1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኅዳር በሽታና አዲስ አበባ

ሐሙስ፣ ኅዳር 17 2013

ኅዳር በሽታ በሃገራችን ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የታየዉ የመጀመሪያው የበሽታው ምልክት በዓለም ላይ ከታየ ከአስር ወር በኋላ በህዳር ወር 1911 ዓ.ም  ነዉ። የእሰፓኒሽ ፍሉ ተብሎ የሚታወቀው ይህ ወረርሽኝ መነሻው ከወደ አሜሪካ እንደሆነ አንዳንድ መዛግብት ይጠቁማሉ። ከአዉሮጳ የተነሳ መሆኑን የሚናገሩም አሉ።  

https://p.dw.com/p/3lskd
Äthiopien Hidar Beshita | Addis Abeba im Smog
ምስል Yared Shumete

ከጎርጎረሳዉያኑ 1914 ዓ.ም እስከ 1918 ድረስ የዘለቀው የመጀመሪያው የዓለም ጦርነነት በሚሊዮን የሚቆጠር የዓለም ሕዝብን ቀጥፎ እንዳበቃ ዓለም ወረርሽኝ ተጠመደ። እስፓኒሽ ፍሉ ወይም በኢትዮጵያ የሚታወቅበት ስሙ የኅዳር በሽታ የኅዳር ወረርሽኝ ብዙ ሰዉን ጨረሰ። አንዳንድ የታሪክ ሰዎችእንደሚናገሩት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ወደ 10 ሺህ ሰዉ በኅዳር በሽታ ሕይወቱን አጥቶአል። የኅዳር በሽታ በሃገራችን ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የታየዉ የመጀመሪያው የበሽታው ምልክት በዓለም ላይ ከታየ ከአስር ወር በኋላ እንደነበረም አንዳንድ የታሪክ መዝገባት ያሳያሉ። ብላቴን ጌታ መርስዔ ሀዘን ወልደቂርቆስ የሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት ወረርሽኙ እስከ አርባ ሺህ ኢትዮጵያዊንን ለሞት ዳርጓል። በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ዘጠኝ ሺህ ያህል ዜጎች በበሽታው መሞታቸዉን አመልክተዋል።  በተለይም ህዳር 12 ቀን 1911 ዓ.ም በርካታ ኢትዮጵያዊያን የሞቱበት በመሆኑ ቀኑ የጽዳት ዘመቻ እንዲደረግ በአዋጅ ተነግሮ ስለነበር፣ ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ይህ ነገር እንደባህል ተወስዶ በየዓመቱ ህዳር 12 ቀን የጽዳት ዘመቻ መደረግ ጀመረ። እስከዛሬም ድረስ ኅዳር12 በኢትዮጵያ ከተሞች እና አካባቢዎች ሁሉ ሰዎች ቆሻሻን ሰብስበዉ ያቃጥላሉ። ኅዳር ታጠነም ይሉታል። ዘንድሮ በርካታ ኢትዮጵያዉያን በተለይ ወጣቶች በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መስከረም ሲጠባ በአደይ አበባ፤ በጥቅምት እኩሌታ እንድ ኩታ ብለዉ፤ ኩታን ደርበዉ ፎቶ ግራፍ ተቀያይረዋል፤ ከዝያም በኅዳርን አጥነዋል። ታሪኩ እንዴት ይሆን? ከኦክስፎርድ ዩንቨርስቲ ጋር በመተባበብር በወጣቶች ላይ ጥናት በማካሄድ ላይ ያለዉን «ያንግ ላይቭስ ፕሮጀክት»የሚመሩት የታዋቂዉ የታሪክ ተመራማሪ የሪቻርድ ፓንክረስት ልጅ አሉላ ፓንክረስት፤ አባታቸዉ ሪቻርድ ፓንክረስት በኢትዮጵያ ስለነበረዉ የኅዳር በሽታ ጉዳይ ጽፈዋል፤ ይህንንም አጫዉተዉናል። 
