1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የናፍታ መኪናዎች የእገዳ ዉሳኔ በጀርመን

ማክሰኞ፣ መጋቢት 4 2010

በሚሊየን የሚቆጠሩ ከባቢ አየርን የሚበክሉ በናፍታ የሚንቀሳቀሱ መኪናዎች ከጀርመን ጎዳናዎች እንዲወገዱ ፍርድ ቤት ዉሳኔ አሳልፏል። ዉሳኔዉ የናፍታ መኪና ባለቤቶችን እና ነጋዴዎችን ሃሳብ ላይ ጥሏል፤ ለአካባቢ ተፈጥሮ የሚቆረቆሩ ድርጅቶችን ደግሞ አስፈንድቋል።

https://p.dw.com/p/2uE1l
Deutschland Fahrverbort in Städten
ምስል picture alliance/AP Photo/M. Meissner

የታገዱት መኪናዎች ወደሌሎች ሃገራት ሄደዉ ብክለትን እንዳያባብሱ ስጋት አለ

ጀርመን ዉስጥ የታወቁት ሽቱርትጋርት እና ድዩሱልዶርፍ ከተሞች የበታች ፍርድ ቤቶች ከባደን ቩተንበርግ እና ከኖርድ ራይን ቬስትፋለን ፌደራል ግዛቶች በተቀረበላቸዉ አቤቱታ መሠረት ነው፤ የናፍታ መኪናዎችን የማገድ ዉሳኔ በቅድሚያ ያሳለፉት። የላይፕሲግ ከተማ ፍርድ ቤት በበኩሉ የሁለቱን ከተሞች አርአያ በመከተል ዉሳኔያቸዉን አፀና። ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት የወሰደዉ በጀርመን የአካባቢ ተፈጥሮ ርዳታ በጀርመንኛ አፅህሮቱ (DUH) የተሰኘ ድርጅት የፍርድ ቤቱ ዉሳኔ በመላዉ የጀርመን ከተሞች ተግባራዊ እንዲሆን ግፊት እያደረገ ነው። ፍርድ ቤቱ ግን ዉሳኔዉን በሥራ ላይ የማዋሉ ነገር የየከተማዉ ማዘጋጃ ቤት ኃላፊነት ነዉ ብሏል። ተግባራዊ በሚደረግበት ጊዜም ሚዛናዊነትን በጠበቀ መልኩ እና ቀስ በቀስ መሆን እንደሚኖርበትም አሳስቧል። በዚያም ላይ የተወሰኑ በናፍታ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ከእገዳዉ ነፃ አድርጓል። አምቡላንሶች፣ ቆሻሻ የሚሰበስቡ መኪናዎች እና የፖሊስ አዉቶሞቢሎች እገዳዉ አይመለከታቸዉም። እንዲያም ሆኖ ይህ ታሪካዊ ዉሳኔ 12 ሚሊየን የሚሆኑ የናፍታ መኪናዎችን ይነካል ተብሏል።

ይህ የፍርድ ቤት ዉሳኔ የመኪና አምራቾቹን እና ሻጮችን ሲያስደነግጥ፣ ከባቢ አየር ተበክሏል በሚል አንዳች ርምጃ እንዲወሰድ ሲወተዉቱ ለኖሩት የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች ደግሞ ደስታ ሆኗል። በዉሳኔዉ የተደሰተው DUH «ለጀርመን ፅዱ አየር ይህ ታላቅ ነገር ነው» ብሎታል። ክሊን አርዝ የተሰኘዉ ሌላኛዉ ተቋም በበኩሉ «የናፍታ ተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለዉ እገዳ የአየር ብክለት ይዞታን ለማሻሻል የሚረዳ ትርጉም ያለዉ አካሄድ ነዉ» በማለት አወድሶታል።

Deutsche Umwelthilfe DHU - Diesel-Verbot
ከናፍታ መኪናዎች የሚወጣዉ ናይትሮጅን ኦክሳይድ ምስል Imago/M. Westermann

በጉዳዩ ላይ ጥናት የሚያካሂዱ ባለሙያዎች እዚህ ጀርመን በአየር ዉስጥ የተከማቸዉ ናይትሮጅን ኦክሳይድ በየዓመቱ ከ6000 እስከ 13 000 የሚገመቱ ሰዎችን ጤና በማወክ ለሞት እንደሚያበቃቸዉ  ይናገራሉ። በከባቢ አየር ዉስጥ የተከማቸዉ ናይትሮጅን ኦክሳይድ አብዛኛዉ በናፍታ ከሚዘወሩ ተሽከርካሪዎች የሚመጣ መሆኑን ምሁራኑ ያስረዳሉ። በአዉሮጳ ኅብረት የአየር ጥራት መመዘኛ መሠረት በከባቢ አየር ዉስጥ የሚገኘዉ የናይትሮጅን ኦክሳይድ መጠን ከ40 ማይክሮ ግራም መብለጥ የለበትም። በጀርመን አብዛኛዎቹ ከተሞች ይህ መጠን ከ70 ከፍ እያለ መሆኑ ተገልጿል። ብክለቱ ከታየባቸዉ ከተሞችም ሽቱትጋርት፣ ድዩስልዶርፍ፣ ኮሎኝ እና ሙኒክ ዋነኞቹ ናቸዉ። የፍርድ ቤቱ ዉሳኔ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ የናፍጣ መኪና ተጠቃሚዎችን ይነካል። የናፍታ መኪና ባለቤቶች እግረኛ መሆናቸዉ ብቻ ሳይሆን የተፈላጊነት ዋጋዉ የወደቀ ተሽከርካሪ መያዛቸዉ ስጋት ላይ ጥሏቸዋል።

ችግሩ ግን በእነሱ ብቻ አያበቃም። ለእነዚህ ወገኖች ካሳ የመስጠት ኃላፊነት የሚያሳስበውበዉ አዲሱ የሀገሪቱ ጥምር መንግሥት ኃያል ራስ ምታት መሆኑም አይቀርም። የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች ለተግባራዊነቱ የሚደርጉት ግፊት እንዳለ ሆኖ የፍርድ ቤቱ ዉሳኔ ያስከተለዉን መደናገጥ ለማረጋጋት ምንም እንኳን መንግሥት በአስቸኳይ የሚደረግ ነገር እንደሌለ ቢናገርም ዉሎ አድሮ ግን እገዳዉ እንደማይቀር አፅንኦት ሰጥቷል። መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል፤

Deutsche Umwelthilfe DHU - Diesel-Verbot
ሰልፈኞቹ «ንፁሕ አየር መሠረታዊ መብት ነው» ይላሉ፤ምስል Imago/M. Westermann

«ፍርድ ቤት ገና መወሰኑ ነው። እኛም ጉዳዩን በእርግጥ በአግባቡ እንመለከተዋለን። ስንመለከተዉም በመጀመሪያ ስለሚኖረዉ የመጠን ደረጃ ያስረዳናል። አሁን ማን ሕጋዊ አማራጭ እንዳለዉ እናያለን። በዚህምምክንያት ከየከተሞቹ እና ማዘጋጃቤቶቹ ጋርም እንነጋገርበታለን። በተመሳሳይ አሁን የወሰድነዉ ርምጃ ከ2017 እስከ 2020 ዓ,ም ድረስ ፅዱ አየር እንዲኖረን ለማድረግ ያሰብነዉን የሚያሟላ ይመስላል።በብክለቱ የተጎዱ አብዛኞቹ ከተሞች በአሁኑ ሰዓት ከተባለዉ መጠን ያን ያህል እንዳላለፉ እናዉቃለን። የሚዛናዊነት ጉዳይም በፍርድ ቤቱ ዉሳኔ ላይ ትልቅ ሚና ይጫወታል። ይህም ማለት ተፈላጊዉ መጠን ላይ በፍጥነት መድረስ እንችላለን፤ በዚህም ላይ ለየት ያለ ችግር ያለባቸዉ ጥቂት ከተሞች አሉ። በመሆኑም እንዴት እና በምን መልኩ ርምጃ መዉሰድ እንዳለብን እንመለከታለን። ለአዉሮጳ ኮሚሽን የፃፍነዉን ደብዳቤ ታዉቃላችሁ፤ በዚያ ላይ ተሟግተናል። እናም በምን መልኩ ቢሆን የአየር ብክለትን መቆጣጠሪያዉ ዕቅድ በመንግሥት ርዳታ አሁን ተግባራዊ መሆን ይኖርበታል።»

