1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአቶ ዳውድ ኢብሳ ከቤት ውስጥ እስር መለቀቅ

ሐሙስ፣ መጋቢት 8 2014

በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ለአንድ ዓመት ያህል ታስረው የቆዩት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ መለቀቃቸው ተነገረ። አቶ ዳውድ ለአንድ ዓመት የቁም እስረኛ ኾነው ከቆዩበት ቅጥር ግቢ ካለፈው ሳምንት ረቡዕ ጀምሮ ለመውጣት መቻላቸውን አንድ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባል ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

https://p.dw.com/p/48d1G
 Logo Oromo Liberation Front

ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ ከቤት ለመውጣት መቻላቸው ተገልጧል

በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ለአንድ ዓመት ያህል ታስረው የቆዩት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ መለቀቃቸው ተነገረ። አቶ ዳውድ ለአንድ ዓመት የቁም እስረኛ ኾነው ከቆዩበት ቅጥር ግቢ ካለፈው ሳምንት ረቡዕ ጀምሮ ለመውጣት መቻላቸውን አንድ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባል ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የካቲት 25 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ባወጣው መረጃ እንዳመለከተው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ከመጋቢት 24 ቀን፣ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በመኖሪያ ጊቢያቸው በተመደቡ የታጠቁ የፀጥታ አካላት እንዳይንቀሳቀሱ ተደርገው በቤት ውስጥ እስር ላይ ቆይተዋል ብሎ ነበር። ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ቅሬታ ለማጣራት በቅርቡ ባቋቋመው መርማሪ ቡድን ይህንን በማጣራቱ ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እና ለብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት በጻፈው ደብዳቤ የቤት ውስጥ እስራቱ በአፋጣኝ እንዲቆምና የተመደበው ጥበቃ ተነስቶ የሊቀመንበሩ የመንቀሳቀስ መብት እንዲከበር መጠየቁንም ማመልከቱ ይታወሳል። 

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከፍተኛ ከፍተኛ አመራር አባል እና የሊቀመንበሩ አቶ ዳውድ ኢብሳ ከፍተኛ አማካሪ ዶ/ር ሽጉጥ ገለታ ለዶይቼ ቬለ እንዳረጋገጡትም አቶ ዳውድ ዓመቱን በሙሉ ከዘለቀው የቤት ውስጥ እስራት በኋላ አሁን መንቀሳቀስ ጀምረዋል ብለዋል። «የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ከአንድ ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ በመኖሪያ ቤታቸው ታግተው ሰው ሄዶ ሊጠይቃቸው እንዲሁም እሳቸውም ወጥተው ሰው ማግኘት በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ነበሩ፡፡ ከረጂም ጊዜ በኋላ ይህንኑን የተረዳው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማጣራት አድርጎ ነገሩ ትክክል አይደለም በማለት መንግስት እንዲፈታቸው መጠየቁም የሚታወስ ነው፡፡ ይህንኑን ሂደት ተከትሎ ይመስላል ከቀናት በፊት ሊቀመንበሩ የካቲት 30 ቀን 2014 ለመጀመሪያ ጊዜ ከዚያ ከሚኖሩበት ጊቢው ወጥተው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመገኘት ከቦርዱ ሃላፊዎች ጋር የኦነግ ጽህፈት ቤት ስለመዘጋቱ፣ በእስር ላይ የሚገኙ የፓርቲው አመራሮች ለደህንነታቸው አስጊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን እና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡ በመሆኑም ከቀደመው ሁኔታ በተሻለ መንቀሳቀስ ጀምረዋል፡፡»

አቶ ዳውድ በአሁኑ ወቅት አግኝተዋል የተባለው የመንቀሳቀስ ነጻነት ወደ ፈለጉበት መሄድ የሚያስችላቸው እና በስልክም የፈለጉትን ሰው ደውለው የሚገናኙበት ነው ወይ የተባሉት አማካሪያቸው ዶ/ር ሽጉጥ ገለታ ቀጣዩን ብለዋል። «እኔ የማውቀው መንቀሳቀሳቸውን እንጂ ከዚህ በፊት የሚጠቀሙበት ስልካቸውን በመቀማታቸው ለጊዜው አግኝተናቸው ማውራት አልቻልንም፡፡ ይሁንና አስፈላጊ የሆኑ አንዳንድ ቦታዎችን ለመድረስ እድሉን እንዳገኙ ነው ለጊዜው የምናውቀው፡፡ይሄ ለውጥ ቦርዱ ደብዳቤውን ከፃፌ ወዲህ ያየነው መልካም የሚባል ለውጥ ነው፡፡ ከሰባት ቀናት በፊት ጀምሮ የተሻለ የመንቀሳቀስ ሁኔታ ቢኖርም ሙሉ በሙሉ በነጻነት የመሄድ ነገር አለ የሚል መደምደሚያ ግን የለንም፡፡»

ዶ/ር ሽጉጥ አክለው አበረታች ያሉት ይህ ለውጥ በእስር ቤት ውስጥ ሕይወታቸው አደጋ ውስጥ ነው ወዳሏቸው የኦነግ አመራር እንደሚሸጋገርም ተስፋ አለን ብለዋል። «ለውጡ መልካም ነው፡፡ ይህ ቀጥሎ ሊቀመንበሩ ሙሉ በሙሉ ነጻ እስኮሆኑ እና በተለያዩ ህመሞች በእስር ቤት እየተሰቃዩ ያሉት እንደነ ሚካኤል ቦረን፣ ከኔሳ አያና እንዲሁም ከ አቶ ባቴ ዑርጌሣ ጋር በአንድ ስፍራ የነበሩ እንዲሁም ስንቴ ፍርድ ቤት ያሰናበተው እና ከ2 ዓመት በላይ ታስሮ የሚገኘው አብዲ ረጋሳ እና ሁሉም የኦነግ አባላትና አመራሮች ተለቀው ቢሮው ቢንቀሳቀስ ለሁሉም ሰላም መልካም ነው፡፡ የፖለቲካ አውዱንም ያሰፋል፡፡ አሁን የተመለከትነው መነሻ ይመስለናል፡፡ መቀጠል ያለበት ነው ብለን እናምናለን፡፡ በዚህ ሂደት ድምጻችን ላያሰሙልን የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችና ሚዲያዎች በህዝባችን ስም ምስጋና ለማቅረብ እንወዳለን፡፡» 

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራር አቶ ሚካኤል ቦረን፣ ኬኔሳ አያና፣ ዳዊት አብደታ፣ ለሚ ቤኛ፣ ገዳ ገቢሳ እና ገዳ ኦልጂራ እንዲሁም ኮሎኔል ገመቹ አያና እና አብዲ ረጋሳ አሁንም በእስር ላይ ናቸው፡፡ ፓርቲውን በቃላ አቀባይነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ባቴ ኡርጌሳ ከቀናት በፊት ከእስር ቢለቀቁም በዚሁ እስር ላይ ሳሉ ባጋጠማቸው የጤና እክል ሆስፒታል ተኝተው እየታከሙ መሆኑን ከቀናት በፊት መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት አስተያየት የሰጡን የፖለቲከኞቹ ጠበቆች በበኩላቸው ሁላቸውም በፍርድ ቤት እንዲለቀቁ የተወሰነላቸው ናቸው ይላሉ፡፡

ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሰ