1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብሊንከን ጋዜጣዊ መግለጫ በአዲስ አበባ

ዓርብ፣ መጋቢት 8 2015

ኢትዮጵያውያን እርቅን እና ተጠያቂነትን ያልተወ አካታችና ሁሉን ያቀፋ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትን ለመተግበር የያዙትን ቁርጠኛ አቋም እንዲያስቀጥሉ የጠየቁት ብሊንከን "መርዛማ ቅራኔዎችንና የጎሳ መከፋፈልን ማስወገድ፣በሰሜን ኢትዮጵያ ፣ በኦሮሚያም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ያለውን ብሔር ተኮር ግጭቶችን ለማስቆም ብቸኛው መንገድ ነው" ሲሉም አሳስበዋል።

https://p.dw.com/p/4Ollo
Äthiopien | PK US Außenminister in Addis Abeba
ምስል Tiksa Negeri/AP Photo/picture alliance

የብሊንከን ጋዜጣዊ መግለጫ በአዲስ አበባ

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን  በፌዴራል መንግሥት እና በሕወሓት መካከል የተደረሰው የተኩስ ማቆም የሰላም ስምምነት አተገባበር ፍሬያማ እንዲሆን አሜሪካ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቁ። በኢትዮጵያ ከትናንት ጀምሮ ይፋዊ ጉብኝት ሲያደርጉ የቆዩት ብሊንከን ከኢትዮጵያ መሪዎች ጋር ከተወያዩ በኋላ በሰጠት መግለጫ የሰላም ስምምነቱ ውሳኔ ትልቅ ስኬት እና እርምጃ መሆኑን፣ በዚህም ሕይወትን ማዳን ማስቻሉን እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲቀንሱ ማድረጉን በአድናቆት አንስተዋል። ኢትዮጵያዊያን እርቅን እና ተጠያቂነትን ያልተወ አካታች እና ሁሉን ያቀፋ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትን ለመተግበር የያዙትን ቁርጠኛ አቋም እንዲያስቀጥሉ ያሳሰቡት ብሊንከን ዘላቂ ሰላም መገንባት ፈታኝ እንደሆነ አስታውሰዋል። "መርዛማ ቅራኔዎችን እና የጎሳ መከፋፈልን ማስወገድ፣በሰሜን ኢትዮጵያ ፣ በኦሮሚያም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ያለውን ብሔር ተኮር ግጭቶችን ለማስቆም ብቸኛው መንገድ ነው" ሲሉም አሳስበዋል።ሰሎሞን ሙጬ ከአዲስ አበባ ዝርዝር አለው።
"የአፍሪካ አመራር ልህቀት አስፈላጊነት አንዱ ማሳያ" በፌዴራል መንግሥት እና በሕወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት መሆኑን የገለፁት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ፣ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነቱ ፍፁም አውዳሚ እንደነበር፣ በመቶ ሽዎች መሞታቸውን ፣ ሚሊዮኖች ከቀያቸው እንዲሸሹ ማድረጉንና ፣ በርካቶች ለምግብና መድኃኒት እጥረት እንዲጋለጡ ማድረጉን፣ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች እና የንግድ ተቋማት በከፋ ሁኔታ እንዲወድሙ ማድረጉንም ጠቅሰዋል። 
"የሰላም ስምምነቱ ውሳኔ ትልቅ ስኬት እና እርምጃ ነው። ሕይወትን ማዳን ችሏል፣ ሕይወትንም እየቀየረ ነው። የመሣሪያ ድምፅ ቆማል። ውጊያው በማቆሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ቀንሰዋል። የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ መድረስ እንዲችል አድርጓል። በትግራይ መሰረታዊ አገልግሎቶች ተመልሰዋል። ሕውሓትም የኤርትራን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራል ያልሆኑ ኃይላትም ከገቡበት እየወጡ ነው። በአሜሪካ ድጋፍ በደቡብ አፍሪካ እና በኬንያ የሰላም ስምምነቱ እንዲሳካ በአፍሪካ ሕብረት አካልት የተደረገው ቁርጠኛ የዲፕሎማሲ ሥራ ይህ ስምምነት እንዲሳካ ቁልፍ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የፌዴራል መንግሥት እንዲሁም የትግራይ መሪዎች ይህ ስምምነት እንዲሳካ እና ይህ መሻሻል እንዲመጣ ስላደረጉ ሊመሰገኑ ይገባል።"
ዛሬ ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህመት ጋር ሰላማዊ እና የበለፀገ አፍሪካ መገንባት በሚለው የሕብረቱን እቅድ ማሳካት በሚቻልበት ዙሪያ እንደሚወያዩ የገለፁት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን አስቀድመው ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ከምክትላቸው እና ከሌሎችም ጋር መወያየታቸውን ገልፀዋል። ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተጨማሪ በስም ባይጠቅሷቸውም የስምምነቱ ፈራሚ የህወሓት ባለስልጣናትንም ማነጋገራቸውን ገልፀዋል። አሜሪካ ከ2020 ወዲህ ለኢትዮጵያ ለሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት እስከ 3 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን የገለፁት ብሊንከን ድጋፍ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል። መንግሥታቸው በግጭት እና በድርቅ ለተጎዱ በርካታ ኢትዮጵያውያን አስቸኳይ የምግብ አቅርቦት እና የሰብዓዊ ድጋፍ ማገዣ የሚውል ተጨማሪ የ331 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጋቸውንም አስታውቀዋል። 
"ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በሁለቱም ወገኖች የተፈፀመውን ከፍተኛ ጉዳት ማስታወስና እውቅና መስጠት ወደፊት የሚያራምድ ወሳኝ ጉዳይ ነው።ኢትዮጵያዊያን እርቅን እና ተጠያቂነትን የሚያካትት አካታች እና ሁሉን ያቀፋ የሽግግር ፍትሕ መርህን ለመተግበር የያዙትን ቁርጠኛ አቋም እንዲያስቀጥሉ እናበረታታለን። መርዛማ ቅራኔዎችን እና የጎሳ መከፋፈልን ማስወገድ በሰሜን ኢትዮጵያ ፣ በኦሮሚያም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ያለውን ብሔር ተኮር ግጭቶችን ለማስወገድ ብቸኛው መንገድ ነው።እንደ አጋር ሀገር አሜሪካ ይህ እንዲሳካ የቴክኒክ እና የገንዘብ ድጋፍ ታደርጋለች"ብለዋል።
በትግራይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየቀነሰ መሆኑን ፣ ይህንንም በገለልተኛ አካላት እንዳረጋገጡ የተናገሩት ብሊንከን
በሁለቱም ወገን ጥሰት የፈፀሙ የጦርነቱ ተዋናዮች ላይ ተጠያቂነት እንዲሰፍን እንዲሁም "የሽግግር ፍትሕ" እንዲተገበር ደጋግመው አንስተዋል። የሰላም ስምምነቱ አተገባበርን እንደ ዋና ጉዳይ ይታያል ያሉት እኚህ የዩማይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ባለስልጣን ኢትዮጵያ ወደ አጎዋ ዳግም ስለመመለስ አለመመለሷ ተጠይቀው ግልጽ ምላሽ አልሰጡበትም።
ሕወሓት ከባድ የጦር መሣሪያውን ስለመፍታቱ የገለፁት ብሊንከን ገና ያልተጠናቀቀ እና በሂደት ላይ ያለ ቢሆንም 
የኤርትራን ጨምሮ "ሌሎች ኃይላት" ከትግራይ ክልል እየወጡ መሆኑን እያየን ነው ብለዋል።የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ አለም የብሊንከንን ገብኝት አስመልክቶ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በሁለቱ ሀገራት መካከል "አዲስ ምዕራፍ" የመከፈቱ ማሳያ ነው ብለዋል።

Äthiopien USA Demeke Hasen Antony Blinken
ምስል Ethiopian Foreign Ministry
የኢትዮጵያና የአሜሪካን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ውይይት በአዲስ አበባ
የኢትዮጵያና የአሜሪካን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ውይይት በአዲስ አበባ ምስል Ethiopian Foreign Ministry

ሰሎሞን ሙጬ 
ኂሩት መለሰ 
አዜብ ታደሰ