1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነሐሴ 10 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ነሐሴ 10 2013

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን በቶክዮ ኦሎምፒክ የ2020 ውድድር የተጠበቀውን ያህል ውጤት ባለማስመዝገቡ የስፖርት ኮሚሽን ትናንት ይቅርታ ጠይቋል። ለኢትዮጵያ ብቸኛውን የወርቅ እና ሌሎች ሜዳሊያዎችን ላስገኙ አራት አትሌቶች እና አሰልጣኞቻቸውም የገንዘብ እና የመሬት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። የአውሮጳ ሃገራት ታላላቅ ቡድኖች የሊግ ጨዋታዎች ተጀምሯል።

https://p.dw.com/p/3z3Ye
Äthiopien | Elias Shikur zur Teilnahme an den Olympischen Spielen
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን በቶክዮ ኦሎምፒክ የ2020 ውድድር የተጠበቀውን ያህል ውጤት ባለማስመዝገቡ የስፖርት ኮሚሽን ትናንት ይቅርታ ጠይቋል። ለኢትዮጵያ ብቸኛውን የወርቅ እና ሌሎች ሜዳሊያዎችን ላስገኙ አራት አትሌቶች እንዲሁም አሰልጣኞቻቸው የገንዘብ እና የመሬት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። የኦሎምፒክ ፉክክር መገባደዱን ተከትሎ የአውሮጳ ሃገራት ታላላቅ ቡድኖች የሊግ ጨዋታዎች ተጀምሯል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የማንቸስተሮቹ ፖል ፖግባ እና ብሩኖ ፈርናንዴዝ በተናበቡበት በዘንድሮው የመጀመሪያ የፕሬሚየር ሊግ ውድድር ድንቅ ብቃታቸውን ዐሣይተዋል። በጀርመን ቡንደስሊጋ ቦሩስያ ዶርትሙንድ፤ ሽቱትጋርት እና ሆፈንሀይም በሰፋ የግብ ልዩነት ተጋጣሚዎቻቸውን ሲረቱ፤ ባየርን ሙይንሽን ነጥብ ተጋርቷል። 

የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ቡድን ምንም እንኳን በአራት አትሌቶች ውጤት ቢያስመዘግብም፤ እንደ ቡድን ግን ዘንድሮ በርካቶችን እጅግ ያበሳጨ አሳዛኝ ውጤትን ይዞ አጠናቋል። 
ዶ/ር ጸጋዬ ደግነህ፦ በጀርመን ሀገር በአንድ የአውቶሞቢል ኩባንያ ውስጥ በብዛህነት ክፍል ሥራ አስኪያጅ ናቸው።  የተገኘው ውጤት እጅግ አሳዛኝ እንደነበር ይናገራሉ። ለቶኪዮ ወበቃማ እና ሞቃታማ የአየር ንብረት ተስማሚ ልምምድ መደረግ ነበረበትም ይላሉ።  

ጋዜጠኛ ዳዊት ቶሎሳ፦ የሪፖርተር ጋዜጣ የአማርኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋ ስፖርት አዘጋጅ ነው። የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን የዘንድሮ ውጤት ብዙዎችን ያበሳጨ እንደነበር በመገናኛ አውታሮች ኢትዮጵያውያን የሰጧቸው አጸፌታቸው ጠቋሚ መሆኑን ይገልጣል። ለውጤቱ መዳከም የተለያዩ ምክንያቶች ቢሰጡም በዋናነት ግን በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እና በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን መካከል ከውድድሩ አስቀድሞ የነበረው ውዝግብ ዋነኛ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች መጠቆማቸውን መታዘቡን ይገልጣል። 

ኢትዮጵያን ጨምሮ አፍሪቃ ውስጥ በተለያዩ የስፖርት እንቅስቃሴዎች ተሳታፊ የኾኑት ዶ/ር ጸጋዬ፦ በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እና በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራር መካከል ያለው ቅራኔ ለውጤቱ መዳከም ዋነኛ ሰበብ መሆኑን ጠቊመዋል። መፍትኄ ያሉትንም አካፍለዋል። 

