1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኅዳር 21 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ኅዳር 21 2013

የአርጀንቲናዊው የኳስ ጠቢብ ሞት ሰበብ ላይ ፖሊስ ምርመራ ጀምሯል። የአውሮጳ ሃገራት ዋና ዋና የእግር ኳስ መረጃዎችንም አካተናል። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ትናንት አንድ አሽከርካሪ ከሚንቀለቀል እሳት ውስጥ መጠነኛ ጉዳት ብቻ ደርሶበት ወጥቷል።  

https://p.dw.com/p/3m2Px
Formel 1 Grand Prix Bahrain | Feuer zerstört Rennwagen
ምስል HochZwei/imago images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በዘመናት ድንገት ብቅ ብለው እንደ ተወርዋሪ ከዋክብት ድንገት ከተሰወሩ የዓለማችን ድንቅ ሰዎች አንዱ የኾነው አርማንዶ ዲያጎ ማራዶና አሟሟት ምርምራ እየተደረገበት ነው። የእግር ኳስ ጠቢብ የነበረው እና በ60 ዓመቱ ባለፈው ሳምንት ከዚህ ዓለም የተለየው ማራዶና የረዥም ጊዜ የግል ሐኪም ላይ ምርመራ ተጀምሯል።  በፎርሙላ አንድ እጅግ አስደንጋጭ የተሽከርካሪ አደጋ ሮማን ግሮዦ እንደ እቶን ከሚንቀለቀለው ተሽከርካሪው ውስጥ በቀላል አደጋ ሕይወቱ መትረፏ በርካቶችን አስደምሟል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቶትንሃም እና ሊቨርፑል በግብ ክፍያ ልዩነት ብቻ የደረጃ ሰንጠረዡ ቀዳሚ ኾነዋል። 

ፕሬሚየ ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየ ሊግ ትናንት ከቸልሲ ጋር ያለምንም ግብ አቻ የተለያየው ቶትንሀም በደረጃ ሰንጠረዡ መሪ መኾን ችሏል።  ዛሬ ማምሻውን ተስተካካይ ግጥሚያውን ከፉልሃም ጋር የሚያደርገው ላይስተር ሲቲ ካሸነፈ ግን የመሪነቱን ስፍራ በአንድ ነጥብ በልጦ ይረከባል። ፉልሃም እስካሁን ባደረጋቸው ግጥሚያዎች አራት ነጥብ ብቻ ይዞ በደረጃ ሰንጠረዡ ወራጅ ቃጣና 19ኛ ላይ የሚገኝ ደካማ ቡድን ነው። ዛሬ ማታ ከላይስተር ጨዋታ በኋላ ዌስትሀም ዩናይትድ ከአስቶን ቪላ ጋር ይጋጠማል።

Fussball Premier League l Aston Villa vs Liverpool
ምስል Rui Vieira/Reuters

ቅዳሜ ዕለት ከብራይተን ጋር አንድ እኩል የወጣው ሊቨርፑል በግብ ክፍያ ልዩነት ብቻ በቶትንሃም ተበልጦ ኹለተኛ ደረጃውን ይዟል። የሊቨርፑሉ ቲያጎ አልካንታራ ወደ ቡድኑ ለመመለስ ሳምንታት እንደሚፈጅበት መነገሩ አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕን ሳያበሳጫቸው አልቀረም።  አሰልጣኙ ለተጨዋቾች ጉዳት ባለፈው ወር ከኤቨርተን ጋር ያደረጉት ግጥሚያ ዋነኛ ሰበብ መኾኑን ዛሬ በብስጭት ተናግረዋል። የሊቨርፑል ዋነና ተከላካይ ቪርጂል ቫን ጂክ በዚሁ ግጥሚያ ጉልበቱ ላይ ከደረሰበት ጉዳት ለማገገም ገና በርካታ ጊዜያት ያስፈልጉታል።