የእሰፓኒሽ ፍሉ ተብሎ የሚታወቀው ይህ ወረርሽኝ መነሻው ከወደ አሜሪካ እንደሆነ አንዳንድ መዛግብት ይጠቁማሉ። ከጎርጎረሳዉያኑ ጥር ወር 1918 ዓ.ም በአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ዋዜማ በጦርነቱ ለመካፈል የአሜሪካ ወታደሮች ወደ አውሮጳ ለመጓዝ ዝግጅት በሚያደርጉበት ወቅት ከተከሰተው ወረርሽኝ ጋር ይያያዛል ተብሎአል። በአሜሪካ ካንሳስ በሚገኘው የወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል የተቀሰቀሰ የሚባለዉ ወረርሻኝ በሦስት ቀናት ብቻ 45 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮች በወረርሽኙ መያዛቸዉ ተነግሮአል ከዝያም በመለጠቅ ነዉ አንደኛዉን የዓለም ጦርነት በማለት አትላንቲክን አቋርጠው አውሮጳን የረገጡ የአሜሪካ ወታደሮች በሸታውን አዉሮጳ ድረስ ይዘዉ መግባታቸዉ ተጠቅሶአል። ይሁንና አንዳንድ ጽሑፎች ወረርሽኙ ከአዉሮጳ ወደ አሜሪካ ማለፉን የሚጠቁሙ ጽሑፎችም አሉ። ታድያ በአዉሮጳ ወረርሽኝ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በፈረንሳይ ቢሆንም በአንደኛዉ ዓለም ጦርነት ምክንያት የፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ ይሆናል በሚል ስለበሽታዉ ለህዝብ ይፋ ሳይደረግ  ተደብቆ መቆየቱ እንዲሁ በታሪክ ተጽፎአል። ይሁንና እንደ ጎርጎረሳዉያኑ በህዳር ወር 1918 ዓ.ም በስፔን በሽታው ለመጀመሪያ ጊዜ ከታየ በኋላ እና ስፔን  በአንደኛዉ የዓለም ጦርነት ተካፋይ ባለመሆንዋ ሃገሪቱ ሳንሱር ወይም ቅድመ ምርመራ ስላልነበረ በሃገሪቱ  የበሽታው መስፋፋት ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን በማግኘቱ ወረርኙ እስፓኒሽ እንፍሉዌንዛ (ስፓኒሽ ፍሉ) የሚለውን ስያሜ ለማግኘት መብቃቱ ይነገራል። የዛሬ 102 ዓመት ኢትዮጵያ ዉስጥ በኅዳር በሽታ በሽዎች ማለቃቸዉን የነገረን አንጋፋዉ ጋዜጠኛ ንጉሴ አክሊሉ ነዉ። 
ጀርመን ኑረምበርግ ቅድስት ስላሴ ቤተክርስትያን ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት መሪ ጌታ ዳዊት ከፍያለዉም የኅዳር በሽታ ቆሻሻ ተቃጥሎ በጢሱ መጥፋቱ እምነት በመኖሩ ምናልባት ወደ ቤተ ክርስትያን የተወሰደ ቱፊት ሊሆን ይችላል ብለዋል። ዛሬ 102 በአፄ ሚኒሊክ ዘመነ መንግሥት የተከሰተዉ " የኅዳር በሽታ" የእስፓኝ እንፍሉየንዛ አልያም ወረርሽኙን ባቡር አመጣዉ ተብሎ ይታመን ስለነበር «የባቡር በሽታ» የሚል ስያሜም ተሰጥቶታል። አስከፊዉ ወረርሽኝ ከጠፋ በኋላ ኢትዮጵያ ላይ ኅዳር ይታጠናል። በየዓመቱ። 

ለዝግጅቱ መሳካት ቃለ ምልልስ የሰጡንን በማመስገን ሙሉ መሰናዶዉን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን ተችነዉ እንዲከታተሉ እንጋብዛለን !

 

 
አዜብ ታደሰ 
ማንተጋፍቶት ስለሺ