1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታሰሩ ጋዜጠኞች ይፈቱ፤ ጠ/ሚ ዐቢይ በነቀምት፤ አሳሳቢዉ ሱዳን ቀዉስ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 13 2015

የመናገር ነጻነት ይከበር፤ የታሰሩ ጋዜጠኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ የቀረ በጥሪ ለመጀመርያ ጊዜ ነቀምት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ እንዲሁም በሱዳን ጦር ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል ተጠናክሮ የቀጠለዉ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ሱዳናዉያንን ወደ ጎረቤት ሃገር እያሰደደ መሆኑ ስር የተሰጡ አስተያየቶችን ይዟል።

https://p.dw.com/p/4QQNz
Symbolbild Whistleblower Afrika
ምስል Andrey Popov/Panthermedia/imago images

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣው ሕዝባዊ አመጽና ብጥብጥ አሳስቦኛል ሲል የአሜሪካ ኢትዮጵያውያን ሕዝብ ጉዳይ ኮሚቴ በምጽሃሩ «ኤፓክ» በዚህ ሳምንት ገልጿል።  የአሜሪካ ኢትዮጵያውያን ሕዝብ ጉዳይ ኮሚቴ እንደተናገረዉ የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎችን ደህንነት ሁልጊዜ የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት ። የሰላማዊ ዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥም፣ የተለያዩ ታጣቂ ኃይላትን የማዋሃድ እንቅስቃሴ በስርአት እንዲያካሂድ ጥሪ አቅርበዋል። «ሕዝቡን በማወያየትና በፈቃደኝነት፣ ለሀገራቸው የተዋደቁትን ኢትዮጵያውያን በማሰባሰብ በፈቃደኝነት እና በመግባባት መፈፀም አለበት ብሏል። ሲብራ ለገሰ የተባሉ የፌስቡክ አስተያየት ሰጭ፤ በሐገራችን ልዩ ሐይሎች ትጥቅ ከፈቱ ጀምሮ ሰላም እየሆነ ነው፡፡ ትንሽ የሚቀሩ ስራዎች አሉ። እነሱን መንግሥት በቶሎ ቢፈታ 100% ሰላማችን ይመጣል፤  የመንቀሳቀስ መብት ይኖረናል፤ ሲሉ ጽፈዋል።

እንድርያስ አምሳሉ የተባሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ ፤ የፌዴራል መንግስት አሁን በልዩ ኃይል ላይ የወሰደውን እርምጃ ባይወስድ ኖሮ በሱዳን የተፈጠረው በኢትዮጵያ በአንዱ ክልል መፈጠሩ  የማይቀር ነገር ነው ሲሉ ጽፈዋል። ዶቼዎች ሲሉ አስተያየታቸዉን የጀመሩት ደግሞ አብደላ ሲራጅ ጅፋር ናቸዉ። ዶቼዎች፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሁሉ ሰላም ነዉ፤ ምንም ችግር የለም ። ትንሽ ከኑሮ ዉድነት በስተቀር ሲሉ ጽፈዋል።

Uganda | Smartphone Nutzerin in Kampala
የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ምስል ISAAC KASAMANI/AFP/Getty Images

የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዉሞን በሰላማዊ ሰልፍ የመግለፅ መብትን እንዲያከብርና የታሰሩ የመገናኛ ዘዴ ባለሙያዎችን እንዲፈታ አምንስቲ ኢንተርናሽናል በዚህ ሳምንት ነበር መግለጫ ያወጣዉ። ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ባለፈዉ ሳምንት አማራ ክልል በተፈጠረዉ ሁከት ምክንያት ያሰሯቸዉን 7 የመገናኛ ዘዴ ባልደረቦች ባስቸኳይ እንዲፈቱ፣ ከእስረኞቹ ባንዷ ላይ ተፈፀመ የተባለዉን አካላዊ ጥቃት እንዲያጣሩ ጠይቋል።መግለጫዉ እንዳለዉ ባለስልጣናቱ «ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትንና ሁሉም ወገን በሰላማዊ መንገድ የመቃወም መብቱን ማስከበር አለባቸዉ።»

