1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ጥቅምት 26 2014

ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ድንጋጌ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አዎንታዊም አሉታዊም  አስተያየቶች ተሰጥተዋል።ዘገየ ከሚሉት አንስቶ አሁንም አልፈረደም ያሉ ምን ሊፈይድ ዓይነት አስተያየት የሰጡም አሉ። ከማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች አመዛኙ ፌስቡክ የዐቢይን መልዕክት መሰረዙን ተቃውመዋል።

https://p.dw.com/p/42be5
Äthiopien Tigray Konflikt l Gedenkgottesdienst für die Opfer mit Premier Abiy Ahmed Ali
ምስል Ethiopian Prime Ministry Office/AA/picture alliance

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ሳምንት ማክሰኞ የደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣አሜሪካን ኢትዮጵያን ከአፍሪካ የዕድገትና ዕድል ድንጋጌ አጎዋ ማገዷ እንዲሁም ፌስቡክ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን መልዕክት መሰረዙ ሰሞኑን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አነጋጋሪ ከነበሩ ጉዳዮች ውስጥ ይገኙበታል።ማክሰኞ ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓም ነበር የኢትዮጵያ ሚኒስትሮች ምክርቤት በመላ ኢትዮጵያ ተግባራዊ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደነገገው። ለስድስት ወራት እንደሚጸና የተገለጸውን ይህን አዋጅ የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት አጽድቆታል። መንግሥት ባወጣው መግለጫ መሠረ፣አዋጁ የተደነገገው በሃገር ህልውና ላይ የተደቀኑ ያላቸውን አደጋዎች በመደበኛ ሕግ ማስከበር ስርዓት መቋቋም በማዳገቱ ነው። ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ድንጋጌ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አዎንታዊም አሉታዊም  አስተያየቶች ተሰጥተዋል።ዘገየ ከሚሉት አንስቶ አሁንም አልፈረደም ያሉ ምን ሊፈይድ ዓይነት አስተያየት የሰጡም አሉ።በርካታ ሊባሉ የሚችሉ ክብረ ነክ፣ ዘር ተኮር ዘለፋዎችና ስሜታዊ አስተያየቶችም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተንሸራሽረዋል። እነርሱን ወደ ጎን ትተን በታረመ አንደበት የቀረቡትን ስንቃኝ፤ አድ ኪያ በሚል የፌስቡክ ስም የተሰጠ አስተያየት በአጭሩ አዋጁን «ትክክለኛ ውሳኔ» ይላል ሃሺም አብደላ ደግሞ በተቃራኒው «በጣም የዘገየ ውሳኔ» ብለውታል፤ጥላሁን ሙሉጌታም እንደ ሃሺም በጣም የዘገየ ካሉ በኋላ ግን «ወሳኝ » የሚል አክለውበታል።ፍሬህይወት ግርማ ገመቹ አስተያየታቸውን ለመስጠት የተጠቀሙት «የቸገረው እርጉዝ ያገባል» የሚለውን ምሳሌያዊ አነጋገር ነው።መቅደስ ሙሉነህም እንደ ፍሬህይወት በተመሳሳይ መንገድ ነው ሃሳባቸውን የገለጹት «ሙሽራ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ ሆናችሁብን እኮ» ሲሉ የቶጎ ውጫሌ ኢትዮጵያ አስተያየት አዋጁን የሚደግፍ ነው።