1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቱኒዚያ ፖለቲካዊ ቀዉስ

ሰኞ፣ ሐምሌ 26 2013

ቀዉሱን ለማስወገድ ኢነሕዳ ከፕሬዝደንቱ ጋር ለመደራደር ጠይቋል። እስከ ዛሬ ግን ፕሬዝደንቱ ጥያቄዉን አልተቀበሉትም። ፕሬዝደንቱ የድርድር ጥያቄዉን እንቢኝ ብለዉ በያዙት ርምጃ ከቀጠሉ ግን ጋኑቺ እንደዛቱት፣የሕዝባዊ አመፅ አብነቲቱ ሐገር አዉራ ጎዳኖች ዳግም በሕዝብ ጎርፍ ይጥለቀለቃሉ።

https://p.dw.com/p/3yRgL
Tunesien Tunis | Proteste | Rached Ghannouchi
ምስል picture alliance / ASSOCIATED PRESS

ቱኒዚያ ከጅምር ዴሞክራሲ ወደ አዲስ ዉዝግብ


የያኔዉ የ26 ዓመት ወጣት ታሪክ ኤል-ጠይብ መሐመድ ቡአዚዝ ታኅሣስ 17፣ 2010 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) እራሱ ላይ የለኮሳት እሳት ሕይወቱን አጥፍታ፣ የቱኒዚያን ሕዝባዊ አብዮት ስታቀጣጥል እሳቸዉ ካይሮ-ግብፅ የአረብ ሊግ ዕዉቅ የሕግ ባለሙያ ነበሩ።ካይስ ሰይድ።በዉልደት፣ ዕድገት፣ ትምሕርት፣ ዕዉቀት፣ ሥራቸዉ ከቡአዚዝ፣ከዚይን ኢል አቢዲን ቤን ዓሊ፣ ከአብዱል ፈታሕ አል ሲሲም ይልቅ ለመሐመድ ሙርሲ ይቀርባሉ።ፕሮፌሰር ነበሩ።ቡአዚዝ እራሱን  ያጋየበት 9ኛ ዓመት ሊዘከር ጥቂት ሲቀረዉ ቤን አሊ በዉርስ፣ ሙርሲ በምርጫ፣ አልሲሲ በመፈንቅለ መንግስት የያዙትን ዓይነት ሥልጣን በምርጫ ያዙ።ጥቅምት 2019።ፕሬዝደንት።ባዓመት ከመንፈቃቸዉ ዘንድሮ የሚሉ-የሚያደርጉት ግን ከቡአዚዝ አርማ አንሺነት፣ ከሙርሲ ጅምር ቀጣይነት ይልቅ የአል ሲሲን ፈለግ መከተላቸዉ እንዳይሆን አስግቷል።ሥጋቱ መነሻ፣ የሰዉዬዉ ርምጃ ማጣቃሻ፣ የቱኒዚያ ጅምር ዴሞክራሲ ወዴትነት መድረሻችን ነዉ።
                                       
የዚያን ምስኪን አትክልት ቸርቻሪ ወጣት አስፈሪ ግን ድንቅ መስዋዕትነት አረብ-ከአፍሪቃ ተከትሎታል።አይሁድ ከአረብ፣አዉሮጳ ካሜሪካ ኮፊያ፣ ቆብ ባርኔጣዉን እያወለቀ አድንቆታል።ዘክሮታልም።
ከብዙዎቹ የአረብ ሐገራት ዘግየት ብለዉ በ2015 ግድም ኦሮሚያ ላይ እንደ ቡአዚዝ ጭቆናን እንቢኝ ብለዉ ያመፁ ወጣቶች በከፈሉት የሕይወት፣ የደም፣ አካል መስዋዕትነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያስረከቡት የበጎ ለዉጥ ተስፋ መክሸፍ-አለመክሸፉ እንደየተመልካቹ የተቃራኒ አስተያየት ምንጭ ከሆነ ከረመ።
ለዉጡና ተስፋዉ የመቀጠል-መጨናጎሉ እንዴትነት አነታረከም፣ አከራከረ ኢትዮጵያዉያን ዛሬም በጦርነት፣ግጭት፣እየተገደሉ፣እየተፈናቀሉ፣እየተራቡ ነዉ።
ቡአዚዝ ራሱን ባቀጣጠለ ማግስት ድፍን ቱኒዚያ ላይ እንደሆነዉ ሁሉ ግብፅ ዉስጥ  የተቀጣጠለዉ ሕዝባዊ አመፅ ከ1950ዎቹ ጀምሮ ካይሮ ላይ የፀናዉን መለዮአቸዉን ያወለቁ የጦር ጄኔራሎች አገዛዝ አስወግዶ በሕዝብ ድምፅ የመጀመሪያዉን የሲቢል መሪን ለስልጣን አብቅቶ ነበር።ግን ባፍታ ፊልድ ማርሻል አብዱል ፈታሕ አልሲሲ በመፈንቅለ መንግስት ቀጩት።2013።
እንደ ቱኒዚያና ግብፅ ሁሉ ሊቢያ ላይ የተቀጣጠለዉ ሕዝባዊ አብዮት በፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኒካላ ሳርኮዚ ፊት አዉራሪነት የዘመተዉ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) ጡቻ በእንጭጩ አምክኖ ያቺን ሐብታም፣ ሰፊ፣ ሐገር ለወርሮበሎች አስረክቦ፣ሕዝቧን የተገደሉ አምባገነን ገዢዉን ናፋቂ አድርጎታል። 
የሞስኮ-ደማስቆ ገዢዎች የሶሪያን፣ የሪያድ-አቡዳቢ ጎረምሶች የየመንን ሕዝብ ንቅናቄ አክሽፈዉ ጥንታዊዎቹን ሐገራት ከትቢያ ሲቀይጧቸዉ እንዳጀማመሩ የዘለቀዉ የቱኒዚያዉ ለዉጥ ብቻ ነበር።የቱኒዞችን ድል፣ የትግሉ አራማጅ፣ የድል ማግስት መሪዎችን ያመራር ጥንቃቄና ብስለት፣ የእነ አል ሲሲን ቅልበሳ፣ የሊቢያ፣ የሶሪያንና የየመንን ዉድመት በቅርብ ከመከታተል ባለፍ ፖለቲካን ሳይጠጉ-ሕግን እያስተነተኑ፣ከሐገራቸዉ ርቀዉ ካይሮ ነበሩ።ካይስ ሰይድ። 
ጥቅምት 2019 ፕሬዝደንት ሆኑ።ባለፈዉ ሳምንት የሐገሪቱን ጠቅላይ ሚንስትር ከነ-ካቢኔያቸዉ ከስልጣን አባረሩ።በሕዝብ ምርጫ የተሰየመዉን ምክር ቤትም አገዱ።ሲሲን፣ሳርኮዚን፣ አሰድን፣ ወይም ቢን ሰልማንን መሆናቸዉ ይሆን? የቱኒዚያ ትልቅ የፖለቲካ ፓርቲ የኢነሕዳ መሪና የታገደዉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ረሺድ ጋኑቺ «መፈንቅለ መንግስት» ለማለት አላመነቱም።
ምዕራባዉያን እንደ ግብፁ ሙስሊም ወንድማማቾች ወይም እንደ ቱርኩ የፍትሕና የልማት ፓርቲ (AKP) ሁሉ «እስላማዊ» የሚሉት የቱኒዚያዉ ኢነሕዳ ፓርቲ በሕዝባዊዉ አብዮት ወቅት ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል።የቤን ዓሊ አምባገነናዊ አገዛዝ ከተወገደ በኋላ በሐገሪቱ ያቆጠቆጠዉን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እየጠጋገነም ቢሆን የመራም ፓርቲም ነዉ።
ፕሬዝደንት ሰይድ ባገዱት ምክር ቤት በርካታ መቀመጫዎች አሉት፣ ጠቅላይ ሚንስትር ሐሺም ማሺሺን ጨምሮ ፕሬዝደንቱ የሻሩት ካቢኔ አብዛኛ ሚንስትሮችም የፓርቲዉ አባላት ወይም ደጋፊዎች ናቸዉ።የፓርቲዉ መሪ ረሺድ ጋኑቺ «መፈንቅለ መንግስት» ማለታቸዉን ፕሬዝድንት ካይስ ሰይድ «በየትኛዉ» የሕግ አንቀፅ? በማለት ይጠይቃሉ።ሰይድ አዉጋዥ-ተቺዎቻቸዉን ሕግ «ተማሩ» ብለዋቸዋልም፣ የሕገ-መንግስታዊ ፕሮፌሰር አልነበሩ?
 «አንዳዶች ትናንት ሥለ መፈንቅለ መንግስት አዉርተዋል።የትኛዉ የሕግ ወይም የፖለቲካ ሳይንስ ትምሕርት ቤት እንደተማሩ አላዉቅም።መፈንቅለ መንግስት እንዴት በሕገ-መንግስት ላይ ሊመሰረት ይችላል?ይሕ የሕገ-መንግስቱን ፅሁፍ ገቢር ማድረግ ነዉ።ፕሬዝደንቱ የማይቀር አደጋ መኖሩን ሲገነዘብ እርምጃ እንዲወስድ ሕገ-መንግስቱ በአንቀፅ 80 ሥልጣንና ኃላፊነት ሰጥቶታል።»
ፕሬዝደንቱ «የማይቀር» አደጋ ያሉት ሐገሪቱ ዉስጥ የሥራ አጥ ቁጥር መብዛቱ፣የኑሮ ዉድነት ማሻቀቡና በተለይ የኢነሕዳ ደጋፊና ከፓርቲዉ ጋር ግንኙነት አላቸዉ የሚባሉ ነጋዴዎች ጠቀም ያለ ገቢ ያገኛሉ መባሉን ነዉ።
ለሥራ አጡ ቁጥር መበራከትና ለኑሮ መወደድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም ከመንግስት ባለስልጣናት እርምጃ ይልቅ  የኮሮና ተሕዋሲ መሰራጨቱ ዋነኛዉ ምክንያት እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ።ትንሺቱ ግን ሥልታዊቱ ዉብ ሰሜን አፍሪቃዊት ሐገር ከሐገር ጎብኚዎች ጠቀም ያለ ገቢ ታገኝ ነበር።
በ2008 ከሐገር ጎብኚዎች ያገኘችዉ ገቢ 10 ቢሊዮን ዶላር ሊደፍን ጥቂት ነበር የቀረዉ።በሕዝባዊ አብዮቱ ወቅት ከተቀዛቀዘ ወዲሕ በ2019 እንደገና ማንሰራራት ጀምሮ ዓመታዊ ገቢዉ 6.2 ቢሊዮን ዶላር ደርሶ ነበር።የኮሮና ተሕዋሲ ወረርሺኝ የዓለምን እንቅስቃሴ ሲያሽመደምደዉ የቱኒዚያን ገቢም ባፍጢሙ ደፋዉ።ያም ሆኖ የኢነሕዳ መሪ ጋኑቺ ለደረሰዉ ምጣኔ ሐብታዊ ኪሳራ ፓርቲያቸዉ በከፊል ተጠያቂ መሆኑን አምነዋል።
                                             