ጀምስ ማዲሰን የተባሉ የፌስቡክ አስተያየት ሰጭ ምን ያገባዋል አምነስቲ እዚህ ሲሉ ጠይቀዋል። ሳሚ አበበ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ በበኩላቸዉ፤ ኢንተርኔት ሲዘጉ የዘጉበት ፓስወርድ ስለጠፋ ነው ለመክፈት ያልተቻለዉ።  ፓስወሩዱ ስለጠፋቸው ለማስከፈት ከቻይና ጋር እየተደራደሩ ነው፤ ሲሉ ምጸት አይነት አስተያየት ጽፈዋል። ማሜ ቡልጋ የተባሉ በበኩላችሁ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሁሉ ሰላም ነዉ አሁን ብጥብጥ እና ሰላማዊ ሰልፍ የሚታየዉ ጎረቤታችሁ የሚገኘዉ ፈረንሳይ ዉስጥ ብቻ ነዉ ብለዋል። 

ዳንኤል ወልደገብርኤል የተባሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ፤ በኢትዮጵያ ሀገራችን የሚታየዉ አሳዛኝ ነገር የመንግሥት ፀጥታ አስከባሪ የተባሉት አካላት ተቃዋሚ የሚባሉ ሚዲያዎችንና፤  ታዋቂ ተቃዋሚ የፖለቲካ ሰዎችን በሙሉ በገንዘብ በመያዛቸው አንድም ሚዲያ ሆነ ታዋቂ የፖለቲካ ሰዎች ስለታሰሩት የሚዲያ አካላትም ሆነ ጋዜጠኞች መታሰር አይናገሩም አይዘግቡም ። ይህም በመሆኑ የኢትዮጵያ ሀገራችን ዉስጥ ያለዉ እንቆቅልሽ ሊፈታ አልቻለም። ወደፊትም ቢሆን የእነዚህን አካላት ሴራና ድርጊት ካልተረዳን በስተቀር ከዐቢይ አህመድና ከህወሓት መሪዎች አገዛዝ በፍጹም መላቀቅ አይቻልም፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ በያዝነዉ ሳምንት በምስራቅ ወላጋ ዞን መዲና ነቀምት ከተማ መገኘታቸዉ ብዙዎችን አግራሞት ፈጥሯል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ወደ ነቀምት ሲያቀኑ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ ነዉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደዝያ የመሄድ ስጋት እንዳላቸዉ ከዓመታት በፊት ተናግረዉ እንደነበር የሚታወስ ነዉ። እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን በስፋት ከሚንቀሳቀስባቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች መካከል አንዱ ምስራቅ ወለጋ ሲሆን በአካባቢዉ ላይ  ከሰላማዊ ሰዎች በተጨማሪ የመንግሥት ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ዒላማ መደረጋቸዉ ይታወቃል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ምስራቅ ወላጋ ነቀምት ሲደርሱ በአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና በአካባቢ አመራሮች ደማቅ አቀባበል እንደተረገላቸው በምስል በተደገፈ መረጃ ይፋ ሆንዋል።

Äthiopien Stadt Nekemit | Premierminister Abiy Ahmed mit Vertretern der Wollega-Zonen Region Oromia
ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ነነቀምትምስል Facebook.com/Office PM Ethiopia

አብሩ አብደላህ የተባሉ የፌስቡክ አስተያየት ሰጭ ከ 150 በላይ ንጹኃን ከባኮ ተወስደው ያለምንም ፍርድ በነቀምት ከተማ ከታሰሩ አንድ ዓመት ሞላቸው ፍትህ፤ ፍትህ፤ ፍትህ ብለዋል።

አበራ አየለ የተባሉ  አስተያየት ሰጭ በበኩላቸዉ አካባቢዉ ላይ በግፍ የተገደሉትን እናስባለን ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል። በርግጥ አድማጮች የጠቅላይ ሚኒስትሩ ነቀምት ከተማን መጎብኘት በተመለከተ  የተሰጡት አስተያየቶች እጅግ በርካታ ይሁኑ እንጂ ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል አብዛኞቹ ለሚዲያ የማይመጥኑ በአብዛኛዉ ዝልፍያና ስድብ በመሆናቸዉ ልናቀርባቸዉ አንችልም።  ወደ ሱዳን እናልፋለን።

ባለፈው ቅድሜ በሱዳን  መከላከያ ሰርዊትና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መክከል የተጀመረው ውጊያ በተለይ በዋና ከተማ ካርቱም አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል ። በጦርነቱ እሳክሁን  ከ300 በላይ ሰዎች እንድተገድሉና ወደ 2800 በላይ ሰዎች እንደቆሰሉ ከልዩ ልዩ ድርጅቶች የሚውጡ ዘገባዎች ያስረዳሉ።  እስካሁን አራት ኢትዮጵያዉያን በቤታቸዉ ዉስጥ እንዳሉ ከአዉሮፕላን በደረሰ ጥቃት እንደተገደሉም ተሰምቷል። ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያዉያን በሚገኙባት ሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን መንግሥት ከጦርነት እንዲያወጣቸዉ እየተማፀኑ ነዉ። ህዝብ በፀሎት እንዲያስባቸዉም ጠይቀዋል። ከጦርነቱ ባሻገር ታጣቂ ሚሊሺያዎች ዘረፋ እየፈፀሙ ነዉ።  

Sudan Eid al-Fitr vor Al-Hara al-Rabaa Moschee
በጦርነት ዉስጥ የተዘፈቀችዉ ሱዳን ምስል AFP

ከተማ ለታ የተባሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተከታታይ አረ የአፍሪቃ መሪዎች ቆም ብላችሁ አስቡ ሲሉ አስተያየት ጽፈዋል። ባህሩ አሞራ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ ለሱዳን ህዝብ ዱኣ እናድርግ አላህ ይድረስለት ። ችግር ውስጥ ናቸው። ወቅቱ ረመዷን ነው።  ይህን ሸርና ሴራን ያሴሩ  ምንም እሳትም ሆነ ጭስ ሳይነካቸው በርቀት ሆነው ወንድም ከወንድም ያገዳድላሉ፤ ያሳዝናል ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።

ደገፉ ደግነት የተባሉ አስተያየት ሰጭ ደግሞ፤ የምሥራቅ አፍሪቃ ቀጣና ያለመረጋጋት ዋናኛ ምክንያት ከሚባሉት አንዱ ለዜጎች ክብርና ደህንናት የሚጨነቅ መሪ አለመኖሩ ነዉ፤  ሲሉ አስተያየታቸዉን በአራት ነጥብ ዘግተዋል።

ካሳሁን የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፣ ከአንድ ዓመት እና ከሁለት ዓመታት በፊት የሱዳን ጀነራሎች ከራሳቸው አቅም ላይ ግብፅንም ጨምረው ኢትዮጲያን ያስጨንቁ፤ ግዛቷንም ይደፍሩ፤ መሬቷንም ይወስዱ ነበር። አሁን ደግሞ ጎራ ለይተው የገዛ ሀገራቸውን እያወደሙ፤ ህዝባቸውንም እየፈጁ ናቸዉ፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ቋጭተዋል። ቢር ዲር የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ ሁለቱ ጄኔራሎች የስልጣን ጥማት ይዟቸው  ምንም የማያዉቀዉን ህዝብ  ውንድም ከወንድሙ እያባሉት ነዉ፤ ያሳዝናል ሲሉ ጽፈዋል።  

 

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