ሜርክል አክለዉም ዝርዝሩንከሚመለከታቸዉ ከተሞች መነጋገሩ እንደሚቀጥል ጠቁመው ጉዳዩ ግን የግለሰቦች ብቻ እንዳልሆነም አመልክተዋል። እንዲያም ሆኖ የእገዳዉ ዉሳኔ ሁሉንም መኪናዎች አይመለከትም የሚለዉን አፅንኦት ሰጥተዉታል።  

የጀርመን የአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ ሚኒስትር ባርባራ ሄንድሪክ በበኩላቸዉ አዳዲስ በናፍታ የሚሽከረከሩ መኪናዎችን የገዙ ወገኖች ላይ እገዳዉን ተግባራዊ ማድረጉ ፍትሃዊነት የሚጎድለዉ እንደሆነ ነዉ የተናገሩት።

«በቅርቡ አዲስ እና ተገቢዉ የብክለት መቆጣጠሪያ ስልት ያለዉ የናፍታ መኪና የገዙ አሽከርካሪዎች ለችግሩ ዋጋ እንዲከፍሉ ማድረጉ ከባድ ኢፍትሀዊነት ነዉ ብዬ አስባለሁ። እያንዳንዱ ሰዉ አዲስ መኪና ለመግዛት ይችላል ማለትም የማይሆን ነዉ። ችግሩ የተፈጠረዉ በመኪና ፋብሪካዎች ነው፤ እናም በአጋጣሚዉ ካለባቸዉ ኃላፊነት ነፃ ልናወጣቸዉ አይገባም። በዚህ ምክንያትም ተጠቃሚዎች ይግባኝ የማለት መብት አላቸዉ።»

Symbolbild Diesel-Fahrverbot in Städten
የመኪናዎች እንቅስቃሴ በበርሊንምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

በናፍታ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ይታገዳሉ ሲባል ሙሉ በሙሉ የናፍታ መኪናዎች ከጀርመን ጎዳናዎች ይወገዳሉ ማለት እንዳልሆነ ከተገለጸ በኋላ የጀርመን የመኪና ፋብሪካዎች ስጋቱ ትንሽ ቀነስ ያለላቸዉ መስሏል። በጀርመን የአዉቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ማሕበር ኃላፊ ማቲያስ ቪስማንም ይህንኑ ነዉ ያንፀባረቁት።

«የጀርመን ፌደራል ፍርድ ቤቶች አስተዳደር ሁሉም የናፍታ መኪናዎች ይታገዱ የሚለዉን ዉሳኔ በመቃወሙ ተደስተናል። በየጊዜዉ እንደምንለው ዩሮ 6 ማለትም በአዉሮጳ ደረጃ የብክለት መጠናቸዉ ከዚህ ያልበለጠ መኪናዎች እገዳዉ እንደማይመለከታቸዉ ግልፅ ነው። የዉሳኔዉ ችግር ምንድነዉ፣ በተለያዩ ከተሞች የተለያዩ ደንቦች ሊኖሩ ይችላሉ፤ እናም ያ ያሳስበናል። በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የሚኖቱ የተለያዩ ደንቦችም የጀርመን መኪና አሽከርካሪዎችን ግራ አጋብተዉ መተማመን እንዳይኖራቸዉ ሊያደርጓቸዉ ይችላሉ።»

በአንድ በኩል የጀርመንን ከባቢ አየር ከብክለት ለማፅዳት የተወሰደዉ ርምጃ አዎንታዊ ቢመስልም በሌላ ጎኑ ደግሞ ለሌሎች ሃገራት እና አካባቢዎች ከወዲሁ የስጋት ምንጭ ሆኗል። ታዛቢዎች እንደሚሉት ጀርመን የራሷን አየር ለማፅዳት ያሳለፈችዉ ይህ ዉሳኔ ብክለትን ወደሉሎች ሃገራት የማሻገር አይነት ነው። ለምሳሌ የምሥራቅ አዉሮጳ ሃገራት እነ ፖላንድ፣ ሮማኒያ፣ ቤልጋርያ እና ቼክ ሪፑብሊክ የጀርመንን ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች እንደወረዱ ተረካቢዎች ናቸዉ። ጉዳዩን በቅርበት የሚያዉቁ እንደሚሉትም በጀርመን ከተሞች እንዳይሽከረከሩ የታገዱ የናፍታ መኪና ባለቤቶች ንብረታቸዉን እንደዋዛ የሚጥሉት ብቻ አይሆንም። ብዙዎቹ ሊሸጧቸዉ እንደሚችሉ ይገመታል። የመጓጓዣ እና የአካባቢ ተፈጥሮን ቁርኝት በቅርበት የሚያጠኑት የአየር ጥራት ጉዳይ አጥኚ ጁሊያ ፓሊስካኖቫ መኪናዎቹ ወደተጠቀሱት ሃገራት የመሻገራቸዉ ጉዳይ አያጠያይቅም ነዉ የሚሉት።

Symbolbild Diesel Zapfsäule
ምስል picture-alliance/dpa/B. Marks

ፖላንድ አየራቸዉ እጅግ የተበከሉ ከተሞች ያላት ሀገር መኗ ይነገርላታል። ጀርመን ዉስጥ እንዳይነዱ እገዳ የሚጣልባቸዉ ተሽከርካሪዎች ወደዚያ ሊሻገሩ እና ብክለቱን ይበልጥ ሊያባብሱት ይችላሉ የሚለዉ ስጋት ከወዲሁ መሰማት ጀምሯል። ሮማንያም ስትታይ ጉዳዩ ተመሳሳይ ነው። ባለፈዉ ዓመት በሀገሪቱ ካሉት ከአምስቱ አራቱ ተሽከርካሪዎች ያገለገሉ መሆናቸዉ ተረጋግጧል። ሀገሪቱ ያገለገሉ መኪናዎች ለሚያስከትሉት የብክለት መጠን የምታስከፍለዉ ግብር ባለመኖሩም ሮማንያን የአሮጌ መኪናዎች መናኸሪያ እንዳደረጋት የሚናገሩ አሉ።

የፍርድ ቤቱ ዉሳኔ ያስከተለዉ ተፅዕኖ በዚህ አላበቃም። ያገለገሉ ተሽከርካሪ የሚሸጡ ነጋዴዎች ገበያም ከወዲሁ ተነክቷል። ማርሴል ዲ አርቦል ያገለገሉ መኪናዎች መሸጫ ባለቤት ናቸዉ።

«የናፍታ መኪናዎች ዋጋ ከወረደ አንድ ዓመት ሆነው፤ እነሱን የመግዛቱ ፍላጎትም በፍጥነት እየቀነሰ ነው። የመግዛት ፍላጎቱ በከፊል 90 በመቶ ዝቅ ብሏል። ዋጋዉም እንዲሁ ወደ 25 በመቶ ወርዷል ማለት እችላለሁ። አሁን በተላለፈዉ ዉሳኔ ምክንያት ይበልጥ ዋጋዉን ሊቀንሰዉ ይችላል። ቆየት ብለን የመግዛት ፍላጎቱ ወዴት እንደሚሄድ እናያለን። በእኔ ግምት ሽያጭ ሊያቆም ይችላል ባይ ነኝ። አዝማሚያዉ ነበር እናም ይበልጥ ሊቀንስ ይችላል።»

ነጋዴዉ እንደሚሉት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችን በብዛት የሚሸጡት ወደ ምሥራቅ አዉሮጳ ነው። ይህም ሆኖ የናፍታ መኪናዎች ዕጣ ፈንታ አጠራጣሪ በሆነበት በአሁኑ ወቅት ታዲያ መኪና ሻጮቹ ለደንበኞቻቸዉ በራቸዉን አልዘጉም። መልሰዉ ሊገዟቸዉ የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩን ነዉ ማርሴል ዲ አርቦል የሚናገሩት።

«መኪናዉን መዉሰድ ይኖርብናል። ደንበኞቻችንን መኪናዉን አንወስድም ልንላቸዉ አንችልም። ሆኖም ግን ቅናሽ ይደረጋል። የፍርድ ቤቱ ዉሳኔ የሚያስከትለዉ ነገር ይኖራል። እርግጥ ዋጋዉን በጣም አናወርደዉም ከ10 እስከ ከ 15 በመቶ ሊቀንስ ይችላል ብሎ መገመት ይቻላል።»

Diesel
ምስል picture-alliance/dpa/J. Woitas

በትናንትናዉ እለትም አዉዲ በተጠቃሚዎች እጅ የሚገኙ የናፍታ መኪናዎቹን መልሶ የመሰብሰብ ጥሪ አስተላልፏል አዉዲ ከሚሸጣቸዉ ከ50 እስከ 55 በመቶ የሚሆኑት መኪናዎች በናፍታ የሚሽከረከሩ ናቸዉ። ባለፈዉ ሐምሌ ወር ለ850ሺህ ስድስት እና ስምንት ሲሊንደር ሞተር ያላቸዉ ምርቶቹ የብክለት መጠን ፍተሻ አካሂዶ ነበር። ይህን ምርመራም ገሚሱ በሰላም አልፈዋል።

ጀርመን ላይ በተለይ በናፍታ የሚንቀሳቀሱ መኪናዎች ጣጣ የመጣባቸዉ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2015ዓ,ም ፎልክስ ቫገን ኩባንያ ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ያጋጠመዉ የብክለት መጠን የሚያጭበረብር ፕሮግራም የተገጠመባቸዉ መኪኖቹ ምሥጢር ከተጋለጠ በኋላ ነው። ኩባንያዉም ጥፋቱን በአደባባይ አምኗል። የፎልክስቫገን መዘዝም ዛሬ ሌሎቹን የናፍታ መኪና አምራቾችን ፈተና ዉስጥ ከቷል። እርግጥ ነዉ ቱጃሮቹ የመኪና ፋብሪካዎች ኪሳራቸዉን የሚያካክሱበት ስልት አይጠፋቸዉ ይሆናል፤ ከባቢ አየር በካይ ተብለዉ ከጀርመን፤ ከፈረንሳይም ሆነ ሌሎች የአዉሮጳ ሃገራት የሚገለሉት ያገለገሉ መኪናዎች በቀነሰ ዋጋ እየተሸመቱ የሚሻገሩባቸዉ እንደአፍሪቃ ያሉ አካባቢዎች ከተፈጥሮ ጋር የሚገጥሙት ግብግብ መፍትሄ ሳያገኝ እንዲህ ባሉት አጋጣሚዎች ከባቢ አየራቸዉ ለተባባሰ ብክለት መጋለጡ እንደማይቀር ከወዲሁ ግምት የሚሰነዝሩ አልጠፉም።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