1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትስስር የቡና ንግድ መንገዱ አቋራጭ ወይስ?

ረቡዕ፣ መስከረም 16 2016

ሂደቱ በአንድ በኩል ቀደም በምርት ገበያ በኩል የሚያልፈውን ረዘም ያለ የንግድ ሰንሰለት አሳጥሮ በተለይ አርሶ አደሩ በቀጥታ ተጠቃሚ እየሆነበት እንደሚገኝ ሲገለጽ በሌላ በኩል ደግሞ ቡናውን ከአርሶ አደሩ ተረክበው ለላኪዎች የሚያቀርቡ ነጋዴዎች አሰራሩ« ለምርት ቅሸባ እና ነጋዴውን ለከፍተኛ እንግልት የሚዳርግ ነው» ሲሉ ይደመጣሉ ።

https://p.dw.com/p/4WppR
የኢትዮጵያዉያን የቡና አጠጣጥ ባሕል
ቡና በሲኒምስል Azeb Tadesse

የቡና እና ሻይ ባለስልጣን መንገድ ለቡና አቅራቢዎቹ ቅሬታ መፍትሄ መሆን ይችል ይሆን?

በኢትዮጵያ ቀደም ሲል በምርት ገበያ በኩል ለማዕከላዊ ገበያ ይቀርብ የነበረው የቡና ንግድ ተቀይሮ በቡና እና ሻይ ባለስልጣን ተቆጣጣሪነት አምራቹ ወይም አቅራቢው በቀጥታ ከላኪው ጋር በሚፈጥሩት የአቅርቦት ወይም የንግድ ትስስር ግብይት ከተቀየረ ሁለት ዓመት ሊሞላው ነው። ሂደቱ በአንድ በኩል ቀደም በምርት ገበያ በኩል የሚያልፈውን ረዘም ያለ የንግድ ሰንሰለት አሳጥሮ በተለይ አርሶ አደሩ በቀጥታ ተጠቃሚ እየሆነበት እንደሚገኝ ሲገለጽ በሌላ በኩል ደግሞ ቡናውን ከአርሶ አደሩ ተረክበው ለላኪዎች የሚያቀርቡ ነጋዴዎች አሰራሩ« ለምርት ቅሸባ እና ነጋዴውን ለከፍተኛ እንግልት የሚዳርግ ነው» ሲሉ ይደመጣሉ ። ጤና ይስጥልን አድማጮቻችን በዛሬው የከኤኮኖሚው ዓለም ዝግጅታችን በኢትዮጵያ የቡና ምርት ግብይት ሂደት ለውጥ የሚሰሙ ቅሬታዎች እና መንግስታዊው የባለስልጣን መስሪያ ቤት በለውጡ እየመጣ ነው  ስለሚለው የገበያ ትስስር ከብዙ በጥቂቱ እንቃኛለን ።

የቡናዉ ፍሬ በጥንቃቄ ግን ወቅቱን ጠብቆ መለቀም አለበት
ከቡና አምራች ገበሬዎች አንዱምስል AP Photo

አቶ ባስራ ባራ ይባላሉ ። በቅርቡ በአዲስ መልክ በተዋቀረው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አማሮ ዞን ኬሌ ከተማ ነዋሪ እና የቡና ነጋዴ ናቸው ። ለረዥም ዓመታት በቡና ንግድ ላይ እንዳሳለፉ የሚገልጹት አቶ ባስራ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የቡና ንግድ ስራቸው እየተረበሸባቸው ነው። ምክንያት ነው የሚሉት ደግሞ የቡና ጥራት መለኪያ ደረጃ አወጣጥ ተገቢውን የገበያ ዋጋ እንዳያገኙ ብሎም ለተጨማሪ እንግልት እንደሚዳርጋቸው ነው። 
« ሀዋሳ ላይ ምርት ገበያ ዉጤቱ ወጥቶ ደረጃ አንድ ነው ከተባለ እንደገና ወደ ላኪ በቡና እና ሻይ የሚሸኘው ከዚያ እንደገና ላኪዎች በራሳቸው ባለሞያ አዲስ ናሙና ወስደው አሰ,ርተው ደረጃ አንድ እና ሁለት ላይ የነበረ ቡናን ደረጃ ሶስት፣ አራት እና አምስት ነው እያሉ በዚህ መሃል ነው እየተሰቃየን ያለነው»
ይህ ብቻ አይደለም ይላሉ የአማሮው ቡና አቅራቢ ቡና በዓለም ገበያከአቅማችን በላይ በሆነ ሁኔታ ተገደን ለቡና ላኪዎቹ ምርቱን ብናስረክብም ተገቢውን ክፍያ በወቅቱ አለማግኘታችን ለምሬት ዳርጎናል ይላሉ።

