1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኑክሌሩ ጣጣ

ሰኞ፣ ኅዳር 27 2014

ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ እንዳታመርት የሚያግደዉ፣ዩናይትድ ስቴትስና ተከታዮችዋ ባንጻሩ በኢራን ላይ የጣሉትን ማዕቀብ እንዲያነሱ የሚያስገድደዉን ስምምነት ከዩናይትድ ስቴትስና በተጨማሪ ብሪታንያ፣ፈረንሳይ፣ሩሲያ፣ቻይና፣ ጀርመንና የአዉሮጳ ሕብረት ከኢራን ጋር ተፈራርመዋል።

https://p.dw.com/p/43uJU
Österreich Joint Commission of the Joint Comprehensive Plan of Action in Wien
ምስል EU Delegation in Vienna/Xinhua/picture alliance

የኢራን ኑክሌር፣የአሜሪካ አቋምና ድርድር


ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ አደነቁት።ሐምሌ 2015 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎርያኑ አቆጣጠር ነዉ) ተከታያቸዉ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አሽቀንጥረዉ ጣሉት።ግንቦት 2018።ጆ ባይደን ደገፉት።ግን ዛሬም ድረስ ገቢር ለማድረግ እያቅማሙ ነዉ፣-የኢራን የኑክሌር ስምምነት-በመደበኛ ስሙ የጋራ አጠቃላይ የድርጊት መርሐ-ግብር (JCPOA በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ።) ዩናይትድ ስቴትስ ስምምነቱን ካፈረሰች በኋላ አራቱ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ አባላት፣ ጀርመንና የአዉሮጳ ሕብረት ከኢራን ጋር የሚያደርጉት ድርድር ባለፈዉ ሳምንት ለ5ኛ ጊዜ ቪየና-ኦስትሪያ ዉስጥ ቀጥሏል።የስምምነቱ ምንነት፣የመፍረሱ እንዴትነት፣ እንደ አዲስ የተጀመረዉ ድርድር ሒደት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁኝ ቆዩ።
ሕዳር 4፣ 1995 የእስከያኔዉ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ኢትሳቅ ራቢን በአንድ አክራሪ አይሁድ ተገደሉ።ሰዉዬዉ እንደ ወታደር ቆፍጣና ተዋጊ-አዋጊ ጄኔራል፣ እንደ ዲፕሎማት ታጋሽ ተደራዳሪ፣ እንደ ፖለቲከኛ ብልሕ መሪ-የሰላም ኖቤል ተሸላሚም እንደነበሩ የምታወሳ አጭር ትንታኔዬን የዚያን  ምሽት የሰሙ አንድ የዘመኑ የኢትዮጵያ ትልቅ ባለስልጣን በማግስቱ፣ ስለትንታኔዉ የሚሉትን ካሉ በኋላ «ለኛ ሲሆን እንደዚሕ የማትሰራዉ ለምንድነዉ?» ብለዉ ጠየቁኝ-የፈገግታም-ያድናቆትም፣ የቅሬታም ድምፀት በተላበሰ ንግግር። 
ብዙ ያላሰብኩባት መልሴ ብዙ መዘዝ የምታመጣ በሆነች ነበር።«ለዚያ ያብቃችሁና----» ነበር ያልኩት።ደግነቱ ሰዉዬዉ አንድም አልገባቸዉም-ሁለትም አልጨከኑም።ዛሬም እንደያኔዉ «ጉዳያችንን ትታችሁ» የሚሉ አሉ፣ እንደመታደል ሆኖ መልሴ የያኔዉ ነዉ።
ራቢን በአክራሪ የሁዳዊ ወጣት የተገደሉት የግብፁ ፕሬዝደንት አንዋር አሳዳት በአክራሪ አረቦች በተገደሉ በ14ኛዉ ዓመት ነበር።እንደራቢን ሁሉ ወታደርም-የጦር አዛዥም፣ፖለቲከኛም የነበሩት ሳዳት ጥቅምት 6 1981 ካይሮ አደባባይ በይጥት ተደብድበዉ የተገደሉት በዩናይትድ ስቴትስ ሸምጋይነት ከእስራኤል ጋር በመስማማታቸዉ ነበር።
ራቢን የሰላም ኖቤል የተሸለሙት፣ቴል አቪቭ-ጃፋ አደባባይ በአክራሪ አይሁድ የተገደሉትም በዩናይትድ ስቴትስ ሸምጋይነት ከፍልስጤሞች ጋር በመደራደር-መስማማታቸዉ ነበር።መደራደር-መስማማት-ያስገድል ይሆን? እርግጥ ነዉ ከግብፅ-እስራኤል ፖለቲከኞች ብዙ ቀድሞ ከማሕተመ ጋንዲ እስከ ማርቲን ሉተር ኪንግ ያሉ ስላማዊ ለዉጥን በመስበክ-በመደገፋቸዉ በየዘመናቸዉ በሰዉ እጅ ተገድለዋል።
ብዙዎች እንደሚሉት የሰላም-ድርድር ሰባኪ ደጋፊዎች እንዳነበሩና እንዳሉ ሁሉ የአመፅ፣ግድያ፣የጡንጫ አምላኪዎች መኖራቸዉ ሰላም ከሰፈነ ጥቅም-ሥልጣናቸዉ የሚቀርባቸዉ ድርድር-ዉይይት አራማጆችን ቢያጠፉ ሊገርም አይገባም።የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ የፖለቲካ መርሕ አዉራሻቸዉን የፕሬዝደንት ጆን ፊትዝጄራልድ ኬኔዲን ብሒልን ይጠቅሳሉ።ፈርተን አንደራደርም፣ መደራደርን ግን አንፈራም» ዓይነት።
 «ፕሬዝደንት ኬኔዲ ከአሜሪካ ሕዝብ ፊት ቆመዉ፣ ፈርተን አንደራደር ነገር ግን ለመደራደር አንፍራ ካሉ 50 ዓመት አለፈዉ።ያኔ ይሕን ያሉት የኑክሌር ጦር መሳሪያ ስርጭትን ለመቀነስ የረዳዉን ከሶቭየት ሕብረት ጋር የተደረገዉን ዉይይት በማስመልከት ነበር።በዚያ ዘመን በሁለቱ ልዕለ-ኃያላን መንግስታት መካከል አዉዳሚ የኑክሌር ጦርነት ይነሳል የሚል ስጋት ነበር።»
ኬኔዲም በሰዉ እጅ ተገደሉ።ሕዳር 1963።በነኬኔዲ ዘመን የነበረዉ የኑክሌር ጦርነት ሥጋት ኦባማ እንዳሉት በሳቸዉ ዘመንም  መልኩን ቀይሮ ምናልባትም ብሶ ቀጥሏል።በተለይ ለዘመናት ግጭት፣ጦርነት ዉዝግብና ሥጋት ተለይቶት በማያዉቀዉ በመካከለኛዉ ምሥራቅ የኑክሌር ጦር መሳሪያ መሰራጨት ለዓለም ሠላም ሲበዛ አሳሳቢ ነዉ-እንደ ኦባማ።
                                      
«በኛ ዘመን ያለዉ ሥጋት የኑክሌር ጦር መሳሪያ በብዙ ሐገራት መሰራጨቱ በተለይም በዓለማችን በጣም ሁከት በበዛበት በመካከለኛዉ ምስራቅ መሰራጨቱ ነዉ።»
አስተዳደራቸዉ ከሁለት ዓመት ድርድር በኋላ የኢራንን የኑክሌር ጦር መሳሪያ መርሐ-ግብር የሚያስቆም ስምምነት የፈረመዉም ኦባማ እንዳሉት አሳሳቢዉን አደጋ ለማስቀረት ነበር።
«ዛሬ፣ ከሁለት ዓመት ድርድር በኋላ፣ዩናትድ ስቴትስ ከዓለም አቀፍ ሸሪኮቻችን ጋር ሆነን ለብዙ ዓመታት የነበረዉ ጠላትነት ያላስገኘዉን ዉጤት አግኝተናል።ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ እንዳታመርት የሚያግድ አጠቃላይ የረጅም ጊዜ ስምምነት ተፈራርመናል።ይሕ ስምምነት የአሜሪካ ዲፕሎማሲ ተጨባጭና ትርጉም ያለዉ ለዉጥ እንደሚያመጣ ያሳያል።ሐገራችንንና ዓለምን ይበልጥ አስተማማኝና ሰላማዊ የሚያደረግ-ለዉጥ።»
ሐምሌ 14 2015።ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ እንዳታመርት የሚያግደዉ፣ዩናይትድ ስቴትስና ተከታዮችዋ ባንጻሩ በኢራን ላይ የጣሉትን ማዕቀብ እንዲያነሱ የሚያስገድደዉን ስምምነት ከዩናይትድ ስቴትስና በተጨማሪ ብሪታንያ፣ፈረንሳይ፣ሩሲያ፣ቻይና፣ ጀርመንና የአዉሮጳ ሕብረት ከኢራን ጋር ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ በተባበሩት መንግስታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ፀድቆ፣የዓለም ደንብ ሆኖ-ዓለም ተቀብሎታልም።ሁለት ሐገራት ግን ተቃዉመዉታል።እስራኤልና ሳዑዲ አረቢያ።ጥር 2017 ኦባማ ሔዱ ትራምፕ ተተኩ።
ቱጃሪ፣ዘረኛዉ አክራሪዉ ፕሬዝደንት ዋይትሐዉስን  ከተቆጣጠሩ በኋላ የዓለምን ፖለቲካዊ ይትበሐል፣ስምምነትና ደንብን ሲገለባብጡት ብዙ የተለፋ፣ ብዙ የተወራ፣ብዙ ተስፋ የተደረገበትን ስምምነትም አሽቀንጥረዉ ጣሉት።ግንቦት 8 2018።
«ዛሬ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ከኢራን የኑክሌር ስምምነት መዉጣትዋን አስታዉቃለሁ።ይሕ ለአንድ ወገን ያዳላ መጥፎ ስምምነት ነበር።በጭራሽ መቼም ቢሆን መደረግ አልነበረበትም።»ጨዋታ---ፈረሰ።ስምነቱ ሲፈረም ሁለት የነበሩት ተቃዋሚዎች ሶስትም፣ትልቅም፣ የኃያሎች ኃልም ሆኑ።ግን ጥር 2021 ትራምፕ ከዋይት ሐዉስ ወጡ፤ ባይደን ገቡ።ባይደን እንደምክትል ፕሬዝደንት ያፀደቁትን ስምምነት እንደ ፕሬዝደንት ከዉድቀት እንደሚያድኑት ቃል ገብተዉ ነበር።ቃሉ በርግጥ የምር ከነበረ ስምምነቱን የሻረዉን የትራምን ዉሳኔ ሽሮ የነበረዉ በነበረበት እንዲቀጥል ከማድረግ በላይ የሚጠይቀዉ አልነበረም።
ይሁንና ባይደን ቃል የገቡት አንደኛ-ድጋፍ በማሰባሰብ ፖለቲካዊ ስሌት በመሆኑ፣ሁለት፣-ቀደም ሲል ስምምነቱን አጥብቀዉ የተቃወሙትን የሳዑዲ አረቢያ በተለይ ደግሞ የእስራኤልን ፖለቲከኞች ፍላጎት ማስታመም ስለነበረባቸዉ ቃላቸዉን ገቢር ለማድረግ ሲጥመለመሉ-ኢራን አዲስ መሪ መርጣ፣ አዲስ መንግሥት መሰረተች።
ከብዙ ዉጣ ዉረድ፣ ከወራት ማቅማማት በኋላ አሜሪካ በተዘዋዋሪ፣ የተቀሩት 5 ሐገራትና ኢራን በቀጥታ የሚካፈሉበት ድርድር እስካሁን ያመጣዉ ተጨባጭ ዉጤት የለም።ባይደን ስልጣን ከያዙ ወዲሕ ባለፈዉ ሳምንት ለአምስተኛ ጊዜ ቪየና ኦስትሪያ ላይ የቀጠለዉን ድርድር የመሩት የአዉሮጳ ሕብረት ምክትል የዉጪ ግንኙነት ኃላፊ ኤንሪክ ሞራ እንዳሉት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ስምምነቱን አፍርሰዉ በኢራን ላይ ዳግም ማቀብ ከጣሉ ወዲሕ ሁለቱ ሐገራት ከየያዙት አቋም የተለወጠ ነገርም የለም።
 «በቅርብ ወራት ዉስጥ የኢራን የኑክሌር መርሐ ግብር ጨምሯል።የዚያኑ ያክል ዩናይትድ ስቴትስ ያንኑ ማዕቀብ እንደጣለች ነዉ።በቀድሞዉ (የአሜሪካ) አስተዳደር ዘመን ከነበረዉ የተለወጠ ነገር የለም።የኑክሌሩን ሥጋት ለማስቀረት፣ለኢራን ሕዝብም ሲባል ሁኔታዉ JCPOAን ዳግም ነብስ ወደምንዘራበት አቅጣጫ ማምራት አለበት።»
ይሁንና ኢራን ስምምነቱን ወደነበረበት ለመመለስ ይረዳል በማለት ለተሰብሳቢዎች ያቀረበችዉ ሰነድ፣   የአዉሮጳ ሕብረቱ አደራዳሪ እንዳሉት በተሰብሳቢዎች ዘንድ ቀና ስሜት አሳድሯል።ድርድሩን የመቀጠል ፍላጊትም አለ- ይላሉ ኤንሪክ ሞራ።
«በጋራ ኮሚሽኑ (ስብሰባ) ዛሬ ያየሁት በጣም ቀና ስሜት አሳድሮብኛል።የመደራደር ፍላጎት በግልፅ ይታያል።አዲሱ የኢራን ተደራዳሪ ቡድን ያቀረበዉን ለማድመጥ በሁሉም መልዕክተኞች ዘንድ ከፍተኛ ፍላጎት አለ።በኢራኖችም በኩል JCPOA እንደገና ሥራ ላይ ለማዋል ሁነኛ ድርድር ለማድረግ ከልብ ለመጣር ፍላጎቱ አለ።ስለዚሕ በሚቀጥሉት ሳምንታት ጠቃሚ ጉዳዮችን እንሰራለን የሚል ቀና ስሜት አለኝ።»
የኢራኑ ዋና ተደራዳሪ ዓሊ ባጋሪ ካኒም  ድርድሩ ጠቃሚ ሐሳቦች እንደተነሱበት ገልፀዋል።ዉዝግቡ በድርድር እንዲፈታ መንግስታቸዉ የሚሻ መሆኑን አስታዉቀዋልም።ዩናይትድ ስቴትስ በድርድሩ ተሳታፊ አይደለችም።ይሁንና የዋይት ሐዉስ ቃል አቀባይ  ጄን ፕሳኪ በድርድሩ መሐልም ኢራንን ከመወንጀል አልታቀቡም።
«ኢራን አዲሱን ዙር ድርድር የጀመረችዉ፣ዓለም አቀፉ አዉቶሚክ ተቆጣጣሪ ድርጅት IAEA እንዳለዉ፣ ከአዲስ የኑክሌር ጠብ ጫሪነት ጋር ነዉ።(ኢራኖች) ባለፉት ወራት የቀነሱትን ትብብርና ግልፅነት ወደነበረበት ለመመለስ አሁንም ከIAEA ጋር አልተግባቡም።»
በድርድሩ የሚካፈሉት የ2015ቱን ስምምነት እስካሁን ያከበሩት  ብሪታንያ፣ፈረንሳይ፣ ሩሲያ፣ቻይና፣ ጀርመን፣ የአዉሮጳ ሕብረትና ኢራን ናቸዉ።ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ይግባቡ ይሆን? አናዉቅም።የሚታወቀዉ ድርድሩ በይደር ቀጠሮ ለጊዜዉ መቋረጡን ነዉ።ለዉጤት መብቃቱንም  ጊዜ ነዉ ነጋሪዉ።

USA I Washington I  Psaki
ምስል Susan Walsh/AP/picture alliance
Enrique Mora | Hoher Vertreter der Europäischen Union
ምስል Lisa Leutner/AP Photo/picture alliance
Österreich | Wien | Atomgespräche mit Iran | Ali Bagheri Kani
ምስል Joe Klamar/AFP/Getty Images
Österreich | Treffen zum iranischen Atomabkommen in Wien
ምስል EU Delegation in Vienna/REUTERS

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