1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

የአሜሪካ የጉዞ ማዕቀብና የምሁራን ዕይታ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 17 2013

የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ የመንግስት ባለስልጣናት ላይ የጉዞ ማዕቀብ ለመጣል መወሰኑ የጎላ ጉዳት እንደማይኖረው ምሁራን አመለከቱ፣ የእቀባ ዓላማው ኢትዮጵያውያንን የበለጠ ለማጋጨት የተሰበ እንደሆነም አመልክተዋል፣ ይህን ተከትሎ ቀጣይ ርምጃዎች ካሉ በኢትዮጵያ ላይ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችልም ገምተዋል። 

https://p.dw.com/p/3twBT
Anthony J. Blinken
ምስል Graeme Jennings/CNP/picture alliance

«ለአሜሪካ ውርደት ነው»

የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ የመንግስት ባለስልጣናት ላይ የጉዞ ማዕቀብ ለመጣል መወሰኑ የጎላ ጉዳት እንደማይኖረው ምሁራን አመለከቱ፣ የእቀባ ዓላማው ኢትዮጵያውያንን የበለጠ ለማጋጨት የተሰበ እንደሆነም አመልክተዋል፣ ይህን ተከትሎ ቀጣይ ርምጃዎች ካሉ በኢትዮጵያ ላይ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችልም ገምተዋል። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  ባለፈው እሁድ ባወጣው መግለጫ በትግራይ ያለውን የሰብአዊ መብት አያያዝ እንዲሻሻል ጥረት አላደረጉም ባላቸውና በስም ባልጠቀሳቸው የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣  የአማራና የህወሓት ባለስልጣናት ላይ የጉዞ ማዕቀብ ማድረጉን አመልክቷል።

አሁን የተጣለው ማዕቀብ የጎላ ጉዳት እንደማያስከትል ምሁራን አስረድተዋል። አቶ ቻላቸው ታረቀኝ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህርና የ3ኛ ዲግሪ ተማሪ ናቸው፡፡ እንደርሳቸው የኢትዮጵያ ባለስልጣናት አሜሪካ ሄዱ አልሄዱ የሚያመጣው ፋይዳ የለም፣ እንዲያውም ለጉዞና ተያዥ ጉዳዮች የሚወጣን ወጪ ይቀንሳል ሲሉ ተናግረዋል። 

በጠቅላይ አቃቤ ሕግ ማዕረግ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዋና የሕግ አማካሪ አቶ መርሐጽድቅ መኮንን በበኩላቸው «የክልል መሪዎችን ሳይቀር እዚህ ውስጥ እስከ ማካተት መደረሱ ለአሜሪካ ውርደት ነው» ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዐዊ መብትና የፌደራሊዝም ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ የአቶ መርሐጽድቅን ሀሳብ በመጋራት በአንድ ሉዓላዊት አገር ያለን ክልል በተናጠል መክሰስ አስፈላጊ ያልሆነና ተሳሳተ እንደሆነ አመልክተዋል።

አጠቃላይ የተወሰደው እርምጃ ትክክል ነው ባይባልም የአማራ ክልል መንግስት ባለስልጣናት የተከሰሱበት ሁኔታ ግን ምክንያት የለሽ ነው ብለውታል ዶ/ር ሲሳይ የአሜሪካ መንግስት ለአማራ ክልል ባለስልጣናት ያለውን ምልከታ የሚያሳይ እንጂ ትርጉም ያለው ውጤት እንደማመጣ አቶ መርሐጽድቅ ተናግረዋል።  «አሸባሪ» ያሉትን ቡድንና የፌደራሉን መንግስት በአንድ ዓይን ማየቱ ራሱ የተዛባ ምልከታ ነው ብለዋል ዶ/ር ሲሳይ  የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲው መምህር አቶ ቻላቸው እንደሚሉት የማዕቀቡ ዓላማ በአገሪቱ ሰላም እንዳይመጣ የታቀደ እንደሆነ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሰት ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የአሜሪካ ድርጅቶች ላይ የሚወስደው ርምጃ ይኖር ይሆን? ተብለው የተጠየቁት ምሁራኑ፣ ውል ከገቡበት ሁኔታ በማፈንገጥ የአገሪቱን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር ከፈፀሙ «አዎ» ብለዋል። 

ዓለምነው መኮንን

 
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