«በምጣኔ ሐብቱና በማሕበራዊዉ መስክ ስሕተቶች ተፈፅመዋል።ኢነሕዳ በያዘዉ ሥልጣን ልክ ሐላፊነቱን ይወስዳል።»
የተቀረዉ ኃላፊነት የፕሬዝደንቱና የሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ነዉ-ጋኑቺ እንደሚያምኑት።የኮሮና ተሕዋሲ ወረርሺኝ  ቱኒዚያ ዉስጥ 18 ሺሕ ሰዉ ገድሏል።ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ በተሕዋሲዉ ተይዟል።12 ሚሊዮን የማይሞላ ሕዝብ ያላት ቱኒዚያ በርካታ ሕዝብ በተሕዋሲዉ ከተያዘባቸዉ ጥቂት የአፍሪቃና የአረብ ሐገራት አንዷ ናት።
ኮሮና ሲሰራጭ፣ ሰዉ ሲገድል፣ሲለከፍ፣ የሐገሪቱን ምጣኔ ሐብት ሲያሽመደም የሕገ-መንግሥት ፕሮፌሰሩ የቱኒዚያ ፕሬዝደንት ነበሩ።ተሕዋሲዉ ላደረሰዉ ጉዳትና ጥፋት ባለስልጣናት ተጠያቂ ከሆኑ ፕሬዝደንቱም በያዙት ስልጣን ልክ ተያቂ የማይሆኑበት አመክንዮ የለም።
ሰዉዬዉ ግን ኃላፊነት መዉሰድ አይደለም ተቃዋሚዎቻቸዉን ሁሉ አንድም ወሕኒ ቤት አለያም ሕግ ትምሕርት ቤት ሊያስገቡ የቆረጡ ይመስላሉ።ዋና ተቺያቸዉ የነበሩ አንድ የምክር ቤት እንደራሴን ባለፈዉ አርብ፣ ቅዳሜ ደግሞ አንድ ዕዉቅ ዳኛን አሳስረዋል።የመገናኛ ዘዴዎች ቢሮዎችን ዘግተዋል።የተቀሩትን «ሕግ ተማሩ»-እያሉ ነዉ-ሕግ አዋቂ ዳኛ ያሰሩት የሕግ-ፕሮፌሰር።
                                          
