1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቻድ ምርጫና ኮቪድ -19 ያባባሰው የመብት ጥሰት በዚምባብዌ 

ቅዳሜ፣ የካቲት 6 2013

በመካከለኛው አፍሪቃ ሰሜን ምዕራብ ክፍል የምትገኘው ቻድ በመጭው ሚያዚያ የምታካሂደው ምርጫና ችግሮቹ እንዲሁም በዚምባብዌ በኮሮና ወረርሽኝ ሰበብ የተቃውሞ ድምጾችን አፈናና የመብት ጥሰቶች እየጨመሩ መምጣት የዛሬው የትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅት የተመለከታቸው ጉዳዮች ናቸው። 

https://p.dw.com/p/3pK5i
Tschad Präsident Idriss Deby Itno
ምስል Präsidentschaft von Tschad

የቻድ ምርጫና ኮቪድ -19 ያባባሰው የመብት ጥሰት በዚምባብዌ 

የቻድ ፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቢ ከጎርጎሪያኑ 1990 ዓ/ም ጀምሮ ሀገሪቱን በመምራት ከ30 ዓመታት በላይ በሥልጣን ቆይተዋል።ያም ሆኖ የ68 አመቱ አዛውንት በመጭው ሚያዚያ 11 ቀን ይካሄዳል ተብሎ በታቀደው ምርጫም ለ 6 ኛ ጊዜ በመወዳደር ስልጣናቸውን ማራዘም ይፈልጋሉ። ይህንን የፕሬዚዳንቱን ውሳኔ ተከትሎም ዋና ከተማውን ንዲያሜናን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ ብዙዎች ተቃውሟቸውን በመግለፅ ላይ ናቸው።ይህም በመልካም አስተዳደር እጦትና በነዳጅ ዘይት ዋጋ ማሽቆልቆል ሳቢያ ድህነት ለተባባሰባት ለወደብ አልባዋ አፍሪካዊት ሀገር ቻድ፤ሌላ ፈተና ሆኗል ፡፡ 
በሀገሪቱ በሳምንቱ መጨረሻ በተደረጉ የተቃዉሞ ሰልፎች ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ በመጠቀም ብዙዎችን ለጉዳት ከ 50 በላይ ሰልፈኞችን ደግሞ ለዕስራት ዳርጓል ፡፡ፕሬዝዳንት ዴቢ ተቃዋሚዎቻቸውን ዝም ለማሰኘት ሰልፎችን በመከልከል፣ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን በማገድና የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የሚታወቁ ሲሆን፤ በጎርጎሪያኑ 2018ም ህገ-መንግስታዊ ለውጥ ከተደረገ በኋላ ከ 10 ወራት በላይ በይነመረብ እንዲቋረጥ አድርገዋል። 
የሰሞኑን ተቃውሞ የጠሩት ታዋቂው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ሱሴስ ማስራም ለደህንነታቸው በመስጋት እሳቸውና ሌሎች 10 የፓርቲው አባላት መጨረሻቸው በአሜሪካ ኤምባሲ መጠጊያ መፈለግ ሆኗል።በመሆኑም ማስሪ በቻድ የመሰረታዊ መብቶች ጥሰት እንዲቆምና የህዝቡ መብት እንዲከበር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እገዛ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። 
«ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፣ እንደ ፈረንሳይ ፣ ጀርመን ፣ የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ያሉ ሀገሮች የቻድ ህዝብ በእነዚህ ትልልቅ የዓለም ሀገራት ውስጥ ያሉ ህዝቦች ያላቸውን ተመሳሳይ መብት እንዲኖራቸው እንዲያግዙ እንጠይቃለን ።ይህም በሰላማዊ መንገድ የመሰብሰብ መብት ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግና አንድ ሰው የሚቀርበውና የሚወደው ስልጣን እንዲይዝ በሰላማዊ መንገድ የመናገር መብት ነው።» 
የ 38 ዓመቱ ማስራ በመጭው ሚያዝያ በሚካሄደው ምርጫ መወዳደር አይችሉም። ምክንያቱም ለመወዳደር የሚፈለገው ዕድሜ ቢያንስ 40 መሆን አለበት። ይልቁንም 16 የተቃዋሚ ፓርቲዎች መከፋፈልን ለማስወገድ በጋራ ቲዎፍሊ ቦንጎሮ የተባሉ የ55 ዓመት ዕጩ ተወዳዳሪ ለማቅረብ ተስማምተዋል።የቻዱ የፖለቲካ ተንታኝ ሮላንድ ማርቻል ግን ህብረቱ ለብዙ ጊዜ ይቆያል የሚል እምነት የላቸውም። 
«ይህ የአንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲ እጩዎች፤ የአንድ ተወዳዳሪ ስልት ቀደም ሲል የነበሩትን ባህላዊ ክፍፍሎች ለማሸነፍ የሚደረግ ሙከራ ነው። ቢሆንም ግን ምንም ነገር ይለውጣል የሚል እምነት የለኝም። መጨረሻም ላይ ኢድሪስ ዴቢ እና መንግስታቸው የይስሙላ ተቃዋሚ ቡድኖችን በመፍጠር በዚያ መንገድ መከፋፈልን ለማባባስ ዝግጁ ናቸው። ስለዚህ ወደ ምርጫው ስንቃረብ ብዙ እጩዎች ይኖራሉ ብዬ አስባለሁ።» 
የቀድሞው የጦር አዛዥ ኢድሪስ ዴቢ ወደ ስልጣን የመጡት በ1990 ዓም አምባገነኑን ሂሴኒ ሀብሬን በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን ባስወገደው አመፅ ነበር።በጎርጎሪያኑ 1996 የቻድ የመጀመሪያዎቹን የነፃነት ምርጫዎች ያሸነፉ ሲሆን፤ በ 2001 ዓ/ም እንደገና ተመርጠዋል ፡፡ 
በጎርጎሪያኑ 2005 በተካሄደው ህዝበ-ውሳኔ ህገ-መንግስቱ ሁለት-ጊዜ የመመረጥ ገደብን በማንሳቱ ዴቢ በ 2006 ፣ በ 2011 እና በ 2016 ዓ/ም የፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎችን በማሸነፍ ስልጣናቸውን ቀጠሉ ፡፡ 
ቻድ በ 2018 ዓ/ም የፕሬዚዳንቱን ስልጣን ከአምስት ወደ ስድስት ዓመት በማሳደግ ህገ-መንግስቷን እንደገና አሻሽላለች ፡፡ ምንም እንኳን አዲሱ ህገ-መንግስት የሁለት-ጊዜ ገደብን እንደገና እንዲመለስ ቢደነግግም ይህ ወደኋላ ተመልሶ ተግባራዊ አይሆንም ተብሏል። ይህም በንድፈ-ሀሳብ ደረጃ እድሜ ከሰጣቸው ፕሬዚዳንት ዴቢ እስከ 2033 ዓ/ም ድረስ በፕሬዚዳንትነት እንዲቆዩ ያደርጋቸዋል ነው የተባለው፡፡ 
በመካከለኛው አፍሪቃ ሰሜን ምዕራብ ክፍል የምትገኘው ቻድ ነፃነቷን ከፈረንሳይ ያገኘችው በጎርጎሪያኑ 1960 ዓ/ም ነበር። ቻድ፣ብዙ ድፍድፍ የነዳጅ ዘይት ያላት ሀገር ብትሆንም፤በዓለም ላይ በጣም ድሃ ከሆኑት ሀገሮች አንዷ ነች። ሀገሪቱ በዓለም የምግብ ፕሮግራም መረጃ መሠረት ከ15.8 ሚሊዮን ህዝቧ ውስጥ ሁለት ሦስተኛው በከፋ ድህነት ውስጥ ይኖራል ፡፡ 
ኮቪድ -19 ያባባሰው የመብት ጥሰት በዚምባብዌ 
የዜጎቻቸውን መብት በማፈን የሚወቀሱት የአፍሪቃ መንግስታት በኮሮና ወረርሽኝ ወቅትም ተባብሶ መቀጠሉን የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እየገለፁ ነው። 
ሂውማን ራይትስ ዎች የተባለው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ያለፈው ሀሙስ የኮሮና ወረርሽኝን የዜጎቻቸውን መብት ለማፈን እየተጠቀሙ ነው ሲል፤ በ23 የአፍሪካ መንግስታት መግለጫ አውጥቷል።ከነዚህም ውስጥ የዚምባብዌ መንግሥት ይገኝበታል ። 
የዝምባብዌ ጋዜጠኛ ፍራንክ ቺኮዎር ባለፈው ዓመት ከታሰሩት ውስጥ አንዱ ነው። ጋዜጠኛው በቁጥጥር ስር የዋለው በጸጥታ ኃይሎች ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል የተባሉ አንዳንድ የተቃዋሚ አባላትን በወረርሽኙ ሳቢያ የእንቅስቃሴ ገደብ በተጣለበት ወቅት ቃለ መጠይቅ በማድረጉ ነበር ፡፡ 
ጋዜጠኛው እንደሚለው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምንጋግዋ የቀድሞውን ፕሬዚዳንት የሮበርት ሙጋቤን መንገድ እየተከተሉ ነው። 
«በመጀመሪያ ደረጃ ፖሊስ እኛን ለማሰር ምንም ምክንያት አልነበረውም ፡፡ በዚምባብዌ የመገናኛ ብዙሃን ነፃ አይደሉም። ፕሬዝዳንት ምናንጋግዋ በጎርጎሪያኑ 2017 ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሃላ ሲፈጽሙ ሁኔታው በተሻለ መልኩ ይለወጣል ብዬ አሰብ ነበር።ነገር ግን አሁንም ቢሆን ሙጋቤ ያደርጉ የነበረውን ነው እያደረጉ ያሉት።የምናንጋግዋ መንግስት በሀገሪቱ የፕሬስ ነፃነት እንዲከበር የበለጠ እንዲሰራ እጠብቃለሁ።» 
ጋዜጠኛው ቺኮዎር ከደረሰባቸው ስቃይ በማገገም ላይ ሳሉ በሚታከሙበት ክሊኒክ ቃለ መጠይቅ ካደረገላቸው ሶስት የተቃዋሚ አባላት መካከል ሲሲሊያ ቺምቢሪን አንዷ ነች። 
ችምቤሪ እንደምትለው በእንቅስቃሴ ገደቡ ወቅት የደመወዝ ክፍያ በመጠየቋ ታስራለች። በደልም ደርሶባታል። ስለሆነም መንግስት ኮቪድ 19ን የተቃውሞ ድምፅ ለማፈን እየተጠቀበት ነው ባይ ነች። 
«ህዝባቸውን የሚጠብቁ መንግስታት ለህዝባቸው ተጨባጭ የሆኑ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው።ነገር ግን መንግስታችን በእሱ ላይ ዝም ያለ ይመስላል። በቋሚነት የሚሰሩት ብቸኛውና የቀጠለው ነገር በሙስና መዘፈቅ፣ ከህዝብ መስረቅና ህዝብን መጉዳት ነው።እያንዳንዱን ድምፅ ለማፈን ኮቪድ 19ን እየተጠቀሙ ነው። የሚያስሩህ የተጣሉ የእንቅስቃሴ ገደቦችን በመጣስህ አይደለም። ስለ ፖሊስ ጭካኔ በትዊተር ላይ በመፃፍህ ነው ፡፡ » 
እንደ የሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባ እንደ ቺኮዎር ያሉ ጋዜጠኞች መታሰራቸው የዚምባብዌ መንግስት የፕሬስ እና የመሰብሰብ ነፃነትን ለመጣሱ ማሳያዎች ናቸው። 
በሂዩማን ራይትስ ዎች የቀውስ እና የግጭት ክል ተባባሪ ዳይሬክተር ጌሪ ሲምፕሰን «ኮቪድ -19 የነፃ ንግግር መብት መጣስን አባብሷል።»በሚል ከጀኔቫ ባወጡት ዘገባ ፤የምንጋግዋ መንግስት በኮሮና ወረርሽኝ መከላከል ሰበብ የሰዎችን መብት ስለመጣሱ የተጠቀሱት የጥቂት ጋዜጠኞችና የመብት ተሟጋቶች በደል ብቸኛ ጉዳይ አይደለም ይላሉ።በዚምባብዌ የኮቪድ-19 የእንቅስቃሴ ገደብ ከተጣለ ወዲህ በፍተሻ ጣቢያዎች ባለሥልጣናት በርካታ ጋዜጠኛችን እንደደበደቡ መረጃ መያዛቸውንም ገልፀዋል።በተጨማሪም አንድ ጋዜጠኛ ስለ ኮቪድ-19 በመዘቡ ብቻ ለዘጠኝ ሳምንታት እንደታሰረ እንዲሁም ያለፈው በመጋቢት ወር ኮቪድ-19ን ጨምሮ የሐሰት ዜና ማሰራጨት እስከ 20 ዓመት እስራት የሚያስቀጣ አዲስ ሕግ እንዳወጣም አስረድተዋል። 
እነዚህን መሰል የመብት ጥሰቶችን ታዲያ ከሃያ በላይ በሆኑ የአፍሪቃ ሀገራት መመዝገባቸውን ገልፀዋል። 
«እነዚህን መሰል በደሎች በአፍሪካ ቢያንስ በ 23 ሀገራት መዝግበናል። ለምሳሌ በኡጋንዳ የፀጥታ ኃይሎች ኮቪድ-19 ጥሰዋል በሚል ታስረዋል።የፕሬዚዳንታዊ እጩ መታሰርን በመቃወም ላይ የነበሩ 54 ሰልፈኞች የተገደሉ ሲሆን ቢያንስ 45 የሚሆኑት ደግሞ ቆስለዋል ፡፡ በተጨማሪም በማላዊ በጎርጎሪያኑ ጥር 22 ቀን 2020 ቢያንስ ሰባት የፖሊስ መኮንኖች የኮቪድ-19 ደንቦችን ሲያስፈጽሙ ፎቶግራፍ ለማንሳት ፈቃድ ከጠየቃቸው በኋላ በጋዜጠኛው ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል።» 
የዚምባብዌ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሀላፊ ኤላስታ ሙጉዲ ሂውማን ራይትስ ወችን ባወጣው ዘገባ አስተያየት ባይሰጡም ሀገሪቱ የእንቅስቃሴ ገደብ ከጀመረች ካለፈው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ ድርጅታቸው በርካታ የመብት ጥሰት ሪፖርቶች እንደደረሱት ግን አረጋግጠዋል። 

Simbabwe Massaker
ምስል Zinyange Auntony/AFP/Getty Images
Simbabwe Corona-Pandemie | Lockdown geplant
ምስል Wilfred Kajese/AA/picture alliance
Tschad Präsident Idriss Deby Itno
ምስል Präsidentschaft von Tschad
Tschad Präsident Idriss Deby Itno
ምስል Präsidentschaft von Tschad


ፀሀይ ጫኔ 
ነጋሽ መሀመድ