1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል አዲስ የመማሪያ መጻሕፍት ሊያዘጋጅ መሆኑ

ረቡዕ፣ ሰኔ 9 2013

አዳዲስ የትምህርት መማሪያ መጻሕፍት ለማዘጋጀት እየሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፣ ቢሮው በባሕር ዳር እየተካሄደ ባለው የመጻሕፍት ዝግጅት የጋራ ውይይት ላይ እንደተገለፀው ቀደም ባለው የትምህርት ፖሊሲ የተዘጋጁ መጻሕፍት፣ ለአገር በቀል እውቀቶች ትኩረት ያልሰጠ፣ የወጣቱን የስራ ተነሳሽነት ያቀዛቀዘ ነበር ተብሏል፡፡

https://p.dw.com/p/3uxW8
Äthiopien | Workshop zu Vorbereitung von neuen Lehrmaterialien an der Bahir Dar Universität
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ 8ኛ ክፍል ያለውን የመማሪያና የመምህሩ መምሪያ ይዘጋጃል


አዳዲስ የትምህርት መማሪያ መጻሕፍት ለማዘጋጀት እየሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፣ ቢሮው በባሕር ዳር እየተካሄደ ባለው የመጻሕፍት ዝግጅት የጋራ ውይይት ላይ እንደተገለፀው ቀደም ባለው የትምህርት ፖሊሲ የተዘጋጁ መጻሕፍት፣ ለአገር በቀል እውቀቶች ትኩረት ያልሰጠ፣ የወጣቱን የስራ ተነሳሽነት ያቀዛቀዘ ነበር ተብሏል፡፡
በ1986 ዓም የተቀረፀው የትምህርት ፖሊሲን መሰረት አድርገው የተዘጋጁ መጻሕፍት ክፍተትያለባቸው በመሆኑ በ30 ዓመት ውስጥ ይሳካሉ የተባሉ ግቦች አሁንም እንዳልተሳኩ የአዲሱን የአማራ ክልል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መጻሕፍት ዝግጅት በበላይነት የሚመራው በአማራ ክልል የምሁራን መማክርት ጉባኤ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር ዳዊት መኮንን ተናግረዋል፡፡
በ1986 ዓ ም የተቀረፀው የትምህርት ፖሊሲ የአደረጃጀት፣ የአሰራር፣ የተገቢነትና አገራዊ እይታው የተሟላ እንዳልነበረ ያስታወሱት ደግሞ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ናቸው፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ትምህርት በጥራቱ፣ በተደራሽነቱ፣ በተገቢነቱና በፍትሃዊነቱ በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይ ባለማግኘቱ ስርዓተ ትምህርቱን እንዲቀየር ዋናው ምክንያት እንደሆነ ዶ/ር ይልቃል አመለክተዋል፡፡
ዶ/ር ይልቃል አያይዘውም ወጥ አገራዊ ማዕቀፍና ደረጃ መዘጋጀቱንና ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ 8ኛ ክፍል ያለውን የመማሪያና የመምህሩ መምሪያ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ በማገናዘብ እንዲዘጋጅ በጥናት ማዕቀፉ የተፈቀደ በመሆኑ ለተጠቀሱት የትምህርት ደረጃዎች መጻሕፍቱ በክልሉ ይዘጋጃሉ ብለዋል፡፡
መጻሕፍቱን እንዲያዘጋጁ ከተመረጡና በውይይቱ ካገኘናቸው መምህራን መካከል ከደቡብ ጎንደር የመጡት አቶ እሸቴ መብራቴ ቀደም ባለው ጊዜ የነበሩ ክፍተቶችን አስታውሰዋል፡፡ ቀደም ባለው የትምህርት ፖሊሲ ምክንያት “ህፃናት ከልጅነታቸው ጀምሮ የእጅ ጽህፈት ስለማይለማመዱ የመርሀ ጽህፈት (የንግግር ድምፅ ወኪል ፊደላትን) በትክክል አይፅፉም፤ ለአገር በቀል እውቀትም ባዳ ነበሩ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የመጻሕፍት ዝግጅቱ በመምህራን እንዲዘጋጅ መታቀዱ በሙያዊ እውቀት ታግዘው መጻሕፍቱ እንዲዘጋጁ እንደሚያግዝም አስረድተዋል፡፡
ትናንት የተጀመረውና ከሁሉም የአማራ ክልል ዞኖች የተውጣጡ የመጻሕፍት ዝግጅት ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ውይይት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበብ ህንፃ እስከፊታችን ሐሙስ እንደሚቀጥል ከወጣው መርሀ-ግብር ለመረዳት ችለናል። 


ዓለምነው መኮንን


አዜብ ታደሰ 
ሸዋዬ ለገሰ