1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአብን 13 አባላት ጥሪ በአማራ ክልል

ማክሰኞ፣ ግንቦት 29 2015

በአማራ ክልል ምክር ቤት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) 13 አባላት “በሕግ ማስከበር ሽፋን በአማራ ላይ ተከፈተ» ያሉት ጦርነት በአፋጣኝ እንዲቆም በጋራ ባወጡት መግለጫ ጠይቀዋል ። የአማራ ክልል ከፍተኛ የፀጥታ ችግር ባለበት በአሁኑ ወቅት የክልሉን ልዩ ኃይልና ፋኖን እንዲበተን ማድረግ ተገቢ አይደለም ብለዋል ።

https://p.dw.com/p/4SG6r
Äthiopien Addis Abeba - Nama Hauptquartier
ምስል DW/ S. Mantegaftot Sileshi

የክልሉ ልዩ ኃይልና ፋኖን መበተን ተገቢ አይደለም ብለዋል

በአማራ ክልል ምክር ቤት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) 13 አባላት  “በሕግ ማስከበር ሽፋን በአማራ ላይ ተከፈተ» ያሉት ጦርነት በአፋጣኝ እንዲቆም  በጋራ ባወጡት መግለጫ ጠይቀዋል ። የአማራ ክልል ከፍተኛ የፀጥታ ችግር ባለበት በአሁኑ ወቅት የክልሉን ልዩ ኃይልና ፋኖን እንዲበተን ማድረግ ተገቢ አይደለም ብለዋል ። በመንግስት ከፍተኛ ስልጣን የተሰጣቸው የአብን አባላትም በክልሉ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ነው ያሉትን በደል እንዲቆም ድምፃቸውን ያሰሙ አልያም ለአማራ ሕዝብም ለራሳቸውም ክብር ሲሉ ስልጣናቸውን ይልቀቁ በማለት አንድ የንቅናቄው አባል ገልጠዋል ። 

አባላቱ ትናንት ባወጡት ረዘም ያለ መግለጫ “ከሁለት ዓመት የሰሜኑ ጦርነትና የጦርነት ጫናዎች የተረፈው ወገናችን በሌላ ጦርነት እየተገደለ፣ ሀብትና ንብረቱ እየወደመ ነው” ሲሉ አመልክተዋል፡፡ የአማራ ክልል ከፍተኛ የፀጥታ ችግር ባለበት በአሁኑ ወቅት የክልሉን ልዩ ኃይልና ፋኖን እንዲበተን ማድረግ ተገቢ እንዳልሆ የአብን የአማራ ክልል 13 ተወካዮች በመግለጫቸው መንግስትን ወቅሰዋል፣ የአማራ ክልል መንግስት ምክር ቤት “የተለየ ሁኔታ አጋጥሞኛል” በሚል የፌደራል መንግስቱንና የመከላከያን ድጋፍ ባልጠየቀበት ሁኔታ በፌደራል የሚገኙ ጥቂት ያሏቸውን የክልሉን ተወላጆ ሹመኞችን በመጠቀምና በእነርሱ አማካኝነት ክልሉን ከአዲስ አበባ የመምራት ፍላጎትና ሙከራ በተደጋጋሚ እንደሚታይና “ያልታወጀ” ያሉት ጦርነትም በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄዱ እንደሆነም አመልክተዋል ፡፡

መግለጫውን በጋራ ካወጡት የአብን የአማራ ክልል ምክር ቤት የህዝብ ተወካዮች አባላት መካከል አቶ ጌትነት ተስፋ በሰጡት ተጨማሪ አስተያየት “  ክልሉ የፀጥታ ችግር አለበት በዚህ ሰዓት ፋኖ ተበተን፣ ልዩ ኃይል ተበተን የሚለው ትክክል አይደለም፣ በሚል ከዚህ በፊት በመግለጫ ጠይቀናል፣ ግን ያንን ለመስማት የፈለገ ኃይል የለም፣ ፋኖንም፣ ልዩ ኃይሉንም እበትናለሁ ብሎ የተነሳው መንግስት ይህን ሰበብ አድርጎ የሀገር መከላከያን ሰራዊት  ወደ ክልሉ አስገብቶ ልታወጀ ጦርነት እተካሄደ ነው ያለው፡፡ በጎጃም ውስጥ ጦርነት እንዳለ እናውቃለን፣ አሁን ገብ ቢልም በጎንደር፣ በደንቢያ  ፋኖን ትጥቅ አስፈታለሁ በሚል ብዙ ችግሮች ነበሩ፣ በሰሜን ሸዋ በመንዝ በጂሩ  አካባቢ  አሁን ድረስ አለመረጋጋቶች አሉ፡፡” 

 የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ዓርማ
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ዓርማ

ባለፉት 5 ዓመታት በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልሎች “መዋቅራዊ ድጋፍ የሆነ ሁሉን አቀፍ” ያሉት ፍጅት  በአማራ ተወለላጆች ላይ እየተፈፀመበት ይገኛል ሲሉም አባላቱ ከስሰዋል፡፡ አቶ ጌትነት ተስፋ በአማራ ክልል ምክር ቤት የአብን ተወካይ፤ “ ከአዲስ አበባ አስተዳደርና ከኦሮሚያ ክልለ የሚፈናቀሉ ዜጎች አሉ፣ እነኝህ ተፈናቃዮች  በተለያዩ የክልሉ ከተሞች በረንዳ ላይ ወድቀው በታዛ ተጠልለው እርዳታ እየጠበቁ ነው ያሉት በአጠቃላይ በክልሉ 2 ሚሊዮን የሚሆን የአማራ ተፈናቃይ አለ 1 ሚሊዮን የሚሆኑት የእለት እርዳታ የሚጠብቁ ናቸው “ ብለዋል፡፡

ወቅታዊ የአፈር ማዳበሪያን እጥረት በተመለከተም አባላቱ፣ በመግለጫው መጋቢት መጀመሪያ ላይ የተካሄደውን የክልል ምክር ቤት ውይይት መነሻ በማድረግ የክልሉን ግብርና ቢሮ በእጅጉ ኮንነዋል፡፡ የቢሮ ኃላፊው በወቅቱ “በ2015 ዓ ም የማዳበሪያ ግብዓት እጥረት እንዳያጋጥም፣በወቅቱ እየተጓጓዘና በገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል በስርጭት ላይ ነው የሚል ምላሽ ቢሰጡም አሁን ገበሬው በማዳበሪያ እጥረት ያለማዳበሪያ እንዲዘራ እየተገደደ ነውም ብለዋል፡፡

በመንግስት ከፍተኛ ስልጣን ላሉ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አባላትም አቶ ጌትነት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ “ይህን በሚያደርግ መንግስት ውስጥ ተሳታፊና ውሳኔ ሰጪ መሆን ህዝባችንን የጎዳ መሆኑን አምነው፣ በተለያየ መንገድ ተቃውሞ እንዲያሰሙ ጥሪ አቀርባለሁ፣ ደፈር ያለ አቋም ወስደው ስልታን ቢለቁም ለህዝባቸውም ለራሳቸውም ክብር ነው” በማለት ተናግረዋል፡፡ መግለጫው አክሎም “በሕግ ማስከበር ስም በማንነታቸው ምክንያት የተሳሩ ወጣቶች፣ ምሁራን፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ የሐይማኖት አባቶችና የአደረጃጀት መሪዎች ከእስር እንዲፈቱ ጠይቋል ፡፡
መግለጫው በርካታ ጉዳዮችን የዳሰሰ ሲሆን የአማራ ክልል ሉዓላዊ አስተዳደር መብቶች እንዳከበሩና ጣልቃ ገብነት ያለው አሰራርም እንዲቆሙ ጠይቋል፡፡ ለቀረቡ ስሞታዎች መረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ ለማካተት ለክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮችና  ለሰላምና ፀጥታ ቢሮዎች ኃላፊዎች ብደውልም ስልካቸው አይነሳም፡፡

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሀመድ