1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ውዝግብ፤ ምርጫና የህገመንግስት ትርጓሜ

ዓርብ፣ ግንቦት 7 2012

በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል ሲካሄድ የቆየው ድርድር መቋረጡን ተከትሎ በቅርቡ ግብጽ ኢትዮጵያ እየገነባቸው ባለው ታላቅ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ አቤቱታዋን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አቅርባለች።ኢትዮጵያ በበኩሏ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚያስችላትን ውሃ በመጪው ሐምሌ ወር መሙላት እንደምትጀምር አስታውቃለች

https://p.dw.com/p/3cIKU
Symbolbild Social Media
ምስል DW/S. Leidel

የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ውዝግብ፤ ምርጫና የህገመንግስት ትርጓሜ
ጤና ይስጥልን አድማጮቻችን መቋጫ ያላገኘው የኢትዮጵያና ግብፅ ውዝግብ ፤የኢትዮጵያ ምርጫና የህገመንግስት ትርጓሜ እንዲሁም ችላ የተባለው የኮሮና ወረርሽኝ ጥንቃቄና የፖሊስ ርምጃ በዛሬው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት የምንዳስሳቸው ጉዳዮች ናቸው ።አብራችሁን ቆዩ።
በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል ሲካሄድ የቆየው ድርድር መቋረጡን ተከትሎ በቅርቡ ግብጽ ኢትዮጵያ እየገነባቸው ባለው ታላቅ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ አቤቱታዋን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አቅርባለች።ኢትዮጵያ በበኩሏ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚያስችላትን ውሃ በመጪው ሐምሌ ወር መሙላት እንደምትጀምር አስታውቃለች።በሌላ በኩል ለግብፅ ካደላዉ የአረብ ሊግ ውሳኔ እራሷን በማግለሏ ከኢትዮጵያ ምስጋናን ከግብጽ በኩል ደግሞ ወቀሳ ሲቀርብባት የነበረችው ሱዳንም አቋሟን ቀይራ የግድቡን ውሃ አሞላል በተመለከተ ከኢትዮጵያ የቀረበላትን ሃሳብ አልቀበልም ማለቷ ተሰምቷል። ይህ ጉዳይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች ዘንድ ብዙ አነጋግሯል።
የነፋስ ስልክ ልጆች በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረው አስተያየት «አሁን የሚታየው የግብፆች ጥናካሬ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ በሀሳብ ልዩነት አንድነታችንን መጠበቅ ባለመቻላችን የመጣ ነው።»ሲሉ አቤሜሌክ ንስር የተባሉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ «ከግበፅ ጋር የገባነውን ውዝግብ በአግባቡ ለመቋጨት የአገር ውስጥ ባንዶችን ከወዲሁ ቦታ ማስያዝ ያስፈልጋል።» ብለዋል።
አሚና ሙሀመድ ግን በዚህ ሀሳብ አይስማሙም «አሁን ከሁሉ አስቀድመን የውስጥ ችግራችንን ፈተን ለሀገራችን ቅድሚያ ሰጥተን መነጋገር ነው መቅደም ያለበት።ባንዳ እየተባባልን አንዳችን በአንዳችን ላይ ጣት መጠቋቆሙ የሚጠቅመው ግብፅን ብቻ ነው»ሲሉ ተችተዋል።