ቸልሲ ትናንት ነጥብ መጣሉ በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ካሉት ቡድኖች ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ የነበረውን ዕድል አምክኗል። 18 ነጥብ ይዞ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሳውዝሀምፕተን እና ዎልቨርሀምተን በ17 እንዲሁም ኤቨርተን በ16 ነጥብ እስከ 7ኛ ደረጃ ተከታትለው ይገኛሉ። ስምንተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ እንደ ኤቨርተን ኹሉ 16 ነጥብ አለው። የፊታችን ቅዳሜ ከዌስትሀም ዩናይትድ ጋር የሚያደርገው አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ግን ይቀረዋል። ኹለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ከሚቀሩት አስቶን ቪላ ዝቅ ብሎ በ10ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ አንድ ተስተካካይ ጨዋታውን ቅዳሜ ከሰአት ከፉልሃም ጋር ያከናውናል።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ግጥሚያ ዐርብ ዕለት ሽቱትጋርትን 3 ለ1 ያሸነፈው ባየር ሙይንሽን በ22 ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡን ይመራል። የእዛኑ ዕለት አርሚኒያ ቢሌፌልድን 2 ለ 1 ያሸነፈው ላይፕትሲሽ 20 ነጥብ ይዞ ኹለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ባየር ሌቨርኩሰን ቅዳሜ ዕለት ባደረገው ግጥሚያ ከኼርታ ቤርሊን ጋር ያለምንም ግብ ቢለያይም 19 ነጥብ ይዞ ደረጃው ሦስተኛ ነው። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በቡንደስሊጋው ከ18 ቡድኖች 17ኛ ደረጃ ላይ በነበረው ኮሎኝ የ2 ለ1 አስደንጋጭ ሽንፈት ገጥሞት የኹለተኛ ደረጃውን አስረክቧል። 18 ነጥብ ይዞ አራተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ኮሎኝ እንደምንም ተንፏቆ ከወራጅ ቃጣናው በመውጣት 15ኛ ደረጃ ላይ መስፈር ችሏል። ማይንትስ፣ አርሜኒያ ቢሌፌልድ እና መከረኛው ሻልከ ከ16ኛ እስከ 18ኛ ደረጃ ከታች ተደርድረዋል።

Bundesliga I Borussia Dortmund v Bayern München
ምስል Leon Kuegeler/Pool/REUTERS

ሻምፒዮስን ሊግ

የሻምፒዮስን ሊግ አምስተኛ ዙር ፍልሚያ ነገ እና ከነገ በስትያ ሲከናወን አራት የጀርመን ቡድኖች ከጠንካራ ተጋጣሚዎች ጋር ይገናኛሉ። በነገው ዕለት የጀርመኑ ባየር ሙይንሽን ከስፔኑ ብርቱ ቡድን አትሌቲኮ ማድሪድ፤ የጣሊያኑ ኢንተር ሚላን ከሌላኛው የጀርመን ቡድን ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ጋር ይጋጠማሉ። ሌለኞቹ የጀርመን ኃያል ቡድኖች ላይፕትሲሽ እና ቦሩስያ ዶርትሙንድም የቱርኩ ባስካሺር እና የጣሊያኑ ላትሲዮን የሚገጥሙት ረቡዕ ማታ ነው።

ነገ በሚከናወኑ የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች፦ የእንግሊዙ ባለድል ሊቨርፑል ከሆላንዱ አያክስ አምስተርዳም ጋር የሚያደርጉት ግጥሚያ በበርካቶች የሚጠበቅ ነው። የስፔኑ ሪያል ማድሪድ ከዩክሬኑ ሻካታር ዶኒዬትስክ፤ የራሺያው ሎኮሞቲቭ ሞስኮ ከኦስትሪያው ዛልስቡርግ፤ የፖርቹጋሉ ፖርቶ ከእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ፤የፈረንሳዩ ማርሴ ከግሪኩ ፒሬውስ እንዲሁም የጣሊያኑ አታላንታ ቤርጋሞ ከዴንማርኩ ሚድቺላንድ ጋር ይጋጠማሉ።

ረቡዕ ዕለት በሚደረጉ የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች ደግሞ፦ የእንግሊዙ ማንቸስተር ዩናይትድ ከፈረንሳዩ ፓሪ ሶንጄርማ፤ የስፔኑ ባርሴሎና ከሀንጋሪው ፌሬንክባሮስ፤ ሌላኛው የስፔን ጠንካራ ቡድን ሴቪያ ከእንግሊዙ ቸልሲ፤ የሚያደርጓቸው ፉክክሮች ይጠበቃሉ። የራሺያው ዜኒት እና የቤልጂየሙ ክሉብ ብሩዥ፤ የጣሊያኑ ጁቬንቱስ እና የዩክሬኑ ዲናሞ ኪዬቭ፤ እንዲሁም የፈረንሳዩ ሬኔ እና የራሺያው ክራስኖዳር ግጥሚያዎችም ረቡዕ ማታ በተመሳሳይ ሰአት የሚከናወኑ ናቸው።