« የገንዘብ ክፍያው በጊዜ አለመከፈሉ ፤ ከዚህ በፊት በኢሲኤክስ በ,ነበረበት ሰዓት ላይ ቀጥታ ቡናው የላኪው መጋዘን እንደተራገፈ 24 ሰዓትባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነበር ክፍያ የሚፈጸመው ። አሁን ያ ቀርቶ አዲሳባ በላኪ መጋዘን ገብቶ ሌላ አዲስ ናሙና ተወስዶ እንደገና ደረጃው ከፍ አለ ዝቅ አለ እየተባለ መዓት ጣጣ እና ውጣ ውረድ ነው ውስጡ ያለው»
 እዚያው አማሮ ዞን ከ1986 ዓ/ም ጀምሮ በቡና ንግድ ላይ መሰማራታቸውን የሚገልጹት ሌላው የቡና አቅራቢ አቶ አሸናፊ አፍሮ ይባላሉ ። በዚህ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ «ትስስር» በተባለው መንገድ ቡና አቅራቢው በቀጥታ ከላኪው ጋር ተደራድሪ የሚገበያይበት አሰራር ለደረቅ ቼክ አጋልጦናል። ገንዘባችንን ከወራት ልመና እና ደጅ መጥናት በኋላ እስከማግኘት ደርሰናል ይላሉ ። 

ቡና ለቃሚዎች የበሰለዉን ከጥሬዉ፣ የተበላሸዉን ከደሕናዉ ይመርጣሉ
«ምርቱን ከእንክርዳዱ» የተበለሻ የቡና ፍሬ በዚሕ መንገድ ይለያልምስል AP Photo