« ጃክ ማር» በሚል የፌስ ቡክ ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ «ሱዳን ከዳችም ተባበረችም ግድቡ እንደሁ መሞላቱ አይቀርም።» በማለት ፈርጠም ያለ ክንድ ከሚያሳይ ምስል ጋር አስተያየት አስፍረዋል።
ዳሎል አያና በበኩላቸው «የአባይ ግድብ ሁላችንም ከጉሮሮአች ቀንሰን የሰራነው ነው።የፈለገ ነገር ቢመጣ መቋረጥ የለበትም።ሙሌቱም መቀጠል አለበት።»ሲሉ፤ራሄል ዘውዱ የተባሉ አስተያየት ሰጭ «እንደ እኔ የሚያዋጣን እልህ ሳይሆን ሰላማዊ ድርድር ነው። ጦርነት «ኮሜንት» እንደመስጠት ቀላል አይደለም።ለዚያዉም በድህነት ላለች ሀገር።ጊዜው የዲፕሎማሲ ነው።መንግስታችን በውይይትና በዲፕሎማሲ ጉዳዩን ለመፍታት መበርታት አለበት።» የሚል ሀሳብ አቅርበዋል።
ጥሩ ብለሻል እህቴ በማለት ይጀምሩና «ግን አይመስለኝም ግብፅ እኮ እናንተ ያለመብራት ተቀመጡ። እኔ ግን አባይን ብቻዬን ተቆጣጥሬ ህዝቤን ልመግብ የምትል ናት።ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚለው ግብፅ ጋ አይሰራም።ይህ ደግሞ ያናድዳል።»ያሉት ደግሞ መብሬ ሀይለማርያም ናቸው።
ተስፋነሽ አዴቦ ደግሞ « እንደሀገር የውሃ ሀብታችን ሀገራዊና ተፈጥሯዊ ፀጋችን ነው። የዛሬው ብቻ ሳይሆን የነገም ተስፋችን መሠረትም ነው።ከድህነት ለመውጣት የውሃ ሀብታችን አቅማችን እንደሆነ ተገንዝበን ይህንን ሀብት ለመጠበቅ መንቀሳቀስ አለብን።»ብለዋል።
የሱዳንን አቋም በተመለከተ ሰላም ሙሉጌታ የተባሉ አስተያየት ሰጪ በፌስቡክ ገፃቸው ያሰፈሩትና ብዙዎች የተቀባበሉት ሀሳብ ደግሞ፤ ሱዳን የኢትዮጵያን ምክረ ሀሳብ ውድቅ ማድረጓን ይገልፁና «እግዲህ ይህ ማለት እንደ እኔ ምልከታ» በማለት ይቀጥላሉ።
«እግዲህ ይህ ማለት እንደ እኔ ምልከታ ሡዳን.........
ኢትዮጵያ ከሃምሌ ጀምሮ የግድቡን ውሃ ሙሌት ለመጀመር የያዘችውን እቅድ መቃወሟን፣ከቀደመ ፍትሃዊ አቋሟ ተንሸራታ ውግንናዋን ለግብፅ ማድረጓን፣፣ኢፍትሃዊው የዋሽንግተኑ ድርድር መቀጠል አለበት የሚል አቋም መያዟን፣ግብፅ የማትደግፈውን ምንም አይነት አማራጭ( የሡዳንን የሚጠቅም ቢሆንም) እንደማትቀበል፣በሶስተኛ አካል የሚካሄድ ድርድርን እንደምትደግፍ፣ከህግ እና ሳይንሳዊ ድርድር ይልቅ ፖለቲካዊ መፍትሄ ምርጫ ማድረጓን፣የሡዳን መንግስት ለጌዜያዊ የሃገሪቱ የፓለቲካ እና የኢኮኖሚ ቀውስ የህዳሴውን ግድብን የውጭ ድጋፍ መሸመቻ ወደ ማድረግ መሸጋገሩን እንዲሁም ፖለቲካዊ ወስልትና ውስጥ መግባቷን አመላካች ነው ።»
ዘይንያ ሁሴን በበኩላቸው፤ «ሀገር የሚፈርሰው በአላዋቂዎች ጩኸትና በአዋቂዎች ዝምታ ነው።ይባላል እባካችሁ በውጭ የምትኖሩ የኢትዮጵያ ሙህራን ድምፃችሁን አሰሙ።ለምሳሌ በአረቡ አለም ያለውን የሚድያ ክፍተት ብቻውን እየሞላ ያለው መሀመድ አል አሩሲ የተባለው ወንድማችን ነው።ምንም እንኳ በኢትዬጲያ በኩል ስለሱ ምንም ሲባል ባንሰማም ፤ስለ አባይ ሲጠየቅ የሚመልሳቸው መልሶች ግብጾችን ጥርስ ያስነከሰ ነው።ሌሎች ሙህራንም በዚህ መልኩ ለሀገራችሁ ብትሰሩ መልካም ነው።ግብፆች ይህንን በደንብ እየሰሩበት ነው።»በማለት አስተያየታቸውን ቋጭተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫና የህገ መንግስት ትርጓሜ
በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ማከናወን አለመቻሉን ቀደም ሲል አስታዉቋል። ይህ ጉዳይ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሲያወዛግብ የቆየ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉዳዩ የህገ መንግስት ትርጓሜ እንዲሰጥበት ለህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ መርቷል። ይህ የምርጫና የህገመንግስት ትርጓሜ ጉዳይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ ነው የሰነበተው።
ኢተል ብሩል የተባሉ አስተያየት ሰጪ«ለወጉ የህግ አማካሪዎችን አወያየን ሀሳብ ጠየቅን ለማለት ለይስሙላ ነው እንጂ ዝናብ ጠብ በለ ቁጥር ዣንጥላ መዘርጋት አስፈላጊ ሆና አይታየኝም ።»ብለዋል።
ግርማ ሽፈራው በበኩላቸው « ዶክተር አብይ በግድ ስልጣን ላይ ልቀመጥ አላለም። ምርጫው የሚራዘመዉ በጤና ጉዳይ ነዉ። ህገ መንግስቱም በቀጭነ ደብዳቤ ሲጣስ መቆየቱን ማሠብ ያስፈልጋል።የምን መጯጯህ ነዉ? ሲሉ፤
አብዱ ሰኢድ ደግሞ እንዲህ ይላሉ «እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የህገ መንግስት ፍረድ ቤት የላትም፡፡ በመሆኑም ስልጣን የተሰጠው ፌደሬሽን ምክር ቤት የፖለቲካው አካል በመሆኑ፤ ምን ያህል ገለልተኛና ሚዛናዊ ሰነድ ይዘጋጀል በሚል ህዝቡ ስጋት ስለገባው ነው። እያነጋገረ የሚገኘው፡፡»
ፈቃዱ አክሊሉ ደግሞ ህገመንግስቱ ይሻሻላል እንጅ አይተረጎምም በሚል ፅፈዋል።
«ህገ-መንግስቱ እንዲህ አይነት ነባራዊ አጋጣሚ/የኮሮና በሽታ/ ታሳቢ አላደረገም።እንዲህ አይነት ክስተት ሲያጋጥም ስልቱ ምንድነው ካልን ደግሞ አሁንም መፍትሄው ህገ-መንግስቱ ላይ ነው። ይህ ደግሞ ህገ-መንግስት ማሻሻል ነው። ህገ-መንግስትም ሆነ ህግ የሚሻሻለው ህጉ ያልሸፈነው አዲስ ፖለቲካዊ ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክስተት ለማካተትና የህግ መሰረት ለማስያዝ ነው።»
ያደቴ ካሊ ደግሞ«ይልቅስ እንደ ባቢሎናዉያን ቋንቋቸው የተደበላለቀው 108ቱ ፓርቲዎች እንዴት ቁጭ ብለው እንደሚያወሩና እንደሚስማሙ ከምርጫዉ በፊት ለምን አያሳዩንም»ብለዋል።
« ፓርቲዎች የሚያቀርቡት ሀሳብ ጠማማም ይሁን ቀና የሀሳብ ልዩነት ለህዝብ እንደቀረበ የምግብ ቡፌ ማለት ነው።ስለዚህ ፓርቲዎቹ ሀሳብ ማቅረባቸው ጥሩ ነው።»ለመሪዎችም ከስንፍናና ከዘራፊነት መጠበቂያ ነው።»ያሉት ደግሞ ፈይሰል አባድር ናቸው።
ዮናስ ተገኝ «ምርጫ አይታሰብም በአሁኑ ሰአት። ምርጫ ይኑር እንኩዋን ቢባል ማን ከማን ነው የሚመረጠው?»ሲሉ ጠይቀዋል።
የኮቪድ-19ን ስርጭት ለመከላከል የፖሊሶች ርምጃ
የኮቪድ-19ን ስርጭት ለመከላከል የሚመለከታቸው አካላት የሰጡትን የግንዛቤ ማስጨበጫና መንግስት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመተላለፍ ህዝብ በስፋት በሚገኝባቸው ቦታዎች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ሳይጠቀሙ ተገኙ ባላቸውና አካላዊ ርቀትን አልጠበቁም ባላቸው ሰዎች ላይ ፖሊስ ርምጃ እየወሰደ ነው።የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በዚህ ሳምንት አደረኩት ባለው ቁጥጥር ከ አንድ ሺ በሚበልጡ ሰዎች ላይ በአዋጁ መሰረት እርምጃ መውሰዱን ገልጿል። ይህ የፖሊስ ርምጃ «ድብደባና ማንገላታት የታከለበት ነው። » በሚል ብዙዎችን አነጋግሯል።
