1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ማሕበራት ጥያቄ

ሐሙስ፣ መስከረም 12 2015

ኢትዮጵያ ዉስጥ ያገረሸዉ ጦርነት እንዲቆምና ተፋላሚ ኃይላት ጠባቸዉን በድርድር እንዲፈቱ ትግራይ ዉስጥ የሚንቀሳቀሱ 72 የሲቪል ማሕበራት ጠየቁ። ወደ ትግራይ ይገባ የነበረዉ ሰብአዊ ርዳታም ዉጊያዉ ዳግም ከተቀሰቀሰ ካለፈዉ ነሐሴ አጋማሽ ወዲሕ ጨርሶ መቆሙን ማሕበራቱ አስታዉቀዋል።

https://p.dw.com/p/4HEGZ
Äthiopien Tigray-Provinz Mekele
ምስል EDUARDO SOTERAS/AFP

72 የሲቪል ማሕበራት ናቸው ጥያቄውን ያቀረቡት

ኢትዮጵያ ዉስጥ ያገረሸዉ ጦርነት እንዲቆምና ተፋላሚ ኃይላት ጠባቸዉን በድርድር እንዲፈቱ ትግራይ ዉስጥ የሚንቀሳቀሱ 72 የሲቪል ማሕበራት ጠየቁ። ወደ ትግራይ ይገባ የነበረዉ ሰብአዊ ርዳታም ዉጊያዉ ዳግም ከተቀሰቀሰ ካለፈዉ ነሐሴ አጋማሽ ወዲሕ ጨርሶ መቆሙን ማሕበራቱ አስታዉቀዋል። ርዳታዉ የሚጓዝበት ሰብአዊ መተላለፊያ ወይም ኮሪዶር እንዲከፈት  ጠይቀዋልም።የመቀሌዉ ወኪላችን ሚሊዮን ኃይለ ስላሴ እንደዘገበዉ ከዚሕ ቀደም በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ተመሳሳይ ማሕበራት ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ እንደሚደግፉም 72ቱ ማሕበራት በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታዉቀል።

በትግራይ የሚንቀሳቀሱ 72 ሀገራዊ እና ክልላዊ ሲቪል ማሕበራት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ በጋራ ባወጡት መግለጫ እንዳነሱት የሰላም ዕድሉ በመግፋት ዳግም የተቀሰቀሰው ጦርነት ለበርካቶች ሞት፣ ጉዳት፣ መፈናቀል እና ሌሎች ችግሮች ምክንያት እየሆነ ነው በማለት ተፋላሚ ኃይሎቹን ወቅሰዋል። እነዚህ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ የሴቶች እና ወጣቶች ጨምሮ የተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍል የሚወክሉ አደረጃጀቶች፣ የሞያ ማሕበራት፣ ግብረሰናይ ድርጅቶች እና ሌሎች ነፃ ተቋማት ከጦርነቱ ዳግም ማገርሸት ጋር ተያይዞ እየተፈፀሙ ባሉ ጥቃቶች መቐለን ጨምሮ በሽረ፣ ራማ፣ ዓዲግራት እና ሌሎች አካባቢዎች ሲቪሎች ለሞትና ጉዳት ተዳርገዋል ያሉ ሲሆን፥ ከሸራሮ ጨምሮ ከሌሎች ከኤርትራ ጋር የሚዋሰኑ አካባቢዎች ደግሞ በርካቶች እየተፈናቀሉ መሆኑ ገልጿል። የትግራይ ሲቪል ማሕበራት ሕብረት ሰብሳቢ አቶ ያሬድ በርሀ "ተፋላሚ ኃይሎች ጦርነቱን አቁመው ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ" ጠይቀዋል። 

ከ72ቱ ሲቪል ማሕበራት መካከል የሆነው እና 70 ሺህ አባላት እንዳሉት የሚገልፀው የትግራይ መምህራን ማሕበር፥ በጦርነቱ ምክንያት የአጠቃላይ ህዝቡ ኑሮ በተለይም ደግሞ የመምህራን ሕይወት በጅጉ የጎዳ ሆንዋል የሚል ሲሆን፣ ለዚህ ችግር መነሻ ደግሞ እየቀጠለ ያለው ጦርነት መሆኑ በማንሳት ጦርነቱ "በአፋጣኝ፣ ያለ ቅድመ ሁኔታ ይቁም" ብሏል።

72ቱ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሲቪል ማሕበራት ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ወዲህ ወደ ትግራይ ይገባ የነበረ ሰብአዊ እርዳታ ሙሉበሙሉ መቆሙ የገለፁ ሲሆን፣ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቱ እንዲቀጥል የሚያድረግ የሰብአዊ እርዳታ ኮሪደር እንዲከፈትም ጠይቀዋል። የትግራይ መምህራን ማሕበር ጨምሮ 72ቱ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሲቪል ተቋማት በቅርቡ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ 35 ሲቪል ማሕበራት እየቀጠለ ያለው ጦርነት በማውገዝ ያወጡት መግለጫ ያደነቁ ሲሆን ሁሉም ሲቪል ማሕበራት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት እና ሌሎች የሰላም ጥረት አካል ይሁኑ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