« ዱቤ ወስደው ሰው ነው የወሰደው ብሎ ሸውዶ በደላላ ነው ሄደን አንሸጥም ፤ ፈርምና ደረቅ ቼክ ይሰጥሃል ብለው ፤ አሁን እኔ ሶስት ወር ነው ሳይከፍል የቀረበት ።»
ኢትዮጵያ ባለፈው የ2015 የበጀት  ዓመት ከ240 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለውጭ ገበያ ማቅረቧን መረጃዎች ያመለክታሉ። በዓመቱ ሳዑዲ አረቢያ፣ ጀርመን፣ አሜሪካ፣ ኮሪያ፣ ቤልጅየም፣ ጃፓን እና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች የኢትዮጵያን የቡና ምርት በቅደም ተከተል በብዛት የገዙ አገራት ናቸው። ባለፈው ዓመት ለዓለም ገበያ የቀረበው ምርት ከቀደመው የ2014 ዓ/ም ጋር ሲነጻጸር የ60 ሺ ቶን ገደማ ቅናሽ አሳይቷል። በወቅቱ ለዓለም ገበያ የቀረበው የቡናምርት ቅናሽ ለማሳየቱ በሀገሪቱ የተንሰራፋው ግጭት እና ጦርነት በዋነኛነት ሲጠቀስ የዓለማቀፉ የቡና ዋጋ ማሽቆልቆሉም በተደራቢ ምክንያትነት ተጠቅሷል። 
ሀገሪቱ ባለፈው የበጀት ዓመት ከ1,4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያገኘችበት እንደነበር የጠቀሱት የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር ናቸው ። አቶ ሻፊ እንደሚሉት እርሳቸው የሚመሩት ባለስልጣን የተከተለው አዲስ የግብይት ትስስር ወይም በእርሳቸው አባባል ሪፎርም ለገቢው መገኘት አይነተኛ ምክንያት ተጫውቷል። ከቡናዬ አንድ ዶላር ለኢትዮጵያ 
«ጥር 2013 ላይ ነው ይህንን ተግባራዊ ያደረግነው ። ጥር ላይ 907 ሚሊዮን ነው ያገኘነው ፤ ይሄ 907 ሚሊዮን ማለት እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ ታሪክ ከ800 ሚሊዮን አልፈን አናውቅም ። ትልቁ የሚባለው 864 ሚሊዮን ነው ያገኘነው። ከዚያ በኋላ በ2014 ደግሞ የ500 ሚሊዮን ጭማሪ አሳይተን 1,424 ቢሊዮን ዶላር አግኝተናል።»
በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በእንግሊዘኛ ምህጻሩ ኢ ሲ ኤክስ አማካኝነት ግብይት ይፈጸም የነበረው የቡና ምርት በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ተቆጣጣሪነት የቀጥታ ትስስር አሰራር ተግባራዊ እንዲደረግ ሲታቀድ አምራቹ እና ሀገር በጋራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዕድል ለመፍጠር ነው ይላ አቶ ሻፊ 
« አንደናው ሪፎርም አርሶ አደሩ በቀጥታ ቡናውን ወደ ውጭ የሚልክበት ሁኔታ ተፈጥሮ ብዙ አርሶአደሮች ከመቶ በላይ የሚሆኑ አርሶአደሮች ወደ ውጭ ቡና ልከዋል።  ራሳቸው ላኪ ሆነው ከዚያም በላይ ወደ ኢንቨስትመንት እየተሸጋገሩ ያሉ አርሶአደሮች አሉ ሁለተኛው አቅራቢዎች የአቅራቢ ላኪነት ፈቃድ አውጥተው ከራሳቸው ማጠቢያ ጣቢያ ቡና ሰብስበው በደንብ የተዘጋጀ ቡና በቀጥታ ወደ ውጭ እንዲልኩ ይሄ ሪፎርም ተዘጋጅቷል። »

