1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአቶ ስመኘው በቀለ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ተፈጸመ

እሑድ፣ ሐምሌ 22 2010

የፌድራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል አቶ ዘይኑ ጀማል ስለ አሟሟታቸው "አመላካች መረጃዎች እና ማስረጃዎች" መገኘታቸውን የተናገሩ ሲሆን "በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዴት እንደሞተ፣ ለምን እንደሞተ የሚገልጹ መረጃዎችን ለኅብረተሰቡ" እናሳውቃለን ብለዋል።

https://p.dw.com/p/32GK3
Äthiopien, Simegnew Bekele, Projektleiter des Grand Ethiopian Renaissance Dam (GERD)
ምስል DW/T.Waldyes

የታላቁ ኅዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ስመኘው በቀለ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ተፈጸመ። አዲስ አበባ በሚገኘው ቅድስት ስላሴ ካቴድራል በተካሔደው የቀብር ሥነ-ሥርዓት የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ፣ ምክትል ጠቅላይ ምኒስትር ደመቀ መኮንን እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ሹማምንት ተገኝተዋል።  

ድንገተኛ ዜና ዕረፍታቸው ከተሰማ ጀምሮ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተፈጠረው ሐዘን እና  ቁጭት አለመብረዱ በመስቀል አደባባይ በተካሔደው የሽኝት መርኃ-ግብር ላይ ታይቷል። በሽኝት መርኃ-ግብሩ ላይ ገዳዮቻቸው ለፍርድ ይቅረቡ የሚሉ በርካታ ድምፆች መሰማታቸውን የአይን ዕማኞች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አቶ ስመኘው ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም መስቀል አደባባይ አካባቢ በተሽከርካሪያቸው ውስጥ ሞተው መገኘታቸው ከተሰማ በኋላ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ሐዘን ተፈጥሯል። ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ የምኅንድስና ባለሙያው አቶ ስመኘው በቀለ የሞት "ዜና ልብ ይሰብራል" ሲሉ ተናግረዋል።

የፌድራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል አቶ ዘይኑ ጀማል ስለ አሟሟታቸው "አመላካች መረጃዎች እና ማስረጃዎች" መገኘታቸውን የተናገሩ ሲሆን "በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዴት እንደሞተ፣ ለምን እንደሞተ የሚገልጹ መረጃዎችን ለኅብረተሰቡ" እናሳውቃለን ብለዋል።

የ53 አመቱ አቶ ስመኘው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ምኅንድስና ያገኙ ሲሆን በግልገል ጊቤ 1 እና ግልገል ጊቤ 2 የኃይል ማመንጫ ግንባታዎች መርተዋል። ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ በተባለው ቦታ በመገንባት ላይ የሚገኘውን የታላቁ ኅዳሴ ግድብ እስከ ዕለተ-ሞታቸው በኃላፊነት ሲመሩ ቆይተዋል።

ከአባታቸው አቶ በቀለ አይናለም እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ዘነቡ አብተው መስከረም 3 ቀን 1957 ዓ.ም. በቀድሞው ጎንደር ልፍለ ሀገር ጠዳ ወረዳ ልዩ ስሙ ማክሰኚት ከተባለ ተወለዱ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በእንፍራንዝ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፣ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በደሴ ቅዳሜ ገበያ ትምህርት ቤት እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በወልዲያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መከታተላቸውን በቀብር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተነበበው የሕይወት ታሪካቸው ይጠቁማል።