1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት 

ዓርብ፣ መጋቢት 30 2014

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ስልጣን ከያዙ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አራት ዓመት ሞልቷቸዋል።ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓም አንስቶ በስልጣን ላይ ያሉት ዐብይ በአራቱ ዓመት የስልጣን ዘመናቸው በርካታ ለውጦች ቢያደረጉም ሀገሪቱ ግን ፖለቲካዊ ኤኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮችን አስተናግዳለች።

https://p.dw.com/p/49gh8
Äthiopien | Premierminister Abiy Ahmed Ali
ምስል Office of the Prime Minister Ethiopia/UPI Photo/Newscom/picture alliance

የመጋቢት 30 ቀን 2014 ዓም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት 

በዚህ ሳምንት አጋማሽ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾቹ ድርጅቶች አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩመን ራይትስ ዋች ከጥቅምት 2013 ዓም አንስቶ በምዕራብ ትግራይ በአማራ ክልል ኅይሎች ተፈጽሟል ያሉትን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የዘረዘሩበት ዘገባ፣ እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አራት የስልጣን ዓመታት ፣ ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል መግባቱ ፣በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተለያዩ አስተያየቶች ከተሰጠባቸው ጉዳዮች ውስጥ ናቸው። የአማራና የትግራይ መስተዳድሮች በባለቤትነት በሚወዛገቡበት ምዕራብ ትግራይ ውስጥ በሲቭሎች ላይ የደረሱት ግፎች ከጦርና በሰብዓዊነት ላይ ከተፈጸሙ ወንጀሎች እኩል ናቸው ሲሉ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩመን ራይትስ ዋች ከትናንት በስተያ ነበር የዘገቡት። ይህ  የሁለቱ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ድርጅቶች ዘገባ፣ ወንጀሎቹ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይሎች እያወቁ እና ምናልባትም አብረው እየተሳተፉ በአማራ ክልል የፀጥታ ኃይሎችና ሲቪል ባለሥልጣናት የተፈጸሙ ናቸው ብሏል።ሁለቱ ድርጅቶች ዘገባውን ያወጡት ከ400 ከሚበልጡ ሰዎች ጋር የተካሄደ ቃለ ምልልስን ጨምሮ ለወራት አካሄድን ባሉት ምርመራ መሆኑን ገልጸዋል። የጋራ ዘገባው በአካባቢው  በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ፣በኃይልና በግዳጅ መኖሪያ ቤታችን ለቀው እንዲወጡ መደረጉን ፣ግድያ እንደተፈጸመባቸው፣እንደተደፈሩ በዘፈቀደ በጅምላ እንደታሰሩ ንብረታቸው እንደተዘረፉባቸውና ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስቸው መደረጉን ገልጿል።
በዚህ የሁለቱ ድርጅቶች ዘገባ ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሀን በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። አብዛኛዎቹ ግን ጥላቻን የሚሰብኩ፣ የበቀል እርምጃዎችን የሚያበረታቱና ሰብዓዊነት ከቁብ የማይቆጥሩ ዘለፋዎች የሚያመዝንባቸው ናቸው።ከመካከላቸው የተሻሉ የሚባሉትን መርጠን ለመቃኘት ሞክረናል።
