1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአህያ ቄራ በቢሾፍቱና ሌሎችም

ዓርብ፣ መጋቢት 29 2009

በርካቶችን ያስደነገጠ ዜና ነበር። የአህያ ሥጋ የሚበለትበት ቄራ ኢትዮጵያ ደብረዘይት ወይንም ቢሾፍቱ ውስጥ ሥራ ሊጀምር እንደሆነ የመነገሩ ዜና። ብዙዎች፦ ለእምነት ባህላችን ደንታ ቢሶች መበራከታቸው የፈጠረው ነው ሲሉ አስተያየቶቻቸውን ተሰጥተዋል። የውጭ ምንዛሬ እስካስገኘ ድረስ ምን ችግር አለው የሚሉም አልታጡም።

https://p.dw.com/p/2apYP
Esel
ምስል Colourbox

በርካቶችን ያስደነገጠ ዜና ነበር። የአህያ ሥጋ የሚበለትበት ቄራ ኢትዮጵያ ደብረዘይት ወይንም ቢሾፍቱ ውስጥ ሥራ ሊጀምር እንደሆነ የመነገሩ ዜና። ብዙዎች፦ ለእምነት ባህላችን ደንታ ቢሶች መበራከታቸው የፈጠረው ነው ሲሉ አስተያየቶቻቸውን ሰጥተዋል።  ድሮም በተደጋጋሚ በረሀብ የምናልቀው እንዲህ ዝግ ስለሆንን ነው፤ የውጭ ምንዛሬ እስካስገኘ ድረስ ምን ችግር አለው የሚሉም አልታጡም። የአህያ ቄራው የተቋቋመው ለውጭ ሃገራት አቅርቦት ነው ቢባልም በየመንደሩ ካሉ ሥጋ ቤቶች ስግብግብ ነጋዴዎች ሳንወድ በግድ ያልፈለግነውን ሥጋ ቢያቀርቡልን በምን እናውቃለን? የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እየተንሸራሸሩ ነው። አንዲት ኢትዮጵያዊት የቤት ሠራተኛ ኩዌት ውስጥ ከዓረብ አሠሪዋ ለማምለጥ ስትሞክር ከፎቅ ስትከሰከስ የሚታይበት ቪዲዮም ከከፍተኛ ቁጣ ጋር መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል። 

የአህያ ቄራ ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ሊጀምር መኾኑ በተነገረ ቅጽበት በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል ጎልቶ የወጣው የተቃውሞ አስተያየት ነው። «በእስልምናም በክርስትናም ውጉዝ የሆነ ድርጊት እንዲፈጸም እንዴት ተፈቀደ?» የሚለው ጥያቄ በበርካቶች ተሰንዝሯል። ዛሬ በአህያ የተጀመረው ወደ ሌሎች እንስሳት ላለመሻገሩ ምን ማስተማመኛ አለ? ያሉም አልታጡም።

ማህሌት በላቸው በትዊተር ማኅበራዊ የመገናኛ አውታር ገጿ ላይ፦ «አህያ ልናርድ ነው የሚባለው ነገር እውነት ነው፥ እንዴት ያለ እዳ ነው የገባነው ?ባህላችን ያደግንበት ስነልቦና በፍፁም አይፈቅድልንም፣ መንግስት እንዴት እንዲህ ያለ የእብደት ፍቃድ ሊሰጥ ቻለ?» ስትል አጠይቃለች። 

Esel auf Wochenmarkt in Dari Nordnigeria
ምስል DW/J-P.Scholz

«‘የአህያ ሥጋ’ የሚል ጽሑፍ ከተለጠፈበት ችግሩ አይታየኝም» ያለው ደግሞ  እዮብ አበሻ ነው፤ ለማኅሌት መልስ ሲሰጥ። «አብዛኛው ወደ ውጪ ሃገራት የሚላክ ይመስለኛል:- ባይላክ እንኳ ሰዎች የፈለጉትን መርጠው መብላት ይችላሉ:: በሁሉ ነገር መመሳሰል የለብንም» ሲል የአህያ ቄራው ለመከፈቱ ድጋፉን ገልጧል። 

ዳንኤል በትዊተር ባቀረበው ጽሑፍ፦ «አሁን የአህያ ሥጋ ወደ ውጭ ይላካል።  በቅርብ ደግሞ የአህያ ሥጋ ወደ ሀገር ቤት ማስመጣት ይቀጥላል» ሲል ስጋቱን ገልጧል። 
አፈንዲ ሙተቂ «የአህያ ሥጋ ወደ ቤጂንግ» በሚል ርእስ ያቀረበው የፌስቡክ ጽሑፍ «በኢትዮጵያ አህያ ማረድም ሆነ ስለ ሥጋው ደረትን ነፍቶ ማውራት በጣም ጸያፍ አድራጎት» እንደሆነ ያብራራል። 

«የማህበረሰቡን ሞራል፣ ስነ ምግባርና የማህበራዊ ኑሮ እሴቶች የማይመጥኑ ድርጊቶችን መከወን እና ዜናውን በሚዲያ ማስተላለፍ ክልክል» እንደሆነ በመጥቀስ «በኢትዮጵያ በወንጀለኛ መቅጫ የተከለከለ ድርጊት መፈጸሙን» ተቃውሟል። አንድ ነገር ከመወሰኑ በፊትም ግራ ቀኙን ተመልክቶ በደንብ ሊታሰብበት እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥቷል። 
ሥዩም ተሾመ በፌስቡክ ገጹ አስፋው ገዳሙን በመጥቀስ ያሰፈረው ጽሑፍ «የዕለቱ ጥቅስ፦ የአህያ ሥጋ ወድቆ እንዲቀር የሚሞግተው ጅብ ብቻ ነው!» በሚል ይነበባል። 

እሸቱ ሆማ ቄኖ በፌስ ቡክ ገጹ ባቀረበው አጠር ያለ ጽሑፍ ደግሞ፦ «ፋና ኢቢሲ ኤዜአ ዋልታ በቢሾፍቱ የአህያ ስጋ ማምረቻ ፋብሪካ ሥራ ስለመጀመሩ አንድም ዘገባ ሳይሰሩ ዝም ጭጭ ያሉት ለምን ይሆን?!?! የጾም ወቅት ስለሆነ እንዳትሉኝ ብቻ» ሲል በሳቅ ምልክት መልእክቱን ቋጭቷል።

ይኽን የአህያ ቄራ በኢትዮጵያ መከፈት በተመለከተ በዶይቸ ቬለ የአማርኛው ክፍል የፌስቡክ ገጽ ላይ ለውይይት አቅርበነው ነበር። «በቀን 200 አህያዎችን አርዶ ለቻይናና ለቬትናም ለዉጭ ገበያ ለማቅረብ የተዘጋጀዉ ‘ሻንዶንግ ዶንግ‘ የተሰኘዉ የቻይና ኩባንያ ቢሾፍቱ ከተማ ላይ የማረጃ ቦታ ወይም ቄራ መክፈቱ እየተዘገበ ነዉ። አህያ ሁነኛ የትራንስፖርት መሳርያ ሆኖ በሚያገለግልበት በኢትዮጵያ አህያን ማረድ ወይም ስጋዉን መብላት በኅብረተሰቡ ያልተለመደ፤ ተቀባይነት የሌለዉ በጣም አፀያፊ ተግባር ነዉ። ይህ የአህያ ስጋን ሊያቀርብ የተዘጋጀዉ ኩባንያ በእንዲህ ባለ ማኅበረሰብ ዉስጥ የአህያን ሥጋ ለዉጭ ገበያ ለማቅረብ ቄራ መክፈቱን እንዴት ይመለከቱታል? ሃሳባችሁን አጋሩን» ስንል ነበር ጥያቄ ያቀረብነው። 

Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

የፌስቡክ ጽሑፉን ግማሽ ሚሊዮን ግድም ሰዎች ተመልክተውታል። ከሰባት መቶ በላይ ሰዎች ደግሞ ተቀባብለውታል። ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ አስተያየቶች በቀጥታ ደርሶናል። ከአስተያየቶቹ መካከል ጥቂቶቹን ለማቅረብ እንሞክራለን። 

«ኤክስፖርት ተባለ እንጂ ለኛስ መቅረቡ ምን ያሳውቀናል ነጋዴና ባለሀብቶቻችን የሸክላ በርበሬ የጄሶ እንጀራ እና ሌላም ነገሮች አብልተውናል እኛ እንደሆነ አናልቅ ምንም ቢያበሉን» ያለው አብድራዛቅ ጠይብ ነው።

ሞሐመድ ዮሱፍ፦ «ጥያቄ አለኝ» ሲል ይጀምራል። «አንድ በኢትዮጵያ የሚገኝ ሆቴል አህያን አርዶ ለደንበኞቹ ቢያቀርብ በምን ሕግ ይቀጣል?  ምክንያቱም አህያ ማረድ ስለሚቻል» በማለት ጥያቄውን አቅርቧል።

«ይህ ነገር ከእምነት አንፃር ሲታይ ትክክል ላይሆን ይችላል። ግን ወደኛ አገር አይደለም የሚላካው። ሀገራችን ደግሞ ብዙ እንስሳ (አህያ) አላት የአህያ ስጋ ተልኮ ወደ አረብ ሀገር የሚሰደዱ ወገኖቻችን ሥራ ቢያገኙ አይሻልም? ይኽ ጉዳይ ሊመለከተው የሚችለው የእንስሳት መብት ተከራካሪዋችን ነው። ዝም ብሎ ማማረር ዋጋ የለውም። ሥራ መፍጠር ነው መፍትሄው» ያለው ደግሞ ሚኪያስ ታደለ ነው።

አለባቸው ክፍሌ፦ «ይህ ነገር እንኳን ሊያዩት ሊሰሙትም ይቀፋል። አህያ አገልጋይ እንስሳ ነው። አብዛኛው የሀገራችን ሰው እንደ መኪና እቃ ማጓጓዣው ነው። ታዲያ ይህ ተቋም ከተከፈተ ድሀው ገበሬ ለችግሩ ሲል ማጓጓዣውን ሽጦ ቁጭ ይላል ማለት ነው» በማለት አስተያየት መስጠቱን ይጀምራል።  

«ያልተለመደ የአህያ ስጋ በህብረተሰባችን እየተለመደ ይሄድና ሃይማኖታዊ ስርዐታችንን ያፈርሳል ማለት ነው» በአህያ ማረድ የጀመረ ወደ ውሻ እያለ ይቀጥላል፦ «ስለዚህ "ሳይቃጠል በቅጠል" ነውና፤ ወገኔ መቃወም ይህንን ነው። ዱሮ በጉልበት ሊገዙን የመጡትን አባቶቻችን በጉልበት መልሰዋቸዋል፤ ዛሬ በማይረባ ጥቅም የባህላቸው ተገዥ ሊያደርጉን የመጡትን ደግሞ የመመለስ የእኛ ሀላፊነትና ግዴታም ነው» በማለት አስተያየቱን ያጠቃልላል። 

Golabal Ideas Walnussernte in Kirgistan
ምስል DW/K. Palzer

ኢትዮጵያዊት የቤት ሠራተኛዋ ከፎቅ ላይ ስትወድቅ ለማዳን ከመሞከር ይልቅ በቪዲዮ ስትቀርጽ የነበረች አንዲት የኩዌት ዜጋ የቀረጸችውን ቪዲዮ በማኅበራዊ መገናኛ አውታር ማሰራጨቷ ብዙዎችን ያስቆጣ ተግባር ነበር። ኢትዮጵያዊቷ ከሰባተኛ ፎቅ ላይ ብትወድቅም ያረፈችው የብረት ግርዶሽ ላይ በመሆኑ አንድ እጇ ተሰብሮ በሕይወት ተርፋለች። ከፎቅ ላይ የወደቀችው የዓረብ ሃገራት መገናኛ አውታሮች እንደዘገቡት ራሷን ለማጥፋት ፈልጋ ሳይሆን ልትገድለኝ ነበር ካለቻት አሠሪዋ ለማምለጥ ስትሞክር እንደነበር የተናገረችበት ቪዲዮ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተሰራጭቷል።  

በርካታ ኢትዮጵያውያን አሣር መከራቸውን በሚያዩበት የዓረብ ሃገራት ገሀድ ያልወጡ በደሎች እንዳሉ ብዙዎች ተናግረዋል። በሳዑዲ ዓረቢያ የሚንገላቱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ጥቂት እንዳልሆነ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በተደጋጋሚ ይገለጣል። ከሳዑዲ ዓረቢያ በዋትስአፕ አድራሻችን የደረሰን አጭር መልእክት።

ሳዑዲ ዓረቢያ «ሀገርን ከሕገወጦች ማንጻት» የሚል ስያሜ የተሰጠው ዘመቻ ከተጀመረ ረቡዕ ዕለት አንድ ሳምንት አልፎታል። ሕገወጦች በራሳቸው ወጪ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ 90 የምኅረት ቀናት እንደተሰጣቸው ያንን የተላለፈ ደግሞ የገንዘብ እና የእስራት ቅጣት እንደሚጠብቀው ተዘግቧል። 

ከሳዑዲ ዓረቢያ በዋትስአፕ አድራሻችን የቪዲዮ መልእክትም ደርሶናል። በቪዲዮው ሰፊ ገላጣ ግቢ ውስጥ ምንጣፍ ላይ እና ሌጣ መሬት ላይ የተቀመጡ በርካታ አዋቂ እና ህጻናት ሴቶች ይታዩበታል። ቪዲዮውን ከቦታው የላከችልን ወጣት በሳዑዲ ዓረቢያ ማረፊያ ቤት ሞልቶ በብርድ ውጪ ለመቀመጥ መገደዳቸውን ገልጣለች። በቪዲዮው ውስጥ ሻንጣዎች እዚህም እዚያም ተዝረክርከው፣ የሚያለቅሱ ህጻናት ወዲህ ወዲያ ሲሉ፣ ግራ የተጋቡ ወጣት እና አዋቂ ሴቶች አቀርቅረው ስልክ ሲደውሉም ይታያል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