1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የአፍሪቃ ጉብኝት እና አንደምታዉ

ሰኞ፣ መጋቢት 18 2015

የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሃገራቸዉ ከአፍሪቃ ጋር ያላትን ግንኙነት ያጠናክራል ያሉትን ጉብኝት በማካኼድ ላይ ይገኛሉ። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቅርቡ በኢትዮጵያና ኒጀር ጉብኝት ካደረጉ በኋላ፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ በሦስት የአፍሪቃ ሃገራት ጉብኝታቸዉን ጀምረዋል። የባለሥልጣኑ ጉብኝት አንደምታ ምን ይሆን?

https://p.dw.com/p/4PJsX
Ghana | Kamala Harris in Accra
ምስል NIPAH DENNIS/AFP/Getty Images

የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሃገራቸው ከአፍሪቃ ጋር ያላትን ግንኙነት ያጠናክራል ያሉትን ተከታታይ ጉብኝት በአህጉሪቱ በማካኼድ ላይ ይገኛሉ። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በቅርቡ በኢትዮጵያና ኒጀር ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ፣ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ በሦስት የአፍሪቃ ሃገራት የሚያካኺዱትን ጉብኝት ጀምረዋል። ዶይቸ ቨለ ያነጋገራቸው፣የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ፣ፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያ ኀያላኑ ሃገራት አፍሪቃ ውስጥ ብርቱ ፉክክር መግጠማቸውን አመልክተዋል።  

Ghana | Kamala Harris in Accra
ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ በጋናምስል MISPER APAWU//AFP/Getty Images

ባለፈው ታኅሣስ ወር ላይ ዋሽንግተን ዲሲ የተካኼው የአሜሪካና አፍሪቃ መሪዎች ጉባዔ፣አሜሪካ የሚጠበቅባትና የሚገባትን ያህል አፍሪቃ ውስጥ እንዳልሰራች የገመገመችበትን አጋጣሚ ፈጥሮላታል። ይህንንም ክፍተት ለመሙላት አሜሪካ፣ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደንን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናቷ በአፍሪቃ ጉብኝት እንደሚያካኼዱ አስታውቃ ነበር። በዚህ መሠረት ቀዳማዊት እመቤት ዶክተር ጁል ባይደን፣በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪን ፊልድ፣እንዲሁም የገንዘብ ሚኒስትሯ ጃኔት የለን ጉብኝት ይጠቀሳል።

ከቅርብ ቀናት በፊት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን አሁን ደግሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ በጋና ታንዛኒያና ዛምቢያ የሚያደርጉትን የአንድ ሳምንት ጉብኝት ጀምረዋል። በአሜሪካው ሞርጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያ ለዶይቸ ቨለ እንደተናገሩት፣ጉብኝቱ ፕሬዚዳንት ባይደን በአፍሪቃና አሜሪካ ጉባዔ ወቅት አሜሪካ አፍሪቃ ነች በማለት ባደረጉት ንግግር ላይ ተመርኩዞ የሚካኼድ ነው።

"አሜሪካ አፍሪቃ ውስጥ ገብታለች፣አሜሪካ አፍሪቃ ውስጥ ነች በሚል ተናግረው ነበር።አንዱ በእዛ በኩል ነው የሚታየው።የዛ ቃል የገቡት ውጤት ነው ይኼ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ወደ አፍሪቃ መመላለስ።" በኢትዮጵያና ኒጀር በቅርቡ በነበራቸው ቆይታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ያነጋገሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፣ጉብኝት በመዛኙ በሃገራቱ የጸጥታ ችግሮች ላይ ያተኮረ ነበር።

ከሰላም ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ሌሎች የታዮ አጀንዳዎች ቢኖሩም ዶክተር ጌታቸው፤ "በኢትዮጵያም እንደተባለው፣እንግዲህ የሰላሙን ጉዳይ አስታከው በዚያ ላይ ደግሞ ለኢትዮጵያ ብድር እንደሚሰጡ ወደ 331 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሰጡና፣ለሰብዓዊ ዕርዳታ ለአየር እንክብካቤ፣የተፈናቀሉ ሰዎችን መልሶ ለማቋቋም አስጊ ሁኔታዎች የሚታዩት ደግሞ የአየር የተፈጥሮ መዛባት እንደውም በዚያ አካባቢ ሰሞኑን የተበደሩት ገንዘብ ብዙ ስለሆነና የመክፈል አቀማቸውም እየተዳከመ ስለኼደ ገንዘብ መክፈሉን ትታችሁ የአየር እንክብካቤ ላይ ምክንያቱም የአየር ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ኾኗል።"

ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ካሚላ ሃሪስ በፈንታቸው፣የአፍሪቃ ጉብኝታቸው  ግቡን የምጣኔ ሃብት ጉዳዮች ላይ አድርጓል።በአፍሪቃ የፈጠራ ሥራዎች፣ ቴክኖሎጂ፣ደህንነት፣የምግብ ዋስትና፣የሴቶችን አቅም ማጎልበት፣የአየር ንብረትና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ላይም ከየሃገሪቱ መሪዎች ጋር ይወያያሉ ብለዋል የዜና ዘገባዎች።  የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት አዋቂው ዶክተር ጌታቸው ፣የጉብኝቶቹን አንደምታ እንዲህ ይገለጹታል።

Ghana | Kamala Harris in Accra
ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ በጋናምስል NIPAH DENNIS/AFP/Getty Images

"በዚህ በዓለም ሽኩቻ ባለበት፣የቻይናና የሩሲያ በአፍሪቃ ውስጥ ያላቸው ተጽዕኖ እያየለ በመምጣቱ፣በዚህ ወቅት እንግዲህ፣በትራምፕም ምክንያት የአሜሪካ ትኩረት ከአፍሪቃ ትንሽ ገለል ገሸሽ ብሎ ስለነበረ፣አሁን ወደ እዛ እየተመለሱ ስለሆነ፣እንግዲህ ለእነዚህ ሁለት ኀያላን ሃገራት ቻይናና ሩሲያ አፍሪቃ ውስጥ በሚያደርጉት ሁኔታ ያንን እንግዲህ ለመወጣትና ከእነሱ ጋር ለመቋቋም የሚደረግ ሽኩቻ ነው" አፍሪቃ፣በማደግ ላይ ባለው ወጣት ሕዝቧ ቁጥር እንዲሁም ግዙፍ የተፈጥሮ ሃብት የኀያላን ሃገራትን ትኩረት ስባለች። ከዚህ አኳያ ዩናይትድስቴትስ፣በተለይ ከቻይናና ሩሲያ ከባድ ፉክክር ተደቅኖባታል።

ዞሮ ዞሮ ግን ሩጫው ኹሉም የራሳቸውን ጥቅም ከማስጠበቅ አኳያ እንደሚታይ፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው አብራርተውልናል። "እንግዲህ፣እነዚህ ታላላቅ ሃገሮች ወደ አፍሪቃ የሚመጡት፣ለአፍሪቃ የሚበጅ ነገር ለመስራት ኃይማኖታዊ ነገር ዝምብሎ ደግ ነገር ለመስራት፣አፍሪቃን ለመርዳት፣የሚል ነገር ሳይሆን ሁላቸውም የራሳቸው ጥቅም ነው የሚያራምዱት።የአፍሪቃኖቹን ጥቅም የሚያራምዱት፣አፍሪቃውያኖች ብቻ ናቸው።ሁሉም አሜሪካም ሆነ ቻይናም ሆነ ሩሲያ ፉክክር ገብተዋል።ልክ እንደቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ሌላ ፉክክር ቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ከወደቀ፣ከአለቀ ካከተመለት በኇላ ሌላ ፉክክር መጥቷል።"ብለዋል።

 

ታሪኩ ኃይሉ

አዜብ ታደሰ

ዮኃንስ ገብረግዚአብሔር