1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ምርጫ፣ሒደትና ዉዝግቡ

ረቡዕ፣ ጳጉሜን 4 2012

የፌደሬሽን ምክር ቤት ባለፈዉ ቅዳሜ ምርጫዉን እና ዉጤቱን የማይፀና እና እንደተደረገ የማይቆጠር ብሎታል።ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድም ትናንት «የጨረቃ-ምርጫ» በማለት ሕገወጥነቱን ተናግረዋል።ይሁንና የፌደሬሽን ምክር ቤትም ሆነ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሕግ ለማስከበር የሚወስዱት ርምጃም ይኑር አይኑር ያሉት ነገር የለም።

https://p.dw.com/p/3iEcz
Äthiopien Tigray | Wahlen | Stimmabgabe
ምስል DW/M.H. Silase

ምርጫ በመቀሌ

የትግራይ ሕዝብ የወደፊት የክልል ምክር ቤት እንደራሴዎቹን ለመምረጥ ዛሬ ድምፁን ሲሰጥ ነዉ የዋለዉ።ምርጫዉን የፌደራዊዉ መንግስት «ሕገ-ወጥ» ቢለዉም ከ2.7 ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ድምፁን ለመስጠት ተመዝግቧል። 190 መቀመጫዎች ላሉት ክልላዊ ምክር ቤት የትግራይ ገዢ ፓርቲ ሕወሓትን ጨምሮ የአምስት ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮችና 4 የግል ዕጩዎች ተወዳድረዋል።የፌደሬሽን ምክር ቤት ባለፈዉ ቅዳሜ ምርጫዉን እና ዉጤቱን የማይፀና እና እንደተደረገ የማይቆጠር ብሎታል።ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድም ትናንት «የጨረቃ-ምርጫ» በማለት ሕገወጥነቱን ተናግረዋል።ይሁንና የፌደሬሽን ምክር ቤትም ሆነ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሕግ ለማስከበር የሚወስዱት ርምጃም ይኑር አይኑር ያሉት ነገር የለም።
የድምፅ አሰጣጡ ሒደትን፣የመራጭ-አስመራጭ ታዛቢዎች አስተያየትን፣ የማሕበራዉ መገናኛ ዘዴዎች እሰጥ አገባን፣ የአዲስ አበባና የመቀሌ መሪዎችን ጠብን መሠረታዊ ምክንያት በየተራ እንዳስሳለን።ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ የተጓዘዉ ወኪላችን ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት እንደዘገበዉ ድምፅ አሰጣጡ ሒደት ማምሻዉን ተጠናቅቋል።ቆጠራዉ ሌሊቱን ሲቆጠር አድሮ የመጀመሪያዉ ዉጤት ነገ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

-----------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

 ምርጫ በአዲግራት
በዛሬዉ ምርጫ ጠንካራ ፉክክር ይታይባቸዋል ተብለዉ ከተገመቱት አካባቢዎች አንዱ   አዲግራት ከተማ ነው። እንደመቀሌው ሁሉ አዲግራት ላይም ሕዝቡ ለምርጫ ገና ሳይነጋ መውጣቱን በስፍራው ተገኝቶ ሂደቱን የተከታተለው ዘጋቢያችን ሚሊዮን ኃይለ ስላሴ ዘግቧል።

--------------------------------------------------------------------------------------------------------

Äthiopien Tigray | Wahlen | Stimmabgabe
ምስል DW/M.H. Silase

   የትግራይ ተወላጆች አስተያየት

አዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች የዛሬውን የትግራይ ምርጫን ሲደግፉ መዘዙን ይሰጋሉ። የአዲስ አበባው ወኪላችን ሰለሞን ሙጩ ያነጋገራቸው የትግራይ ተወላጆች ምርጫው መደረጉን ተገቢና ዴሞክራሲያዊ ይሉታል። ይሁንና በምራጫውም ሆነ በሌላ ምክንያት የትግራይ እና የፌደራዊው መንግሥት ባለሥልጣናት የገጠሙን እሰጥ አገባ በድርድር መፍታት አለባቸዉ ባዮች ናቸው። 

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት
ትግራይ ውስጥ ዛሬ የተደረገው ምርጫ ከወትሮው የምርጫ ሒደት እና ዕውነት ይልቅ በክልሉ መስተዳድርና በፌደራዊው መንግሥት መካከል ላለው ግንኙነት የሚኖረው እድምታ የዓለም አቀፍ መገናኛ ዘዴዎችን ትኩረት ስቦ ነው የዋለው። አንዳድ መገናኛ ዘዴዎች ምርጫዉ በቀድሞው አማፂ ቡድን፣ በኢሕአዴግ መስራችና በትግራይ ገዢ ፓርቲና በፌደራዊዉ መንግሥት መካከል እስካሁን የነረዉ ቀጭን ግንኙነት ጨርሶ የመበጠሱ ማረጋገጪያ አድርገው ዘግበውታል። የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አስተያየት ሰጪዎችም እሰወስት ተገምሰው ስለምርጫውና መዘዙ ተፃራሪ አስተያየቶችን ሲሰጡ ነው የዋሉት። ማንተጋፍቶት ስለሺ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ሲከታተል ነው የዋለው። ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት አነጋግሬዋለሁ።

---------------------------------------------------------------------------------------------

Äthiopien Wahl in Tigray, Adigrat
ምስል DW

                      የትግራይ ምርጫና የሕግ ባለሙያው
የትግራይ ገዢ ፓርቲ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የወሰነ፣ የመራና ያስተባበረው የዛሬው ክልላዊ ምርጫ የቀድሞው ሸማቂ ቡድን ከፌደራዊው መንግሥትና ገዢ ፓርቲ (ብልፅግና ፓርቲ) ጋር የገጠመው አተካራ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያረጋግጥ ነው። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ምርጫውን «የጨረቃ ምርጫ» በማለት አጣጥለው ሲነቅፉት፣ የጠቅላይ ሚንስትሩ ደጋፊዎች ደግሞ መንግሥት ምርጫውን በጠሩና ባስተባበሩት ላይ ሁነኛ ርምጃ እንዲወስድ ግፊት እያደረጉ ነው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምሕር ቸርነት ሆርዶፋ በበኩላቸው ምርጫውን «ፌደሬሽኑን የማፍረስ እንቅስቃሴ» ብለውታል። የአዲስ አበባው ወኪላችን ሰለሞን ሙጬ አቶ ቸርነትን አነጋግሯቸዋል።

ዘጋቢዎች

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ


 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ ዘገባዎች አሳይ