1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሐሙስ፣ ጥቅምት 17 2009

የኢትዮጵያ መንግሥት ያወጣዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንቀፅ 30 የሕግ አስከባሪዎች ትምህርት ተቋማት ላይ ያላቸዉን ስልጣን ይዘረዝራል።ተማሪዎችም ሆኑ ሕህዝቡ በፍራቻ ተዉጧል፣ ሁለት... ሦስት ሆኖ መቆም ወይም መነጋገር ሌላ ጣጣ ያመጣል,,,

https://p.dw.com/p/2RnBI
Hauptcampus der Universität Addis Abeba AAU
ምስል DW

Edited--State of Emergency Impact on Studnets - MP3-Stereo

ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባሉት ዉስጥ «አድማ የሚያደርጉ ሰዎችን ለመያዝና ችግሩን ለማስቆም የሕግ አስከባሪ አካላት በእነዚህ ተቋማት ውስጥ በመግባት አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ» እንደሚችሉም ይገልፃል። ከአዋጁ በፊት በኦሮሚያና አማራ ክልል በተካሄዱ የተቃዉሞ እንቅስቃሴዎች ብዙ ተማሪዎች መሞታቸዉ እና መታሠራቸዉ ይታወሳል። ከአዋጁ በኋላም ተማሪዎች እየተሰሩ መሆኑ ይሰማል። 

ለአዳማ ዩኒቬርስት ቅርበት አለኝ የሚሉት ግን ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የፈለጉት ግለሰብ አወጁ ሳይወጣ በፊትም ተማርዎች እየተባረሩ፣ እየታሰሩና እየተገደሉ ነዉ ይላሉ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ተግባራዊ መሆን ከተጀመረም ከበፊቱ ልዩነት የለዉም በማለት ለዶቼ ቬሌ ገልጸዋል። ከተማሪዎች የሰሙትንና የታዘቡትንም እንዲህ አጋርተዉናል።

ተማሪዎችም ሆኑ ሕህዝቡ በፍራቻ ተዉጧል፣ ሁለት... ሦስት ሆኖ መቆም ወይም መነጋገር ሌላ ጣጣ ያመጣል በማለትም እኚሁ እማኝ ተናግረግረዋል። ይህን ሃሳብ የሚጋሩት ስማቸዉም እንዳይጠቀስ የጠየቁን የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ፤ ዩኒቨርሲቲዉ «ፍርሃት ነግሶበታል» ነዉ የሚሉት።

ከመስከረም 18, 2009 ጀምሮ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸዉ እንዲመለሱ ጥሪ መደረጉን በትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴታ የሆኑት ዶክተር ካባ ኡርጌሳ «ተማሪዎቹ በሙሉ አሁን ወደየ ዩኒቨርሲቲያቸዉ ደርሰዉ፣ ትምህርቱም በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ» መሆኑን ለዶቼ ቬሌ ገልጸዋል። የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ «አድማ» የሚያነሱትን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ለሕግ አስከባሪዎች ስልጣን በመስጠቱ በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ ተፅዕኖ አይኖረዉም ወይ ለሚለዉ ጥያቄ፣ አዋጁ የተማርዎችን ደንነት ለመጠበቅ እንጅ ለተቃራንዉ ኢንዳልታቀደ ይናገራሉ።

የፌስቡክ ድረ ገፃችን ተከታታዮችንን በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ አወያይተን ነበር። አስተያየት ከሰጡን ዉስጥም አንዱ «ሕጉ የወጣዉ እኮ ድሮ ለተሠሩ ወንጀሎች ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት ነው። ዛሬ ቢገድሉ፣ ቢያስሩ፣ ቢዘርፉ ሕጉ ፈቅዶላቸዋል። ለምን እንዲህ አደረጋችሁ ቢባሉ አዋጁን ስለተላለፈ ነው ይላሉ። አላማው ይህ ብቻ ነው»  ሲሉ፣ ሌላዉ ደግሞ «አዋጁ ያስቀመጠዉ በትምህርት ተቋማት ዉስጥ አድማ ከተደረገና ለማድረግ ከተሞከረ እንዲሁም ሁከት ከተነሳ፤ ገብቶ የማስቆም ግዴታ አለበት ነዉ የተባለዉ እንጂ በሰላማዊ ተማሪዎች ለይ ምንም ተፅኖ ያስከትላል ብዬ አላስብም» ብለዋል። «ከትምህርት ቤት ዉስጥ መምህራን እንጂ መከላከያ ሠራዎት ምን ይሠራል፣ ትምህር ቤት እኮ የእዉቀት ገበያ እንጂ የአገሪቱ ዳር ደንበር አይደለም፤ በእዉነት ግራ የገባዉ የሚገርም መንግሥት ነዉ» በማለትም አስተያየታቸዉን የሰጡ አሉ።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሰ