1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኖቤል የሰላም ሽልማት ለሁለት ጋዜጠኞች ተሰጠ

ዓርብ፣ መስከረም 28 2014

የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊዎች ይፋ በተደረጉበት ስነ ስርዓት፣በጎርጎሮሳዊው 2019 የኖቤል የሰላም የኖቤል ሽልማት ለኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እንዲሰጥ በተላለፈው ውሳኔ ላይ የተጠየቁት፣ የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ ሊቀመንበር ራይስ-አንደርሰን ከዛሬው ተሸላሚዎች ውጭ ስለሌሎች የሰላም ኖቤል ተሸላሚዎች አስተያየት አልሰጥም ብለዋል።

https://p.dw.com/p/41Sdx
Bildkombo-Die Freidensnobel-Preistraeger Maria Ressa und Dmitry Muratov 2021

ፊሊፒናዊቷ ጋዜጠኛ ማርያ ርየሳና ሩስያዊው ጋዜጠኛ ዲሚትሪ ሙራቶቭ  የዘንድሮውን የሰላም ኖቤል ተሸለሙ። ሁለቱ ጋዜጠኞች ለሽልማቱ የተመረጡት መገናኛ ብዙሀን ላልተቋረጡ ጥቃቶች በተጋለጡባቸው አገሮች ሃሳብን በነፃ ለመግለጽ ላደረጉት ትግል መሆኑን የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴው ሊቀመንበር ቤሪት ራይስ አንደርሰን አስታውቀዋል።
«የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ የጎርጎሮሳዊው 2021 ዓም የኖቤል የሰላም ሽልማት ለማርያ ሬይሳና ለዲሚትሪ ሙራቶቭ እንዲሰጥ የወሰነው ለዴሞክራሲና ለዘላቂ ሰላም ቅድመ ሁኔታ የሆነውን ሀሳብን በነጻ መግለጽን ለማስጠበቅ ላደረጓቸው ጥረቶች ነው። ሚስ ሬይሳና ሚስተር ሞራቶቭ የኖቤል የሰላም ሽልማት የሚቀበሉት በፊሊፒንስና በሩስያ ሃሳብን በነጻ ለመግለጽ ያለ አንዳች ፍርሀት ላካሄዱት ትግል ነው። »
አንደርሰን  «ነጻ ገለልተኛ እና ተጨባጭ እውነትን መሠረት ያደረገ ጋዜጠኝነት ሥልጣንን አለአግባብ መጠቀምን ውሸትን እና የጦርነት ቅስቀሳን ለመከላከል ያገለግላል» ብለዋል። «ሀሳብን በነጻነት መግለጽና የፕሬስ ነጻነት በሌለበት፣ የሕዝቦችን፣ ወንድማማችነት በተሳካ መንገድ ማራመድ፣ ትጥቅ ማስፈታትና የተሻለ የዓለም ስርዓት ማስፈን አስቸጋሪ እንደሚሆንም ጠቅሰዋል። ጋዜጠኛ ሬይሳ «ራፕለር» የተባለው ዜናዎችን የሚያቀርብ ድረ ገጽ ተባባሪ መሥራች ስትሆን ጋዜጣው በፕሬዝዳንት ሮድሪጎ ዱቴርቴ አገዛዝ ሰዎች ለተገደሉበት ለአወዛጋቢው ፀረ አደንዛዥ እጽ ዘመቻ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራ ነው። እርስዋና ራፕለር ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እንዴት የሀሰት ዜናዎችን ለማሰራጨት እና ተቃዋሚዎችን ለማሸማቀቅ ጥቅም ላይ እንደሚውሉ የሚያሳይ ሰነድም አዘጋጅተዋል። ጋዜጠኛ ማርያ ሬይሳ ባለፈው ዓመት በስም ማጥፋት ተወንጅላ የእስር ብይን ተላልፎባታል። ሌላው የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሙራቶቭ ኖቫያ የተባለው ነጻ የሩስያ ጋዜጣ  ተባባሪ መሥራች ነው። የኖቤል ኮሚቴ እንዳለው ጋዜጣው በሩስያ ከሚገኙ ነፃ ጋዜጦች ከፍ ያለ ደረጃ የሚሰጠው ነው። ባለፉት አስር ዓመታትም በፊሊፒንስ 17 በሩስያ ደግሞ 23 የመገናኛ ብዙሀን ሠራተኞች ተገድለዋል። የሩስያው ኖቭያ ጋዜጣ ሥራ ከጀመረበት ከዛሬ 28 ዓመት አንስቶ ስድስት ጋዜጠኞቹ ተገድለዋል። ከመካከላቸው ደም አፋሳሹን የቼችንያውን ጦርነት የዘገበችው አና ፖሊቶኮቭስካያ ትገኝበታለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊዎች ይፋ በተደረጉበት ስነ ስርዓት ላይ በጎርጎሮሳዊው 2019 የኖቤል የሰላም የኖቤል ሽልማት ለኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እንዲሰጥ በተላለፈው ውሳኔ ላይ የተጠየቁት፣ የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ ሊቀመንበር ራይስ-አንደርሰን ከዛሬው ተሸላሚዎች ውጭ ስለ ሌሎች የኖቤል የሰላም ተሸላሚዎች አስተያየት አልሰጥም ብለዋል። ሆኖም አንደርሰን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፕሬስ ነጻነት ይዞታ ከሚፈለገው በጣም የራቀና በርካታ ገደቦችም የተጣሉበት ነው ሲሉ መልሰዋል።

Äthiopien | Premierminister Abiy Ahmed Ali
ምስል Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance

ኂሩት መለሰ 

ሸዋዬ ለገሠ