«ዛሬ ኃላፊነቴ የሚጠይቀዉን አድርጌያለሁ።የወሰድኩት ታሪካዊ ኃላፊነት ነዉ።ጉዳዩ ከመፈንቅለ መንግሥት ጋር ይገናኛል የምትሉ ወገኖች የሕገ-መንግስታዊ ትምህርታችሁን እንድታድሱ እጠይቃለሁ»
ቀዉሱን ለማስወገድ ኢነሕዳ ከፕሬዝደንቱ ጋር ለመደራደር ጠይቋል።እስከ ዛሬ ግን ፕሬዝደንቱ ጥያቄዉን አልተቀበሉትም።ፕሬዝደንቱ የድርድር ጥያቄዉን እንቢኝ ብለዉ በያዙት ርምጃ ከቀጠሉ ግን ጋኑቺ እንደዛቱት፣የሕዝባዊ አመፅ አብነቲቱ ሐገር አዉራ ጎዳኖች ዳግም በሕዝብ ጎርፍ ይጥለቀለቃሉ።
                                       
«ምክር ቤቱ ካልተከፈተ፣መንግስት ካልተመሰረተና ለምክር ቤቱ ተጠሪነቱን ካልቀጠለ የቱኒዚያ ጎዳኖች መነቃነቃቸዉ ምንም ጥርጥር የለዉም።እኛም የቱኒዚያ ሕዝብ ዴሞክራሲዉን ከጥፋት እንዲከላከል ጥሪ እናደርግለታለን።በምክር ቤቱ ላይ የተጣለዉን እገዳ እንዲቃወም እንጠይቃለን።ፕሬዝደንቱ የምክር ቤቱን አዳራሽ ቆልፈዉታል፣ በሩ ላይ  ታንክ አቁመዋል።ይሕ በጣም አደገኛ ስሕተት ነዉ።»
ቱኒዚያ ካዲስ ፖለቲካዊ ቀዉስ የገባችዉ፣ ጎረቤትዋ ሊቢያ ካስር ዓመት ምስቅልቅል፣ ጥፋት፣ ዉድመት በኋላ ወደመረጋጋት የማምራትዋ ፍንጭ ብልጭ ባለበት ወቅት ነዉ።ሳርኮዚን አምነዉና ተከትለዉ ሊቢያን የማጥፋታቸዉ ዳፋ ለራሳቸዉ የተረፋቸዉ የሰሜን አትላንቲካ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት አባል ሐገራት በተለይም የሜድትራኒያን ባሕርን የሚዋስኑት አዉሮጶች የቱኒዚያዉ ቀዉስ ሲበዛ ያሳጋቸዉ መስለዋል።
ቀዉሱ ተባብሶ ሌላ የስደተኞች መተላለፊያ በር እንዳይከፍት ለማድረግ አዉሮጶች በፖለቲካ-ዲፕሎማሲዉ እየተራወጡ ነዉ።የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ግንኙነት ኃላፊ የጆሴፍ ቦርየል ቃል አቀባይ ነቢላ መስራሊ ግን ሕብረታቸዉ ጉዳዩን በቅርብ እየተከታተለ ነዉ ከማለት ባለፍ የሕብረታቸዉን የስጋት ደረጃ አልጠቀሱም።
                                  