ሙስጠፋ ሀይረዲን « ማስክ ማድረግ የግድ ከሆነ ሳይነገር ሰዎችን ማሰር ለምን አስፈለገ? የግድ ነው ከተባለ ለሁሉም በሚድያ ሊነገር ይገባል ።»ሲሉ
ዳዊት ሩት ደግሞ «ቢያንስ በነጻ የሚታደልበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል። በድህነት ለሚኖር እና የእለት ዳቦ ፋላጊ ለሆነ ህዝብ በየቀኑ የሀያ ብር ማስክ መግዛት በጣም ይከብዳል»ብለዋል።
ወርቅነህ አላሮ በበኩላቸው«በወረርሽኙ ምክንያት በወንጀሉ የተፈረደበት እስረኛ ከወህኒ ለቆ ይህን ያህል ሰው ፤በማስክ ምክንያት አፍሶ ማሰር እርስ በርሱ ይጋጫል። ባይሆን ቀለል ባለ ቅጣት አንድ ስፍራ እንዳይሰባሰቡ መበተን ይሻላል።» የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
ውቤ ካን«እኛ ሰፈር ይሄ ህግ የተሰማም አይመስልም። ሰው ሲሄድም መጠጥ ቤት ሲገባም ሰብሰብ እንዳለ ነው። ጥንቃቄው ማንን እንደሚጠቅም ያወቅን አይመስልምና፤ ፖሊሶችዬ መበርታት አለባቸሁ።ነገር ግን ማንገላታትና ዱላን አይጨመርም።» ብለዋል።
«ጥሩ ነው ስራ ቀዝቀዝ ስላለ የሚበላ ከተገኝ እኛንም ከቤት እየወሰዳችሁ አሰሩን።»ያሉት ቀለመወርቅ ዉቤ ናቸው።
አስራት አሌኮ ደግሞ «በቁጥጥር ስር ማዋሉን ለጋራ ደህነት ሲባል ማስተማሪያ ብለን እንቀጥላለን ። ነገር ግን ዱላ ማስቀደሙ ለምን ተፈለገ ? ዱላዉ የወረርሽኙ አንዱ የመከላከያ ዘዴ መሆኑ ነው ?» ሲሉ ጠይቀዋል።
አዲሱ መካሻ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ እንዲህ ብለዋል።
«የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የአፍና የአፍ መሸፈኛ አልተጠቀማችሁም። ተራርቃችሁ አልሄዳችሁም። በሚል የአዲስ አበባ ፖሊሶች በጅምላ እያሰሩ ነው።እሽ ለሰው ጤንነት ከመጨነቅ ከሆነ መልካም ግን ዱላን ምን አመጣዉ።ለምሳሌ ትናንት በፖሊስ ሲያዙ ከየኋቸው ሰዎች መካከል አንዱ ወጣት አፍንጫው ደም በደም እስኪሆን ነው የደበደቡት።ለመሆኑ ኮሮናስ ቢሆን ለዚህ ወጣት ከዚህ የከፋ ጉዳት ሊያደርስበት ይችላልን?»
መሰለ ቱፋ በበኩላቸው «እኔ የሚገርመኝ አልተራራቃችሁም ብለው ከያዙን በኋላ ሁላችንም አንድ ላይ በመኪና ጭነው የሚወስዱት ነገር ነው።»በማለት ተችተዋል።
ገረመው ግዛዉ «ከመብት በፊት ህይወት የቀድማል፡፡ አጉል ቂቤ መሆን አግባብ አይመስለኝም፡፡ አሁን ዝም ቢባል ነገ k,n,g, w,diia መንግሥት ህዝብ ጨረሰ ብለህ መጮህህ ስለማይቀር ፤ህይወት ማትረፍ ይቀድማል፡፡»ሲሉ፤ «በከተማዋ ውስጥ ቁጥጥር ከመደረጉ በፊት በቂ የፊት መሸፈኛ ማስክ ቀርቦ ነው ወይንስ …. ???»ያሉት ክፍሌ ገብረአረጋዊ ናቸው።
« መደብደቡን እቃወማለሁ ነገር ግን ከህዝብ ጤንነትና ደህንነት ኣንፃር ኣይተው የተመጣጠነ እርምጃ መውሰዱን እደግፋለሁ ይህንን የምለው በኣንዱ ቸልተኝነት ሌላው ለኣደጋ መጋለጥ ስለሌለበት ነው»ያሉትተስፋዬ ከበደ ናቸው።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም ኮሮናን ለመከላከል በሚል በፀጥታ ሀይሎች እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች በመኮነን መግለጫ አውጥቷል።ኮሚሽኑ የፖሊስ የዘፈቀደ እስር በአስቸኳይ እንዲቆምና የታሰሩትም እንዲሊቀቁ ጠይቋል።