በሻምፒዮንስ ሊግ አምስተኛ ዙር ግጥሚያ ባየር ሙይንሽን በ12 ነጥብ አትሌቲኮ ማድሪስ፣ ሎኮሞቲቭ ሞስኮ እና ዛልስቡርግ ያሉበትን ምድብ «ሀ»ይመራል። አትሌቲኮ ማድሪድ በ5 ነጥብ ይከተላል። ሎኮሞቲቭ ሞስኮ 3 እንዲሁም ዛልስቡርግ 1 ነጥብ ይዘው በምድቡ መጨረሻ ላይ ይገኛሉ።

ምድብ «ለ»ን ሌላኛው የጀርመን ቡድን ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ በ8 ነጥብ ይመራል። ሪያል ማድሪድ በ7 ነጥብ ይከተላል። ሻካታር ዶኒኒዬትስክ እና ኢንተር ሚላን 4 እና 2 ነጥብ ይዘው ከታች ይገናኛሉ።

Champions League Bayern München - Paris Saint-Germain Pokal
ምስል picture-alliance/dpa/M. Lopes

የምድብ «ሐ» መሪ ደግሞ ማንቸስተር ሲቲ ነው፤ 12 ነጥብ አለው። ፖርቶ በ9፣ ፒሬውስ በ3 ይከተላሉ። ማርሴ ያለምንም ነጥብ የምድቡ መጨረሻ ላይ ተዘርግቷል። የምድብ «መ» መሪ ሊቨርፑል 9 ነጥብ አለው፤ አያክስ እና ቤርጋሞ በ7 ነጥብ ግን በግብ ክፍያ ሊቨርፑልን ይከተሉታል።  ምንም ነጥብ የሌለው ሚትድቺላንድ የምድቡ ግርጌ ላይ ይገኛል።

ቸልሲ የምድብ «ሠ» መሪ ነው፤ ከሴቪያ ጋር እኩል 10 ነጥብ ይዞ ግን በግብ ክፍያ ይበልጣል። ሬኔ እና ክራንስዶር እያንዳንዳቸው አንድ ነጥብ አላቸው። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ9 ነጥብ ምድብ «ረ»ን ይመራል።

ላትሲዮ በ9 ይከተለዋል። ክሉብ ብሩጅ እና ዜኒት 4 እና 1 ነጥብ ይዘው ከምድቡ ታች ይገኛሉ። በምድብ «ሰ» መሪው ማንቸስተር ዩናይትድ 9 ነጥብ አለው። ፓሪ ሳንጃርሞ እና ላይፕትሲሽ እኩል 6 ነጥብ ይዘው በግብ ክፍያ ይለያያሉ። ባስካሺር 3 ነጥብ ይዞ የምድቡ መጨረሻ ላይ ይገኛል።

የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር ዛሬ ባከናወነው የስልክ ስብሰባ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ዮኣኺም ሎይቭ እስከሚቀጥለው የጎርጎሪዮሱ አዲስ ዓመት የቡድኑ አሰልጣኝ ኾነው እንደሚቆዪ ይፋ አድርጓል። ምንም እንኳን የጀርመን ቡድን በቅርቡ በስፔን አቻው 6 ለ0 በኾነ ሽንፈት ጉድ ቢኾንም አሰልጣኙ ግን ወዲያው ከመሰናበት ተርፈዋል። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ካለፈው የዓለም ዋንጫ አንስቶ ውጤቱ ማሽቆልቆሉ የበርካቶች መነጋገሪያ ኾኖ ቆይቷል። እስከሚቀጥለው የአውሮጳ ዋንጫ ድረስ አሰልጣኝ ዮኣኺም ሎይቭ ቡድኑ ከገባበት ቀውስ እንዲታደጉት ግን ጊዜ ተሰጥቷቸዋል። ምናልባትም ያን የማያሳኩ ከኾነ ግን የዮኣኺም ሎይቭ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የረዥም ጊዜ አሰልጣኝነት የሚያበቃ ይመስላል።

Champions League | FC Bayern München v SC Neapel 1989 - Diego Maradona
ምስል Rauchensteiner/Augenklick/picture alliance

