የትግራይ ምሁራን ዓለም አቀፍ ጉባኤ
ሰኞ፣ ሐምሌ 22 2011ጥናቶቹ ያተኮሩት በ14 የተመረጡ ዘርፎች ላይ ሲሆን የክልሉ መንግሥት ለምሁራኑ ባቀረበው ጥሪ መሠረት ለስትራቴጂክ ዕቅዶች ግብአት የሚሆኑ ሃሳቦች እንደሚቀርቡበት የጉባኤው አስተባባሪ ኮሚቴ ሊቀመንበር ለዶይቼ ቬለ DW ገልጸዋል። ጉባኤው እስከ ሐምሌ 25 ቀን 2011 ዓ,ም ድረስ የሚቆይ ይሆናል።
ትናንት እሁድ በተጀመረው ዓለም አቀፍ የትግራይ ምሁራን ስብሰባ በ200 ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት የሚሠሩ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል። ከተሳታፊ እና ጥናት አቅራቢ ምሁራኑ መካከል 600ዎቹ PHD ያላቸው ሲሆኑ ሌሎች 120 ደግሞ PHD ተማሪዎች መሆናቸውን የጉባኤው አስተባባሪዎች ተናግረዋል። ካለፈው ዓመት ክረምት ጀምሮ በ14 የተመረጡ ዘርፎች ጥናት ሲያደርጉ የቆዩት እነዚህ ምሁራን በግብርና፣ ቱሪዝም፣ ኢነርጂ፣ ሚድያና ኮምኒኬሽን እንዲሁም ሌሎች ርእሰ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ የጥናት ውጤቶች እያቀረቡ ነው።
የዓለም አቀፍ ምሁራን ኮንፈረንስ አስተባባሪ ኮሚቴ ሊቀ መንበርና የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝደንት ዶክተር ኪሮስ ጉዑሽ መድረኩ የትግራይ ክልል መንግሥት ለምሁራን ባቀረበው ጥሪ መሠረት እየተደረገ ያለ መሆኑ በመግለፅ ለስልታዊ ዕቅዶች ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦች እንደሚቀርቡበት አመልክተዋል።
በጉባኤው መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በምሁራኑ አነሳሽነትና ድጋፍ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት እየተቋቋሙ መሆኑ ገልፀዋል። በ2011 ዓ,ም የትግራይ ፖሊሲ ጥናት እና ምርምር ኢንስትቲትዮት፣ የትግራይ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የትግራይ ስታስቲክስ ኤጀንሲ እና ሌሎች ተቋማት መመሥረታቸውን የገለፁት ዶክተር ደብረፅዮን እነዚህ የምሁራኑ ጥናት ተቋማዊ በሆነ ሁኔታ ለመጠቀም ዕድል የሚፈጥሩ ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል። የምሁራን ኮንፈረንሱ አስተባባሪዎች እንደነገሩን በአንድ የትኩረት ዘርፍ ብቻ እስከ 20 የመፍትሔ ሐሳቦችና ጥናታዊ ፅሑፎች እየቀረቡ ነው፡፡ ኮንፈረንሱ እስከ ሐምሌ 25 ድረስ ይዘልቃል።
ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ
ሸዋዬ ለገሠ
እሸቴ በቀለ