1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታጋች ተማሪዎች ወላጆች አዲስ አበባ ተጠሩ

ረቡዕ፣ ጥር 20 2012

የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ልጆቻቸው ከታገቱባቸው ወላጆች መካከል ሦስቱ ወደ አዲስ አበባ ተጠርተው በአውቶቡስ በመጓዛ ላይ መኾናቸውን ለዶይቸቬለ (DW) ተናገሩ። ከሦስቱ ወላጆች ሁለቱ ከሰሜን ጎንደር አንደኛው ከደቡብ ጎንደር የተነሱ ሲኾን፤ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ከሚኖሩበት ዞኖች ጽ/ ቤቶች ተደውሎ የተነገራቸው ሰኞ ዕለት መኾኑንም ገልጠዋል።

https://p.dw.com/p/3Wy9z
Karte Ethiopia und Eritrea ENG

ወላጆች ወደ አዲስ አበባ የተጓዙት ተስፋ ሠንቀው ነው

«ጠቅላይ ሚንሥትሩ ስለልጆቻችሁ እንጠይቃችኋለን ብለውን ወደ አዲስ አበባ እየሄድን ነው።» 

የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ልጆቻቸው ከታገቱባቸው ወላጆች መካከል ሦስቱ ወደ አዲስ አበባ ተጠርተው በአውቶቡስ በመጓዛ ላይ መኾናቸውን ለዶይቸቬለ (DW) ተናገሩ። ከሦስቱ ወላጆች ሁለቱ ከሰሜን ጎንደር አንደኛው ደግሞ ከደቡብ ጎንደር የተነሱ ሲኾን፤ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ከሚኖሩበት ዞኖች ጽ/ ቤቶች ተደውሎ የተነገራቸው ሰኞ ዕለት መኾኑንም ገልጠዋል። ከወረዳ፦ ዞን፤  ከዞን ወደ አዲስ አበባ ትሄዳላችሁ ተብለው እንደተጠሩ እንጂ ዝርዝር ነገር እንዳልተነገራቸውም ተናግረዋል። 

«ሂድ አሉኝ፤ ምነው ምን ላደርግ ነው የምሄደው? እንዴት ነው፤ ልጆቹን ልናገኝ ነው ወይንስ ምንድን ነው? ገንዘብ የለ፤ እኛ ገበሬዎች ገንዘብ ከየት እናገኛለን ያን ያኽል ሀገር በማናውቀው ሀገር የምንሄድ ብዬ በምልበት ሰአት» ሲሉ በአስቸጋሪ ኹኔታ እየተጓዙ መኾኑን መሪ ጌታ የኔነህ አዱኛተናግረዋል። የተሰጣቸው መልስም፦ «አያይ ለአኹኑ ከዚህ አካባቢ ቤተሰብ ካለ ከጎንደር ያለ ገንዘብ ትንሽ ያዝ እና መድረሻ ያዝና ከዚያ ወዲያ እነሱ ነው የሚከፍሉት፤ የመጣችሁበትን አበል ይቆርጣሉ እና ሒድ ዝም ብለህ» እንደተባሉም አክለዋል። «ምናልባት ልታገኝ ትችላለህ የሚሉት ዐይታወቅም ሲሉኝ፤ መቼም እንግዲህ የጠፋው ችግር ነው፤ እማገኝ እና እናቲቱ ደግሞ የማረጋጋ መስሎኝ ላመጣልሽ በሚል ደረጃ ወጥቼ ወደዚያው እየኼድኩ ነኝ» በሚል ተስፋ ሰንቀው እየተጓዙ መኾናቸውን ገልጠዋል።  

ማዕከላዊ ጎንደር ዞን አዲስ አበባ ሲደርሱ ተቀባይ እናዳላቸው እና በተስፋ ልጆቻችንን እናገኛለን ብለው ረዥሙን እና አስቸጋሪውን ጉዞ በአውቶብስ መያያዛቸውን ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። «እዚህ ከተፈለገ ታዲያ እዚህ ቢመጡልን ምን አለ ብለን ብንል፤ አያይ ዝም ብላችሁ ተፈልጋችኋል ሒዱ። ምናልባት ለልጆቻችሁ የምታስቡ ከኾነ ሒዱ አሉን። እንግዲህ እኛም ደግሞ የጠፋው ሰው ሞኝ ነው እንደሚባል ያው እየመሰለን ሒደናል እንግዲህ። መፍትኄ አልደረስንም እንጃ እንግዲህ የሚሉንን ነገር እናኛ ዐናውቅም» ሲሉ መሪጌታ የኔነህ አክለዋል።  

Bahir Dar Demonstration Amhara Region Äthiopien
ምስል DW/A. Mekonnen

ልጃቸው ከታገተባቸው ወላጆች መካከል ከጭልጋ ወረዳ የተነሱት አቶ ሐብቴ እማኘው ደግሞ፦ «አቶ ንጉሡ ስላስጠሩን ከዞን፤ ዞኑ ልከውን ነው፤  ወደ ንጉሡ እየሄድኩ ነው» ብለዋል። ለምን ተደውሎ እንደተጠሩ ያውቁ እንደኾን ከዶይቸ ቬለ ተጠይቀውም፦ «ተፈልጋችኋል ነው እንጂ ምንም ዐላወቅንም» ሲሉ መልሰዋል። እርግጠኛ ባይኾኑም ከሦስቱ ወላጆች በተጨማሪ ሌሎች ሦስት ወላጆችም አስቀድመው ጉዞ መጀመራቸውን መስማታቸውን ተናግረዋል። 

ከደቡብ ጎንደር የተነሱት ሌላኛው ወላጅ አቶ ላጨው ጓዴም፦ «ከዞን ከደብረታቦር ተደውሎልኝ እየሄድኩ ነው» ብለዋል። ከደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ ማንነታቸው ባልታወቀ ሰዎች የታገቱት በአብዛኛው ሴት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንዲለቀቁ መንግሥትን የሚጠይቁ መጠነ ሰፊ ሰልፎች በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች እና በዩናይትድ ስቴትስ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ትናንት ተከናውኖ ነበር። ከታገቱት 17ቱ ተማሪዎች አብዛኞቹ ሴቶች ናቸው። ወላጆቻቸው ባልታወቀ አካል የታገቱ ልጆቻቸውን ድምጽ እስካሁን ባይሰሙም፤ ከዚህ ቀደም ግን መንግሥት ተማሪዎቹ መለቀቃቸውን ገልጦ ነበር።

ከሦስቱ ወላጆች ጋር የተደረገውን ሙሉ ቃለ መጠይቅ ከድምጽ ማገናኛው ማድመጥ ይቻላል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