1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ መስተዳድር ወቀሳ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 24 2013

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና የኤርትራ መንግስት ትግራይ ላይ የኃይል እርምጃ ለመውሰድ በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው ሲል የትግራይ ክልል መንግስት ከሰሰ። የትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስትና የትግራይ ክልል መንግስት ግንኙነት ወደ ከፋ ደረጃ እያመራ መሆኑ አንስተዋል።

https://p.dw.com/p/3knFF
Äthiopien l PK - Dr. Debretsion Gebremichael
ምስል DW/M. Haileselassie

«የፖለቲካ እስረኞች ተፈትተው ሁሉን አካታች ውይይት ማካሄድ መፍትሄ ነዉ»

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና የኤርትራ መንግስት ትግራይ ላይ የኃይል እርምጃ ለመውሰድ በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው ሲል የትግራይ ክልል መንግስት ከሰሰ። የትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ትላንት ለክልሉ መንግስት መገናኛ ብዙሐን በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ ፌደራሕ መንግስት እና የትግራይ ክልል መንግስት ግንኙነት ወደ ከፋ ደረጃ ተሻግሮ ወደ ጦርነት እያመራ መሆኑ አንስተዋል። በዚህም ርእሰ መስተዳድሩ ለህዝባቸው 'ለሁሉም ነገር ዝግጁ ሁን' ሲሉ ጥሪ ሲያቀርቡ ተደምጠዋል። ባለፉት ግዜያት የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት በክልሉ ላይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የፕሮፓጋንዳ ጦርነት ከፍቶ መቆየቱ ያነሱት ርእሰ መስተዳደሩ፤ አሁን ላይ ነገሮች መልካቸው እየቀየሩና ወደ ሐይል እርምጃ እየተንደረደሩ ነው ሲሉ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሀገር መከላከያ ሰራዊት በተጠንቀቅ እንዲቆም ከሁለቱ ሀገራት መሪዎች መልእክት መተላለፉ መረጃ እንዳላቸው ያነሱት የትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረፅዮን "ከውጭ መንግስት ጋር ወግኖ በሀገሩ ውስጥ ያለ ህዝብ ለመምታት መንቀሳቀስ  ክህደት ነው" ሲሉ ተናግረዋል። "ጦርነት አንፈልግም፤ ከመጣ ግን ራሳችን እንከላከላለን። ለዚህም ተዘጋጅተናል" ብለዋል ርእሰ መስተዳድሩ። የታሰሩ 'የፖለቲካ እስረኞች' ተፈትተው ሁሉን አካታች ውይይት ማካሄድ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ እየታየ ላለው የፖለቲካ ችግር በመፍትሔነት ያቀረቡት ዶክተር ደብረፅዮን "ከጦርነት በፊትም ሆነ በኃላም መፍትሔው መነጋገር ነው። ጦርነት አስቀርተን ሁሉም ያካተተ ውይይት እናድርግ" ሲሉ ገልፀዋል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ 

አዜብ ታደሰ 

ነጋሽ መሐመድ