የቶጎ ውጫሌ ኢትዮጵያ ቢዘገይም ሲሉ ይጀምሩና «እጅግ በጣም አስቸኳይና ተመጣጣኝ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችል ነው፣ ሐገርን ማዳን ያስፈልጋል ።ሲሉ ጠቀሜታውን ዘርዝረዋል። ሰሎሞን ፉራ ግን ይህን የሚቀበሉ አይመስሉም።«ተኝታችሁ ትከርሙና ኮሽ ባለ ቁጥር ወረቀትና እስክርብቶ አገናኝቶ መደስኮር ነው ስራችሁ ጠላት እያለ ትራስ አመቻችቶ የሚተኛ መንግስት እናንተን አየን ሲሉ ጠንካራ ወቀሳቸውን ከሰነዘሩ በኋላ  « አገር እየሞተ ፣እንስሳት ሳይቀር እያለቀ ፣ ምን ልትመሩ እንደሆነ አላወቅንም አናውቅም ፣በይሉኝታ አገር አይመራም ፤ ከፈጣሪ እንጅ ከእናንተ ምንም አንጠብቅም በማለት ሀሳባቸውን ደምድመዋል። 
በዚህ ሳምንት ማክሰኞ የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም የሚከታተልና በበላይነት የሚመራ የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ ዕዝ ተቋቁሟል።በአዋጁ እንደሰፈረው የመምሪያ ዕዙ የሰዓት እላፊ ገደብ ሊወስን ፣ማናቸውም የህዝብ የመገናኛ እና የህዝብ መጓጓዥ ዘዴ እንዲዘጋ ወይም እንዲቋረጥ ሊያዝ ይችላል።  ሰዎች ለጊዜው በተወሰነ ቦታ እንዲቆዩ፣ ወደ ተወሰነ አካባቢ እንዳይገቡ ወይም ከተወሰነ ቦታ እንዲለቁ ለማዘዝ እንደሚችልም በአዋጁ ተጠቅሷል።
የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ኢትዮጵያን ምርቶቿን ከቀረጥ ነጻ ወደ አሜሪካ ማስገባት ከሚያስችላት ከአፍሪቃ የዕድገት እና ዕድል ድንጋጌ (አግዋ) ማገዳቸውን ያሳወቁት በዚህ ሳምንት ማክሰኞ ነበር።ባይደን ውሳኔውን ያስተላለፉት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ነው ባሉት የመብት ጥሰት ምክንያት ነው።ውሳኔው በዚህ ድንጋጌ ተጠቃሚ በሆኑ ኢንዱስትሪዎች ተቀጥረው የሚሰሩ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ሥራ እንደሚያሳጣ የኢትዮጵያን እድገትም እንደሚጎዳ ተደጋግሞ ሲገለጽ ቆይቷል። የባይደን የእገዳ ውሳኔ ከተሰማ በኋላ በማኅበራዊ መገናና ዘዴዎች ቁጣ ብሶትና ቁጭት አዘል አስተያየቶች ተሰጥተዋል።መፍትሄ ይሆናል ያሉትን የበኩላቸውን አማራጭ የሰነዘሩም ጥቂት አይደሉም። ፍቃዱ ሸዋረጋ «የነጭ አጎብዳጅ አይደለንም ያለአሜሪካ ይኖረናል እንኖራለንም በማለት እጥር ምጥን ያለ ሃሳባቸውን በፌስቡክ አስፍረዋል።»«ሲጀመር አግዋ ድሀ ሀጋራት ከድህነት እንዲወጡ የታሰበ ፕሮጀክት አይደለም።» ሲል የተንደረደረደረው የጥላሁን መስፍን ሃሳብ ከዚያ ይልቅ« የአሜሪካንን አገዛዝን በሌሎች አገሮች ላይ ለመጫን ያለመ መፍቅሬ የአፍቃሪ ቅኝ አገዛዝ ፕሮጀክት ነበር ይላል።ስሚዝ ጎልድ ደግሞ የተበደለን መንግሥት መቅጣት ምን የሚሉት ድራማ ነው ሲሉ ጠይቀዋል«ማዕቀቡ የሚጎዳው ጠግበው የማይበሉ ምስኪን ኢትዮጵያውያንን መሆኑን በማስረዳት ።
ጌቶች በማለት ሃሳባቸውን የሚጀምሩት አሌክስ ገብረወልድ « ጌቶች አገር ሰላም ሲሆን ነው ማንኛውንም ነገር ወደ ውጭ መላክ የሚቻለው በአሁኑ ሰዓት ለኢትዮጵያ ይኸ አያስጨንቀንም AGOA 2000ን አገዱ አላገዱ ኢትዮጵያ መቼ ከ ድህነት ወጣ ታውቃለች በማለት መልዕክታቸውን  አጠቃለዋል።ዮሐንስ ከበደ በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረ አጭር አስተያየት «ኢትዮጵያ ቀድማ የነበረች እንጂ በአገዋ አልተመሰረተችም።»ይላል። 

Äthiopien Hawassa Industrial Park
ምስል AFP/E. Jiregna

ኢትዮጵያ ከአግዋ እንድትታገድ ባይደን መወሰናቸውን ካሳወቁ በኋላ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሜሪካን ውሳኔውን መልሳ  እንድታጤን የሚጠይቅ መግለጫ አውጥቷል። መግለጫው አሜሪካን ኢትዮጵያን ከአግዋ ለማገድ ሰበብ ያደረገችው የሀገሪቱ የሰብዓዊ መብት አያያዝ በቂ ምክንያት እንዳይደለም ጠቅሷል። እገዳው ከ200 ሺህ በላይ አነስተኛ ገቢ ያላቸው እና ከጉዳዩ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው በተለይም ሴቶችን ተጎጂ እንደሚያደርግ የጠቀሰው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ የአሜሪካ መንግስት ውሳኔውን መልሶ እንዲያጤነው በአጽንኦት  ጠይቋል። ሌላው የሰሞኑ የማኅበራዊ መገናና ዘዴዎች መነጋገሪያ ፣ፌስቡክ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ያስተላለፉትን መልዕክት ማንሳቱ ነው። ዐቢይ ባለፈው እሁድ በተረጋገጠ የፌስቡክ ገጻቸው ያወጡትን መልዕክት ፌስቡክ ግጭት ያባብሳል በሚል ምክንያት ማንሳቱን አስታውቋል።ፌስቡክ የሰረዘው ፣ዐቢይ አሸባሪ ያሉትን «ህወሓት ለመመከት ለመቀልበስና ለመቅበር» ኢትዮጵያውያን እንዲነሱ ባለፈው እሁድ በፌስቡክ ጥሪ ያስተላለፉበትን መልዕክት ነበር። ከማኅበራዊ መገናናዘዴዎች ተጠቃሚዎች አመዛኙ የፌስቡክን እርምጃ ተቃውመዋል።ሶሎማን የተባሉት አስተያየት ሰጭ በፌስቡክ «ስርዓት የሚባል ነገር አለ ! አልበዛም ፌስቡክ  በማለት ሲያስጠነቅቁ ,መስፍን መዝሙር ውግያው ከአሜሪካ ጋር ነው በሌላ ወገን ሲለጥፉ ለምን ዝም ይላል በማለት ሞግተዋል።  
ኤም ኡስ ዲ አሊም ፌስ ቡክ ፍትሀዊ ከሆነ ለምን የህወሓትን ገፅ አልዘጋውም በማለት ጠይቀዋል። አስናቀ ተስፋዬ የምዕራባውያንና ሶሻል ሚዲያዎቹ በኢትዮጵያ ላይ የሐሰት መረጃና የጥላቻ ዘመቻ አዲስ ባይሆንም እንዲህ ተጠናክረው የተነሱት ግን የአሁኑ ይብሳል። በዚህ ደግሞ አንድነታችንና ሀገራዊ ስሜታችን እንድንሳሳ አድርገውናል፤ እንወጣዋለን ብለዋል።ዳዊት አባይነህ ደግሞ የፌስቡክን እርምጃ« 110 ሚሊዮን ህዝብን መናቅ ነው ካሉ በኋላ ፌስቡክን የኢትዮጵያ መንግሥት መዝጋት አለበት ሲሉ የበኩላቸውን ሃሳብ አቅርበዋል። ዮሴፍ ዮሴፍ ፊስ ቡክ ይዘጋ አንፈልገውም አሰከ ወዲያኛው ብለዋል። ከይራት ጃምም ፌስቡክ እትዮጵያ ውስጥ እንዳይሰራ ለምን አያረገዉም ? ለእትዮጵያ በፌስቡክ የተረፋት ግጭት መባላት ነው ይቅርብን ፌስቡክ ሲሉ የዳዊትን ሃሳብ አጠናክረዋል። ማክ ማክ ደግሞ በተቃራኒው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ወቅሰዋል ።« ሲጀመር ከአንድ የሀገር ጠቅላይ ሚ/ር የማይጠበቅ የስድብ ናዳ ያወርዳሉ ካሉ በኋላ ይሄ መሆን የለበትም በማለት አሳስበዋል። አሊ ሃያ ኢድሪስም ስድብ ከሀገር መሪ አይጠበቅም ብለዋል።
ሁሴን መሐመድ ደግሞ ፌስቡክን ይከሳሉ «ስንት ሽብር የሚነዙ የህወሓት ጀሌዎች እያሉ የዶክተር አብይን ንግግር መሰረዝ በኢትዮጵያ ላይ ምን ያህል ጥላቻ እንዳላቸው ማሳያ ነው፡፡ቢቻል ኑሮ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ፌስቡክን ባለመጠቀም ከመሪያችን ጉን መሆናችንን መሳየት ነበረብን ሲሉ ሃሳብ አቅርበዋል።«ዲሞክራት ነኝ ከሚል አካል ይህ አይጠበቅም።በቅኝ ሊገዙን ይፈልጋሉ ልበል ያሉት ደግሞ ጸጋዬ አለማየሁ ናቸው። የዐቢይን መልዕክት ፌስቡክ ትናንት ጠዋት ካነሳው በኋላ ፣በኢትዮጵያ ግጭት እንዲባባስ እየሰራ ነው ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት ፌስቡክን ከሷል።

USA Facebook Logo
ምስል JB Le Quere/Maxppp/picture alliance

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