1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቱርክ ጦር ዘመቻ በሶሪያዋ አፍሪን ግዛት

ሰኞ፣ ጥር 14 2010

በሳምንቱ መጨረሻ የቱርክ የምድር ጦር ኃይሎች በሰሜን ሶሪያ ወደምትገኘው አፍሪን ግዛት ገብተው የከፈቱትን የጥቃት ዘመቻ ቀጥለዋል። ዘመቻው ቱርክ አሸባሪ ድርጅት ብላ በሰየመችው በኩርዳውያኑ የሚሊሽያ ቡድን (YPG) ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ትገልጻለች።

https://p.dw.com/p/2rJ2F
Türkei Grenze Syrien Artilleriebeschuß Operation Olivenzweig
ምስል Getty Images/AFP/B. Kilic

የቱርክ ጦር ዘመቻ በሶሪያዋ አፍሪን ግዛት

በቱርክ ጎረቤት ሀገር ሶርያ ጦርነቱ ቀጥሏል።  ጦርነቱ ግን ከቅዳሜ አንስቶ በቱርክ ጦር እና ቱርክ አሸባሪ ድርጅት ብላ በፈረጀችው በኩርዶች የሚሊሽያ ቡድን በምህጻሩ (YPG) መካከል ነው።  የቱርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢናሊ ይልድሪም እንደገለፁት የቱርክ ጦር ሶርያ ውስጥ በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ ያቀደው 30 ኪሎ ሜትር የሚያክል የፀጥታ ቀጣና ነው። የኩርዶች የሚሊሽያ ቡድን በበኩሉ ታይል ላይ አፀፋውን ሰሜን ሶርያ ውስጥ ጀምሯል። የሶርያ የሰብዓዊ መብቶች ታዛቢ ቡድን ዛሬ ይፋ እንዳደረገው የቱርክ ጦር በእጁ አስገብቶት የነበረውን አካባቢ የኩርድ አማፂያን መልሰው ተቆጣጥረውታል። የኩርድ ሚሊሽያ በዩናይትድ ስቴትስ እንደሚደገፍ ይነገራል፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ በYPG ይመራል የሚባለው የሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎችን 30,000 ሰዎች የማሰልጠን እቅድ እንዳላት ይፋ አድርጋ ነበር።ይህ ቡድን ቅዳሜ ዕለት በቱርክ ጦር በተጀመረው ጦርነት ኢላማ ሊሆን የቻለውም ዩናይትድ ስቴትስ ከቡድኑ ጋር ጥምረት መፍጠሯ ቱርክ ለደህንነቷ አስጊ ሆኖ ስላገኘችው እንደሆነ ሁሴይን ባክጂ ይገልጻሉ። ባክጂ አንካራ በሚገኝ ዮኒቨርሲቲ የዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ፕሮፌሰር ናቸው።« YPG ወይም የኩርዱ ቡድን ከ PKK ማለትም ከኩርድ ሠራተኞች ፓርቲ ጋር ግንኙነት አለው። የቱርክ መንግሥት ከጥቂት ቀናት አንስቶ የቱርክ ድንበርን አሸባሪ ቡድን ሊቆጣጠረው አይገባም የሚል አቋም ይዟል። ይህ ደግሞ ከብሔራዊ ጥቅም አቋም ሲታይ ይገባል።» 

YPG - Kurdische Miliz
የኩርድ የሚሊሽያ ቡድን (YPG) ምስል Getty Images/AFP/B. Kilic

900 ኪሎ ሜትር ርዝመት ካለው የቱርክ እና ሶርያ ድንበር 700 ኪሎ ሜትር ያክሉ የኩርዶች ጠንካራ ሰፈር ነው።  ሰሜን ምዕራቡ የአፍሪን አካባቢ ደግሞ ያሉት ኩርዶች ሁለት የተከፈሉ ናቸው። ይህ ቱርክ ጦርነቱን እንድታሸንፍ ዕድል ያመቻችላታል የሚሉት ደግሞ የመካከለኛው ምሥራቅ የጥናት ማዕከል ባልደረባ ኦይቱን ኦርሀን ናቸው። «በአፍሪን አካባቢ ነገሮች አመቺ እንደሆኑ ቱርክ ታስባለች። ስፍራው ከሌሎች ስፍራዎች ጋር ሲነፃፀር ገለል ብሎ የሚገኝ ቦታ ነው። በእዛ ላይ ዕድሜ ለሩሲያ ትብብር። ዘመቻው ከሩሲያ እና ከኢራን ጋር ሊወሰን ይችላል።»
እርግጥ ነው በቱርክ እና እና በሩሲያ መካከል ስምምነት ተደርሷል ተብሎ ይታመናል። የቱርክ ጦር ቅዳሜ ዕለት ሰሜን ሶሪያ ወደምትገኘው አፍሪን ግዛት ከመዝመቱ ቀደብ ብሎ የሩሲያ ወታደሮች አካባቢውን ለቀው ወጥተዋል።

Türkei Kilis Raketenangriff aus Syrien
የቱርክ ጥቃት ምስል picture-alliance/abaca/C. Erok

የቱርክ ፕሬዝዳንት ራቺብ ጣይብ ኤርዶኻን “ፈጣሪ ከፈቀደ ዘመቻችንን በፍጥነት እናጠናቅቃለን ፣ PKKንም ይሁን YPG እናጠፋቸዋለን።» ሲሉ እሁድ ዕለት ተናግረዋል። የቱርክ ጦር እንደሚለው በዚሁ ዘመቻ ከ150 በላይ የኩርድ ሚሊሽያ ቡድን ስፍራዎችን በሮኬት ደብድቧል። እንደ ኩርድ መረጃ ደግሞ 10 ሰዎች ተገድለዋል። ከነዚህ ውስጥም ሲቪሎች ይገኙበታል።  ቱርክ  ካለፉት ሦስት ቀናት ወዲህ ሰሜን ሶርያ ውስጥ በኩርዶች ላይ በመውሰድ ላይ የምትገኘውን ርምጃ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት አሳሳቢ ነው ብሎታል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን የቱርክ ስጋት አግባብ ቢሆንም ሀገሪቱ ሲቪሎችን ከማጥቃት እንድትቆጠብ አሳስበዋል። አክለውም ሚኒስትሩ የጥቃቱ ሁሉ ዋና አላማ ራሱን እስላማዊ መንግሥት እያለ የሚጠራውን ቡድን መዋጋት መሆን እንዳለበት አሳስበዋል። እንደ ፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዣን ኢቭ ሌ ድሪያን ከሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ሶርያ ውስጥ በከረረው ጉዳይ ላይ በቅርቡ መምክር ይሻል።

ክርስቲያን ቡትኬራይት/ ልደት አበበ 

ሸዋዬ ለገሰ