ዶ/ር ጸጋዬ ደግነህ፦ የዓለም አቀፍ ጁጂትሱ ፌዴሬሽን የሥነ ምግባር ኮሚቴ ምክትል ፕሬዚደንት እና የዘላቂነት ኃላፊ ኾነው በማገልገል ላይም ይገኛሉ። በተለይ አዳዲስ የስፖርት ዘርፎች ላይ ትኩረት እንዲደረግ እና ጋሬጣዎች እንዲወገዱም ጠይቀዋል። ጋዜጠኛ ዳዊት ቶሎሳ ባደረገው ዳሰሳ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ላይ ውጤቱ ያበሳጫቸው በርካታ ሰዎች ተቃውሞ ማሰማታቸውን ገልጧል። ከዚያም ባሻገር የኦሎምፒክ ቡድኑ ወደ ሀገር ቤት ሲመለስ በአካል ተገኝተው ተቃውሟቸውን ያሰሙ ሰዎች መኖራቸውንም ጠቁሟል። 

Äthiopien | Elias Shikur zur Teilnahme an den Olympischen Spielen
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

አድማጮች አሁን ደግሞ የኦሎምፒክ ውጤታችን ጋር የተያያዘ ዘገባ ከሐዋሳ ደርሶናል። ወደዚያ እናቅና። የኢትዮጲያ ስፖርት ኮሚሽን በቶኪዮ ኦሎምፒክ የተገኘው ውጤት ሕዝቡ ሲጠብቀው በነበረው ልክ ባለመሆኑ ይቅርታ ጠይቋል።

Äthiopien | Elias Shikur zur Teilnahme an den Olympischen Spielen
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር ትናንት ምሽት በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው የአትሌቶች እና አሰልጣኞች የማበረታቻ ሽልማት ስነስረዓት ላይ «ከዝግጅታችንና ከለምድነው ድል አንፃር የተገኘው ውጤት ሕዝቡንም አኛንም ያዛዘነ ነው» ብለዋል። በትናንቱ የማበረታቻ ዝግጀት ላይ ሜዳልያ ላስገኙ አራቱ አትሌቶች እና አሰልጣኞች የገንዘብ እና የመሬት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። የሀዋሳው ወኪላችን ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ ተጨማሪ ዝርዝር ዘገባ ልኮልናል።

እግር ኳስ
በቀሩን ጥቂት ደቂቃዎች ስለ ፕሬሚየር ሊግ እና ቡንደስሊጋ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች እናካፍላችሁ። በሳምንቱ መጨረሻ በተከናወኑ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ዩናይትድ በመጀመሪያ ግጥሚያው ሊድስ ዩናይትድን ኦልድ ታራፎርድ ስታዲየም ውስጥ 5 ለ1 አንኮታኩቷል። በቅዳሜ ዕለት የከሰአት በኋላ ግጥሚያ የማንቸስተሮቹ ፖል ፖግባ እና ብሩኖ ፈርናንዴዝ እጅግ ተናበው ድንቅ ብቃታቸውን ዐሣይተዋል። በውድድሩ ብሩኖ ፈርናንዴዝ ለማንቸስተር ዩናይትድ የመጀመሪያ ሔትትሪኩን በመሥራት ሦስት ግቦችን ከመረብ አሳርፏል። ፖል ፖግባ በበኩሉ አራት ግብ መሆን የቻሉ ኳሶችን አመቻችቷል። ሌሎች ሁለት ግቦች በግሪንውድ እና ፍሬድ ነው የተቆጠሩት። ለሊድስ ዩናይትድ ብቸኛዋን ግብ ሉክ አይሊንግ ከመረብ አሳርፎ በባዶ ከመውጣት ቡድኑን ታድጓል። 

England Manchester United Jadon Sancho
ምስል Malcolm Bryce/imago images/Pro Sports Images

በመክፈቻው ግጥሚያ አርሰናል ወደ ፕሬሚየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ በተቀላቀለው ብሬንትፎርድ የ2 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል። ብራይተን በርንሌይን 2 ለ1 ሲያሸንፍ፤ ክሪስታል ፓላስ በቸልሲ 3 ለ0 እንዲሁም ሳውዝሐምፕተን በኤቨርተን 3 ለ1 ተሸንፈዋል። ሊቨርፑል ኖርዊች ሲቲን 3 ለ0፤ ዋትፎርድ አስቶን ቪላን 3 ለ2 እንዲሁም ላይስተር ሲቲ ዎቨርሀምተንን 1 ለo አሸንፈዋል። ትናንት ሴንት ጄምስ ፓርክ ስታዲየም ውስጥ በተከናወነው ግጥሚያ ኒውካስል በዌስት ሐም ዩናይትድ የ4 ለ2 ሽንፈት ገጥሞታል። ቶትንሀም በደጋፊው ፊት ቶትንሀም ሆትስፐር ስታዲየም ውስጥ ማንቸስተር ሲቲን 1 ለ0 አሸንፏል። 

በጀርመን እግር ኳስ ታሪክ እጅግ ስመገናናው የባየርን ሙይንሽን እና የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ አጥቂ ጌርድ ሙይለር በ75 ዓመቱ ትናንት ከዚህ ዓለም ተለይቷል። ጌርድ ሙይለር፦ በጀርመን እግር ኳስ በርካታ ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ክብረወሰን ባለቤት ነው። በ607 አጠቃላይ ጨዋታዎች 566 ግቦችን ለባየርን ሙይንሽን ማስቆጠር የቻለ ብርቱ አጥቂ ነው። በአንድ የቡንደስሊጋ የጨዋታ ዘመን ለባየርን ሙይንሽን 40 ግቦችን በማስቆጠርም ለረዥም ዓመታት ክብረወሰን ባለቤት ኾኖ ቆይቷል፤ ሮቤርት ሌቫንዶብስኪ 41 ግቦችን ከመረብ አሳርፎ ክብረወሰኑን እስኪረከብ ድረስ። ከዚያም ባሻገር በቡንደስሊጋ ታሪክ ለባየር ሙይንሽን የ365 ግቦችን በማስቆጠር አሁንም ድረስ ማንም ሊደርስበት ያልቻለው ክብረወሰን ባለቤት ነው። ባየርን ሙይንሽን  በዘንድሮ የቡንደስ ሊጋ መክፈቻ ግጥሚያ ዐርብ ዕለት ከቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል። በበነጋታው ባየር ሌቨርኩሰን እና ዑኒዬን ቤርሊን አንድ እኩል እንዲሁም አርሜኒያ ቢሌፌልድ እና ፍራይቡርግ ያለምንም ግብ አቻ ወጥተዋል። ሆፈንሀይም አውግስቡርግን 4 ለ0 ድል ሲያደርግ፤ ሽቱትጋርት ግሮይተር ፍዩርትስን 5 ለ0 አንኮታኩቷል። ቦሁም በቮልፍቡርግ፤ እንዲሁም ላይፕትሲሽ በማይንትስ 1 ለ0 ተሸንፈዋል። ኮልን ሔርታ ቤርሊንን 3 ለ1 ሲያሸንፍ፤ ቦሩስያ ዶርትሙንድ አይንትራኅት ፍራንክፉርትን በሰፋ 5 ለ2 ድል አድርጓል። 
ማንተጋፍቶት ስለሺ/ ሸዋንግዛው ወጋየሁ

Fußball Gerd Müller 1977
ምስል Sven Simon/dpa/picture alliance

አዜብ ታደሰ