ኢብራሂም አህመድ የሚል የፌስቡክ ስም ያላቸው አስተያየት ሰጭ «ማን እንደገደላቸው በገለልተኛ ወገን እስካልተረጋገጠ ድረስ ከኬንያ ሁነው የፃፉትን የአንድ ወገን ሪፖርት ተዓማኒ ማድረግ አይቻልም።»በማለት ዘገባውን እንደሚጠራጠሩ ሲገልጹ  ተይብ ቢያለሉ ደግሞ «ውሸት ነው ለማለት ይከብዳል ። በወቅቱ ባዶ እጃቸውን ትግራይ ገብተው መሳሪያ ታጥቀው የተመለሱ ጀግና  እየተባሉ መሞካሸታቸውን ዛሬ ለመካድ አመቺ አይደለም ።ካሉ በኋላ «የሚያዋጣው» ሲሉ ዘላቂ መፍትሄ ያሉትን ጠቁመዋል።«የሚያዋጣው ወንጀሎኞችን አሳልፎ መስጠት ነው ህወሃቶችም በነሱበኩል ያሉትን ወንጀለኞች አሳልፈው መስጠት ፤ያለው አማራጭ ይሄነው።
ኡርጂ ቢያ ደግሞ «ይህ የስው ፍርድ ነው ወደ ፊት የምናየውን የእግዚአብሔር ፍርድ እየጠበቅን ነው ብለዋል። 
አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩመን ራይትስ ዋች ያወጡት የጋራ ዘገባ በምዕራብ ትግራይ ፣በትግራይ ተወላጆች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት« ዘር ማጽዳት» ሲል ገልጾታል። 
መሐመድ ለገሠ አሊ ዘገባውን ከፋፋይ ብለውታል።«እናት ሀገራችን እንድትበታተን እርስ በርስ እንድንበላላ መግለጫ ከማውጣት አንድ እንድንሆን ፣ስለሰላም የሚሰብክ ድርጅትም ሆነ ግለሰብ አላየሁም እንደዚህ ዓይነቱ መግለጫ ጭራሽ ከማባባስ እና ከመከፋፈል በስተቀር የሚያስገኘው ነገር የለም። ያለፈው ኪሳራ ሳያንሰን ለውድቀትና እልቂት ይዳርገናል።» ሲሉም ኮንነውታል ቡልክ አቡልክ በሚል ስም የሰፈረ አስተያየት «ቦታው ላይ ሳይገኙ ከአንድ ወገን ብቻ የተሰበሰበ መረጃ በመሰለኝና በደሳለኝ የግል ስሜትንና ፍላጎትን ወይም ድብቅ የፖለቲካ ፍላጎትን ማቅረብ እውነቱን ቢያዳፍን እንጂ እንዳይጋለጥ አያደርገውም።»ሲል ተጠቃሏል። ዐቢያ ግርማ ደግሞ በተቃራኒው «አጥፊ ሲጠየቅ ዛራፍ ዘራፍ አይሰራም ከዚህም ከዚያም ካለ ይጠየቁ ጠያቂ ካለ ህግ ማስከበር ተብሎ ብዙ ስተት መሰራቱ እማይቀር እዳ ነው ።የደቦ ፍርድ እያየነው ነው ጦርነቱ ሁሉን ነካክቷል» ሲሉ የበኩላቸውን ሀሳብ ሰንዝረዋል። ሚካኤል ወርቅነህ የተባሉ አስተያየት ሰጭ ደግሞ ምሬታቸውን ገልጸዋል,«በእርግጥ ያማል የአብሮነትንና የወንድማማችነትን ገመድ እንዲህ ዳግመኛ እንዳይጠገን አርጋችው ፍጹም ሀረመኔያዊ በሆነና ስብዕና በጎደለው መልኩ ቆራረጣችው አሁንም እንኳን የቀሩት በረሀብ ያልቁ ዘንድ እየፈረዳችውባቸው ነው ለዚህም እግዚአብሔር በእርግጥ ይፈርዳል። »ሲሉ ሃሳባቸውን ገልጸዋል።
«ማንም ኃያል ነኝ ባይ፣ ከኔ በላይ ሃብት፣ንብረት፣ኢኮኖሚ፣ሥልጣን አለኝ ብሎ ሌላዉን በኃይል፣ በማዕቀብ፣በማንበርከክ ለመግዛት ያስብ ይሆናል። እዉነትን አጣሞ ሊያወራ ይችላል ፈጣሬ ግን ይፈርዳል ያሉት ደግሞ ወዩ ቄ ናቸው።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ስልጣን ከያዙ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አራት ዓመት ሞልቷቸዋል። ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓም አንስቶ በስልጣን ላይ ያሉት ዐብይ በአራቱ ዓመት የስልጣን ዘመናቸው በርካታ ለውጦች ቢደረጉም ሀገሪቱ ግን ፖለቲካዊ ኤኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮችን አስተናግዳለች። ስልጣን እንደያዙ ኢትዮጵያዊነትን ደጋግመው ማቀንቀናቸው ብዙ ደጋፊ ያፈራላቸው ዐቢይ አሁን የሚተቹዋቸው ጨምረዋል። ስለ ዐቢያ የአራት ዓመት የስልጣን ዘመን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተለያዩ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። ከመካከላቸው የአብነት ጽጌ አስተያየት አንዱ ነው።