ገበሬዉ ከቡናዉ ማሳ መሐል አረፍ ብሎ ጫት ሲቅም
ኢትዮጵያዊዉ የቡና አምራች ገበሬ በእረፍቱ ሰዓትምስል AP

አይ ይላሉ ሌላ ከደቡብ ክልል በወቅታዊ የቡና ግብይት ምሬታቸውን የገለጹልን ቡና አቅራቢ ፤ ዮሐንስ ቺሎ ይባላሉ በትስስር ገበያ ለቡና ላኪ ግለሰብ ቡና ያቀረቡበትን እና በመጨረሻ የገጠማቸውን ባወጉን ወግ ሂደቱ በችግር ስለመሞላቱ ያወሳሉ።
« የማያውቀኝ ሰው ስልክ ደወለ ቡና አልህ አለኝ፤ አለ አልኩት ናሙና ይዜ ሄድኩ ፤ በቃ ሁለት ደላሎች አሉ አሉ አንድ ባለንብረት የሚባል አለ፤ ተገናኝተን ናሙና ወስዶ ደረጃ ሶስት ወጥቷል ብሎ ፤ ዋጋ ተስማማን ፤ ቡናውን ካራገፍኩለት በኋላ ይኸው ሶስት ወር ገንዘቤን መቀበል አልቻልኩም ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ከቡና ምርት ግብይት እና ወደ ውጭ መላክ ጋር ተያይዞ በርካታ ሃሳቦች ሲንሸራሸሩ ይታያል ይሰማል። ዘርፉ ሀገሪቱ ከፍተኛ የውች ምንዛሪ ከምታገኝባቸው ምርቶች ከቀዳሚዎቹ የሚሰለፈው የቡና ምርት ከግብይቱ ጋር ተያይዞ በርካታ ችግሮች አብረው ሲነሱም ይስተዋላል ። ህግ እና ስረዓት ተበጅቶለት የነጻ ገበያ አሰራርን ተከትሎ ተግባራዊ ሲደረግም ከግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው መሰረታዊ እሳቤዎች ሲዘነጉም ይታያል። 
አቶ አሸናፊ አፍሮ እንደሚሉት በዚሁ የነጻ ገበያ አሰራር  እርሳቸው እና ልጃቸው ከ600 ኩንታል በላይ የተገዛ ቡና በመጋዘናቸው አከማችተው እንደሚገኙ ይናገራሉ ። ምክንያቱ ደግሞ የቡና ዋጋ በመውረዱ ነው ይላሉ። የአየር ንብረት ለዉጥ ያሰጋዉ የኢትዮጵያ ቡና
« ቡና አሁን ምንም ሳይሸጥ የቆየ አለ እኛጋ የቆየ የታጠበ ቡና አለ። የእኔ ልጅ እና የእኔ 600 ኬሻ ቤት ውስጥ አለ። ገዢ የለም ። ከወሰዱም ደግሞ ብር አይሰጡም።  »
የቡና እና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር ቡና አቅራቢዎች የዓለም የቡና ዋጋን ሳያገናዝቡ ቡና መግዛታቸው ለመሰል ችግር እየዳረጋቸው እንደሆነ ነው የሚገልጹት 
« የዓለም ገበያ ዋጋን ሳያዩ በውድድር ገንዘብ በእጃቸው ስለገባ በከፍተኛ ዋጋ ቡና ገዝተው ላኪው ደግሞ ቡናውን የሚገዛው በዓለማቀፍ የገበያ ዋጋ ላይ ተመስርቶ ስለሆነ እንደሚታወቀው የእኛ ብቻ ሳይሆን የብራዚልም ሆነ የሁላችንም ዋጋ ተቀባይ ነን እንጂ ዋጋ ላይ ተጽዕኖ ማድረግ አንችልም። »
እንደ አቶ ሻፊ በመሰል ሁኔታ ቡና ገዝተው በሚያከማቹ ነጋዴዎች ላይ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የመቆጣጠሪያ ስልት እንዳለው ነግረውናል። ነገር ግን የቡና ምርት በቀላሉ ለብክለት ተጋላጭ ከመሆኑ የተነሳ እና ለወትሮም በግጭት ጦርነት እየተናጠች ላለች እና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ላለባት ሀገር መሰል በአሰራር ችግር ለሚደርሱ የጋራ ኪሳራ አምጭ ጉዳዮች ሳይቃጠል በቅጠል ሊባል የሚገባ ጉዳይ ነው። 

የቡና ምርትን ጨምሮ በርካታ የጥራጥሬ ምርቶችን በማገበያየት የሚታወቀው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ወይም ኢሲኤክስ በዚሁ ከቡና አቅራቢዎች ከሚያነሷቸው አቤቱታዎች እና በአሰራር ሂደት ክፍተት የተፈጠረው የት ይሆን ብለን ለማጣራት ባደረግነው ጥረት ሃሳባቸውን ሊያካፍሉን ፈቃደና ሳይሆኑ ቀርተዋል። ከፍተኛ የቡና ምርት በሚወጣበት የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ተመሳሳይ ችግር ካለ ብለን አንዳንድ የቡና አቅራቢዎችን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ሃሳባቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሳይሳካ ቀርቷል። የሆነ ሆነ በዚህ በአዲሱ የ2016 የበጀት ዓመት ኢትዮጵያ  350 ሺህ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ከቡና እና ሻይ ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ከቅሬታ ሽኩቻ ባሻገር ዕቅዱ ይሳካ ይሆን ? የከርሞ ሰው ይበለን ። 
ታምራት ዲንሳ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር