውና ከቁጥጥር ውጭ አይሆንምም ባይ ናቸው አቶ በላይነህ።

FAO, Food and Agriculture Organisation of the United Nations, Logo
ምስል AP Graphics

ፀረ ሰብል የሆኑት አንበጣ መንጋ እና ግሪሳ ወፍ ዘንድሮ ለኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ዋነኛ ስጋት መሆናቸው ነው የሚነገረው።  በምሥራቃዊ የአማራ ክልል ዞኖች የነበረው የአንበጣ መንጋ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የአካባቢዎቹ አርሶ አደሮችና የአማራ ክልል ግብርና ልማት ቢሮ ገልጿል።  አሁን በተለይ በክልሉ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርና ሰሜን ሸዋ ዞን በማሽላ ሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያስረዳል። እናም አርሶ አደሮች በባህላዊ መንገድ እየተከላከሉ መሆናቸውን ተናግረዋል። እንደአንበጣው ሁሉ ግሪሳ ወፉንም በኬሚካል ማስወገድ እንደሚቻል የገለፁልን አቶ በላይነህ ርጭቱን በተመለከተ ያለውን ልዩነት አስረድተዋል። እሳቸው እንደሚሉትም የኬሚካል መርጫ አውሮፕላኑን የሚያበርሩት ባለሙያዎችም ልምዳቸው ለየቅል ነው።

የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት በምሥራቅ አፍሪቃ ባሉት ሃገራት እንደ ሶማሊያ፤ በኬንያ፣ በኤርትራ እና በሱዳን ገና ያላደገ አንበጣ መንጋ ፈጥሮ በቅርቡ ለመንቀሳቀስ መዘጋጀቱን እየተከታተለ እንደሚገኝ ጠቁሟል። የተጠናከረ መንግሥት የማይታይባቸው እንደየመን ያሉት ደግሞ ዋናው የዚህ ጸረ ሰብል መፈልፈያነታቸው መቀጠሉን መረጃዎች ያሳያሉ። ለሰጡን ማብራሪያ  በግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ በላይነህ ንጉሤን እናመሰግናለን።

ሸዋዬ ለገሠ