«እውነት ነው እልልልል ብለን ተቀብለናል ግን እልልልታችን ሀዘን ይዞብን መጣ።ብዙ ሰው ያለ ኃጥእቱ ያለበደሉ ሞተ ተራበ ተጠማ ከኖረበት መንደር ተሰደደ ብቻ ምን ልናገር እግዚአብሔር ይድረስልን ።አብይንም ቆራጥ መሪ ያድርገው። ትንሽም ቢሆን ይጨክን ወንጀለኛንና ስግብግብ ነጋዴን ለህግ ያ ቅርብልን።ብቻ ቆራጥ ሁን።ብለዋል አብነት።ደረጀ አንዳርጌ አራቱን ዓመት በአጭር አረፍተ ነገር ነው የገለጹት «የአራት አመት ጉዞ ከዳጡ ወደ ማጡ ማጡ ነዉ።»ሱሉ መንገሻ ሲሳይም በተመሳሳይ መንገድ ያስቀመጡት።«የኛ ነገር ከእሾህ ወደ ጋሬጣ ሆነ ! በማለት ፣ሲሳይ በቀለ «ምን ዋጋ አለው ብሶ ቁጭ አለ እንጂ» ብለዋል።«ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ በንግግር አስደስተውናል አጥግበውናል አበልፅገውናል ሲሉ ሃሳባቸውን ጀምረው« በተግባር መሬት ላይ እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው አገራችን ታይቶ የማይታወቅ መከራና አደጋ ውስጥ የገባችበት ጊዜ ነው እግዚአብሔር ሀገራችንንና ህዝቧን ይጠብቅልን ።» በማለት መልክሙን የተመኙት  ደግሞ መኮንን ዎልዴ ናቸው። ብስራት ጉቱ አቢያ አህመድ እወድዎታለሁ ሲሉ ፍቅራቸውን ገልጸውላቸዋል።
ሲሳይ የሱስ ረታ በሚል የፌስቡክ ስም ስር የሰፈረ አስተያየትም ዶክተር ዐቢይ እንወድሀለን በማለት ጀምሮ ችግሩ ሲል ይቀጥላል። «ችግሩ የሱ ሳይሆን ከሱ ስር ያሉት ሃላፊነት የማይሰማቸው ሰዎች ናቸው ሀገሪቱን ይህን ሁሉ ዋጋ ያስከፈሉት »ይላል ።ካለፈው ሳምንት መጨረሻ አንስቶ ሰብዓዊ እርዳታ ወደትግራይ ክልል በየብስ መግባት ጀምሯል። የትግራይ መስተዳድር እስከ ትናንት ድረስ እርዳታ የጫኑ 26 መኪናዎች ትግራይ ክልል መግባታቸውን አስታውቋል። ሆኖም መስተዳድሩ እርዳታው በሚፈለገው መጠንና ፍጥነት እየገባ አይደለም ሲል አማሯል። ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል መግባት መጀመሩን በሚመለከት ከተሰጡ አስተያየቶች ውስጥ ከሰብዓዊነት ያፈነገጡና ሚዛን የጎደላቸው ይበዛሉ። ጥቂት ቢሆኑም ግን የተሻሉ አስተያየቶችም አልጠፉም።  አዩሬ የእቴ ሆነልኝና ሄሌላ አሰፋ «ተመስገን» ሲሉ ተናኘ  ዴሌቦም እናመስግንሀለን ጌታ ብለዋል።  «ጥሩ ነገር ምንጊዘም ጥሩ ነዉ ጦርነት ለማንም አይበጅም ያሉት ደግሞ  ጌቱ አለማየሁ ናቸው። 
 ጥላቻና መጨካከን ያመዘነባቸው አስተያየቶች ልብቸውን የነካ የሚመስለው «ይጋራ አገር» የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ « አንዱ ሌላውን በዚህ ልክ አምሪሮ ይጠላል ብየ አስበ አልዉቅም። የአለማችን አስመሳይ ዜጎች ሳንሆን አንቀርም። እንዴት አንዱ በሌላዉ ስቃይ ይደሰታል ??? በተለይ ትንሽ ፊደል ከቆጠረዉ ዜጋ ??? በጥላቻ የሚንገነባዉ ትዉልድ ፣አገር ሁሉ ዉሸት ነዉ» ብለዋል። ዳዊት ዘለቀ ደግሞ « መንገድ ስልክ መሰረታዊ ነገሮችም ይከፈቱ ሲሉ ጠይቀዋል።ይድነቃቸው ተስፋዬ ደግሞ መኪኖቹን በሰላም ይመልሳቸው ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል። 

Äthiopien Mekelle | WFP Nahrungsmittellager
ምስል Million H. Silasse/DW
Human Rights Watch Logo
Logo Amnesty International
ምስል Sebastian Kahnert/dpa/picture alliance

ኂሩት መለሰ 

ሸዋዬ ለገሠ