«ለማድረግ የምንሞክረዉ ሁኔታዉን በቅርብ እየተከታተልን ነዉ።ከአቻችን ጋር እየተነጋገርን ነዉ።የሕብረቱ የዉጪ ግንኙነት  ኃላፊ ጆሴፍ ቦርየል ከቱኒዚያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጋር ተነጋረዋል።ከሕብረቱ አባል ሐገራት ጋርም እየተመካከሩ ነዉ።»
ዩናይትድ ስቴትስም ቱኒዚያ ባስቸኳይ ወደ ዴሞክራሲዊና የሕግ የበላይነት ሥርዓት እንድትመለስ ጠይቃለች።የአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊክን ከፕሬዝደንት ካይስ ሰይድ ጋር መነጋገራቸዉ ተዘግቧልም።
የካይሮ መሪዎችም እንደዲፕሎማሲዉ ወግ የቱኒዚያን ጉዳይ በቅርብ እየተከታተልን ነዉ ማለታቸዉ አልቀረም።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሳሚ አል ሽኩሪ ባለፈዉ ቅዳሜ የአልጄሪያ አቻቸዉን ራማታን ላማራን ሲነጋግሩ እንዳሉት ግብፅ በቱኒዚያ ፖለቲከኞች ላይ ፅኑ ዕምነት አላት።
                          
«የቱኒዚያ ባለሥልጣናት ፀጥታን፣ መረጋጋትን እና የቱኒዚያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የሚያደርጉትን በከፍተኛ ፍላጎት እየተከታተል ነዉ።የቱኒዚያ ፖለቲካዊ አመራር የሐገሪቱን ሕዝብ ፍላጎት ለማሟላት ያለዉን ብልሐት፣ ብቃትና ሁኔታዉን የመቆጣጠር አቅሙን ሙሉ በሙሉ እንተማመናል።የአልጄሪያዉ ሚንስትር እንዳሉት ጉዳዩ የቱኒዚያ የዉጥ ጉዳይ ነዉ።»
ፕሬዝደንት አል ሲሲ፣ ከአረብ ኤምሬቶች ነገስታት ጋር ሆነዉ የሊቢያዉን የጦር አበጋዝ ኸሊፋ ሒፍጣርን በግልፅ ይደግፋሉ።የፕሬዝደን ካይስ ሰይድን እርምጃ መደገፍ-መቃወማቸዉ ግን ግልፅ አይደለም።እዚያዉ ቱኒስ ሰይድን የሚደግፉና የሚቃወሙ ሰልፈኞች ባለፈዉ ሳምንት አደባባይ ወጥተዉ ተጋጭተዉ ነበር።በግጭቱ ጥቂቶች ከመፈከታቸዉ በስተቀር የደረሰ ከባድ ጉዳት የለም።የግራ-ቀኝ ሰልፈኛዉ ቁጥርም አነስተኛ ነበር።
ይሁንና የፖለቲከኞቹ ሽኩቻ እንዳጀማመሩ ከቀጠለ ቱኒዚያዉያን እንደገና አደባባይ መዉጣታቸዉ አይቀርም።ላለፉት 10 ዓመት በመልካም ጎዳና ሲጓዝ የነበረዉ የቱኒዙያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደ ግብፅ መቀልበሱ፣ እንደ ሊቢያ፣የመንና  ሶሪያዎች የሐገር ጥፋትና ዉድመት ማስከተሉ በዉል አይታወቅም።ጉዞ መንገራገጩ ግን አንድ ሁለት አላሰኘም።

Tunesien Frauen protestieren gegen die Regierung in Tunis
ምስል picture-alliance/abaca/F. Nicolas
Rachid Ghanouchi
ምስል AP
Tunesien I Präsident Kais Saied
ምስል Slim Abid/AP/picture alliance

ነጋሽ መሐመድ 

ሸዋዬ ለገሠ