1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኔቶ የሩቅ ምስራቅ ጉብኝት

ማክሰኞ፣ ጥር 23 2015

የስሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ ዋና ጸሐፊ የንስ ስቶልትንበርግ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ፤ ለዩክሬን የሚስጡት እርዳታ ከሰብዓዊ እርዳታ ባሻገር የጦር መሳሪያዎችንም እንዲጨምር አሳሰቡ። ሚስተር ስቶልትንበርግ ይህን ያሳሰቡት ባለፉት ሁለት ቀናት በደቡብ ኮሪያና ዛሬ ደግሞ በጃፓን እያደረጉ ባለው ጉብኝት ነው።

https://p.dw.com/p/4MvKA
Südkorea Seoul | Jens Stoltenberg trifft Verteidigungsminister Lee Jong-sup
ምስል Yonhap/picture alliance

«ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ከሰብዓዊ ርዳታ ባሻገር የጦር መሳርያንም እንዲሰጡ» ኔቶ

የስሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ ዋና ጸሐፊ የንስ ስቶልትንበርግ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ፤ ለዩክሬን የሚስጡት እርዳታ ከሰብዓዊ እርዳታ ባሻገር የጦር መሳሪያዎችንም እንዲጨምር አሳሰቡ። ሚስተር ስቶልትንበርግ ይህን ያሳሰቡት ባለፉት ሁለት ቀናት በደቡብ ኮሪያና ዛሬ ደግሞ በጃፓን እያደረጉ ባለው ጉብኝት ነው። ሩሲያ ዩክሬንን እነደወረርች ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ የጣሉትን ማዕቀብ ተግባራዊ በማድረግና ለዩክሬንም እርዳታ በመለገስ ከጥምር ኃይሉ ጎን ከተሰለፉት አገሮች ቀድሚዎቹ እንደሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፤ የሁለቱ አገሮች መሪዎች ባለፈው ዓመት በተደረገው የኔቶ የመሪዎች ጉባኤም ተሳትፊዎች ነበሩ ። 

Südkorea Seoul | NATO Generalsekratär Stoltenberg und Südkoreas Außenminister Park Jin
የኔቶ ዋናፀሐፊ እና የደቡብ ኮርያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ምስል Kim Min-Hee/REUTERS

ዋና ጸሐፊ ስቶልትንበርግ በአሁኑ ወቅት የሚይደርጉት ጉብኝትም ሁለቱ አገሮች ለዩክሬን እየሰጡ ካለው የሰባዊና የሎጂስቲክስ ድጋፍ  ባለፈ የወታደራዊ እርዳታዎችንና የጦር መሳሪያዎችን እንዲጨምሩ ለማግባባት እንደሆነ ተገምቷል። ዋና ጸሐፊው ባለፉት ሁለት ቀናት  የዴቡብ ኮሪያ ጉብኝታቸው፤ ከኮሪያ መሪዎችና ባለስልጣኖች ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች፤ የሩሲያ ዩክሬንን መውረር በአካባቢው ሰላም ጭምር የፈጠረውን  ስጋት  በመግለጽ ዩክሬንን በመሳሪያ በመርዳት የሩሲያን ጦረንነት  መግታትን ወቅታዊነትና  አስፈላጊነት አስረድተዋል።

“ የኔቶና ደቡብ ኮሪያ ደህንነት ጉዳይ የተያያዘ መሆኑን እንረዳለን።  የሰሜን ኮሪያ የሚሳይል ሙክራዎችንና የኒውክለር ፕሮግራሞች ስጋት መሆኑ ግልጽ ሲሆን፤ ስሜን ኮሪያ ለሩሲያ የሮኬትን ሚሳይል ድጋፍ እያደረገች መሆኑ ለአካባቢውም አደጋ“ መሆኑ ግልጽ ነው በማለት ለዩክሬን የሚስጠውን እርዳታ በዓይነትና በመጠን ማሳደገን አስፈላጊነት አስገንዘበዋል። 

ደቡብ ኮሪያ የጦር መሳሪያን በግጭት ውስጥ ላሉ አገሮች መስጠትን የሚከለክል ህግ እንዳላት ቢታወቅም፤ እንደፖላንድ ካሉ  አገሮች ጋር ባላት ከፍተኛ  የመስሪያ ንግድ አማካይነት እርዳታዋን ልትሰጥ እንደምትችል ነው የሚነገረው። 

ሚስተር ስቶልትንበርግ ዛሬ በጃፓን አየር ሀይል ቢዝ ተገንተው ባደረጉት ንግግርም፤ “ የዩክሬን ጦርነት የጋራ ደህንነታችን የተያያዘ መሆኑን ያረጋገጠ ነው። ፕሬዝዳንት ፑቲንን ዩክሬንን ካሸነፉ ለዩክሬኖች አሳዛኝ ክስተትና ትልቅ ሽንፈት ነው፤ ለአምባገነች ደግሞ  በጦር ሀይል የሚፈልጉትን ሊያገኙ እንደሚችሉ መልእክት የሚያስተላልፍ ነው” በማለት የዩክሬን ጦርነት የሁላቸውም ጦርነት የሚሆነውም በዚህ ምክኒያት እንደሆነ ገልጸዋል።  

ሚስተር ስቶልትንበርግ እና የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስተር ሚስተር  ፉሚዮ ኪሺዳ ዛሬ በጋራ ባወጡት የጋራ መገልጫም ሩሲያ በዩክሬን የፈጸመችው ወረራና ከቻይና ጋርም የፈጠሩት ወታደራዊ ትብብር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ  የወታደራዊ ስጋት የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል። ቻይና በበኩሏ ኔቶ በእስያ የሚያደርገውን መስፍፋት አጥብቃ ስታወግዝ ቆይታለች።  

Japan  PM Kishida NATO  Jens Stoltenberg
የኔቶ ዋና ፀሐፊ እና ጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትርምስል Yoichi Hayashi/AP/picture alliance

በአሁኑ ወቅት ኔቶ ለምን የሩቅ ምስራቅ አገሮችን፤ በተለይም የጃፓንና ደቡብ ኮሪያን ድጋፍ እንደፈለገና ያላቸውን ታሪክዊ ግንኙነት በሚመመለከት ሚስተር ብሌከ ሄርዚንገር በአሜሪካ  ኢንተርፕሪዝስ ተመርማሪ ሲናገሩ፤

 “ የኔቶ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ አጋርነት ከ80ዎቹና  ዘጠናዎቹ ዓመታት ጀምሮ የነበረ ነው በማለት የቆየ የመከላከያ ግንኙነት እንዳላቸውና የአሜሪንንም የተለያዩ ወታደራዊ ዘመቻዎች ይደግፉ እንደነበር“ አስታውሰዋል። 

ዋና ጸፊ ስቶልትንበርግ በነገው ዕለት በቶኪዮ ዩንቨርስቲ ንግግር እንደሚያደርጉም ተገልጿል። ጉብኝታቸው ጃፓን በዓለም የበለጸጉት ሰባት አገሮች ወይም ጂ ሰቨን የሚባሉት አገሮች ስብሰብ  የወቅቱን የፕሬዚዳንትነትን ስልጣን በያዘችበት ወቅትና በሚቀጥለው ወርም ጠቅላይ ሚኒስተር ኪቪዳ ዩክሬንን ይጎበኛሉ ተብሎ በሚጠበቅበት፤ እንዲሁም የዩክሬን የጦር መሳሪያ ጥያቄ እያደገ ባለበት ወቅት ነው።፡የዩከሩኑ ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ አጥብቀው ሲጠይቁ የነበረውን የጦር ታንክ እርዳታ ባለፈው ሳምንት ከጀርመንና ሌሎች አገሮች ያገኙ ቢሆንም  አሁንም ግን የተዋጊ ጀቶች ካልተሰጠኝ እያሉ ነው። ሆኖም ግን አሜሪካና ጀርመን የተዋጊ ጀቶችን ጥያቄ ከወዲሁ ውድቅ እንዳደረጉት ተገልጿል።   

 

ገበያው ንጉሴ  

ለዲደብሊው  

ብራስልስ