አርጀንቲናዊው የኳስ ጠቢብ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና በ60 ዓመቱ ከዚህ ዓለም የመለየቱ ነገር ሌላ መዘዝ ይዞ ብቅ ብሏል። የማራዶና የግል ሐኪም ሊዮፖድሎ ሉኩዌ ፍሎሰን ከማራዶና ሞት ጋር በተያያዘ ምርመራ ተከፍቶባቸዋል። የማራዶና ሦስት ሴት ልጆች ሐኪሙ ለማራዶና ምን አይነት መድሐኒት ሲሰጡ እንደነበ ይመርመርልን ብለዋል። የቦነስ አይረስ አቃቤ ሕግ የሐኪም ሊዮፖድሎ ሉኩዌ ፍሎሰን ጽ/ቤት እሁድ እለት በርብሯል። «ውስብስብ ኅመም ለነበረበት ታማሚዬ የቻልኩትን ኹሉ ለማድረግ ተጣጥሬያለሁ» ያሉት የማራዶና የግል ሐኪም ፍርድ ቤት እንደሚቆሙ ግን እየተነገረ ነው። የጭንቅላት ቀዶ ጥገና ሕክምና ጠበብቱ ሐኪም ማራዶና ለመሞቱት የሠሩት ስህተት ሳይኖር አይቀርም ተብሏል። ረቡዕ ዕለት በ60 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ማራዶናን የግል ሐኪሙ ከጥቂት ቀናት በፊት የአዕምሮ ቀዶ ጥገና አድርገውለት ነበር።

ፈረንሳይ ላይ ከ18 ዓመት በፊት በዓለም ዋንጫ መክፈቻ ግጥሚያ ብቸኛዋን ግብ በማስቆጠር ኩም ያደረገው ሴኔጋላዊው አማካይ ፓፓ ቦባ ዲዮ ትናንት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ፊፋ በ42 ዓመቱ ሴኔጋላዊ አማካይ ሞት ሐዘኑን ገልጧል።  ፓፓ ቀድሞ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ የነበረችው ፈረንሳይ ላይ እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር በ2002 የዓለም ዋንጫ የመክፈቻ ግጥሚያ ያስቆጠራት ብቸኛ ግብ ዛሬም ድረስ በበርካታ ኳስ አፍቃሪያን ዘንድ ስትታወስ ትኖራለች። ፓፓ ቦባ ዲዮፕ በሕይወት ዘመኑ 63 ጊዜያት ለሀገሩ ተሰልፎ 11 ግቦችን ከመረብ ማሳረፍ የቻለ አማካይ ነበር።

ፎርሙላ አንድ

Formel 1 | Grand Prix Bahrain | Hamilton und Verstappen
ምስል Giuseppe Cacace/REUTERS

እንደ እቶን ከሚንቀለቀለው እሳት ውስጥ በሕይወት ተርፎ ይወጣል ማለት እጅግ ይከብድ ነበር። የፎርሙላ አንድ አሽከርካሪው ሮማን ግሮዦ ትናንት ያሽከረክራት የነበረችው መኪና ከፍጥነት ጋር የመላተም አደጋ ከደረሰባት በኋላ ለሁለት ተገምሳ አልቆመችም። በአቅራቢያው ከሚገኘው ማገኛ ብረት ጋር ተላትማ ጋየች፤ በሰከንድ ውስጥም በነበልባ ተዋጠች። ከግማሽ ደቂቃ በኋላ ግን በርካቶችን እፎይ ያስባለ ክስተት ታየ። አሽከርካሪው ሮማን ግሮዦ  ከነበልባሉ ውስጥ ዘሎ ወጣ። እጆቹ ለመለብለባቸው ለነፍስ አድን ወደምትንቀለቀለው ተሽከርካሪ በፍጥነት የደረሱት የፎርሙላ አንድ ሠራተኞች ደግፈው ሲያወጡት ተስተውሏል። እጆቹ ላይ ብቻ ቀላል የመለብለብ አደጋ ደርሶበት ከመቃጠል በተአምር ተርፏል። የለበሰው ልዩ እሳት ተከላካይ ልብስ እና አስተማማኝ የራስ ቁር አካሉ እንዳይቃጠል ረድቶታል። ሮማን ግሮዦ ሐኪም ቤት አልጋው ላይ ኾኖ ተዘረጋግተው በፋሻ የተጠቀለሉ ዐሥሩንም ጣቶቹን እያንቀሳቀሰ ስለደህንነቱ በፈገግታ ቀጣዩን ብሏል፦

«ሠላም ሁላችሁም እንዴት አላችሁ? ደህና ነኝ፤ ምንም አልል ለማለት ነው። ለመልእክታችሁ በጣም አመሰግናለሁ።»

ሮማን ግሮዦ ከሚንቀለቀለው እሳት ይተርፋል ብሎ የጠበቀ ማንም አልነበረም። የሳምንቱ አስደናቂ የስፖርት ክስተት ኾኖ አልፏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