1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአንድነት ድልድይ

ሰኞ፣ ኅዳር 1 2012

ጀርመን በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ጥቅምት 3 ቀን 1990 ዓም ከተዋሀደች በኋላ በቬራ ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይ በተደጋጋሚ ዕድሳት ተደርጎለታል። ዛሬ ከፋራ ወደ ፍሊፕስታይ አሊያም በተቃራኒው የሚጓዙ እግረኞች እና ሳይክል ጋላቢዎች የሚጠቀሙበት የአንድነት ድልድይ ተብሎ ይጠራል።

https://p.dw.com/p/3R2St
Brücke der Einheit in Vacha
ምስል DW/E. Bekeler

«የአንድነት ድልድይ»


በቬራ ወንዝ ላይ የተገነባው እና 225 ሜትር የሚረዝመው ድልድይ ከ30 አመታት ገደማ በፊት ከወታደሮች በቀር የሚሻገርበት አልነበረም። የሔሰ እና የቱሪንጊያ ግዛት ሰዎችን ለማገናኘት ከ650 አመታት በፊት ይገንባ እንጂ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ግብሩን ተነጥቆ በስሙ ብቻ ቀርቶ ነበር።

የፋራ ከተማ ከንቲባ ማርቲን ሙለር "ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ሩሲያውያን እና አሜሪካኖች መጡ። እኛም ተከፋፈልን። ፋራ በሶቭየት ኅብረት ተያዘች። ፊሊፕስታይል በአሜሪካኖች እጅ ገባች። የሶቭየት ኅብረት ቀጠና እና የአሜሪካ ቀጠና ብለው በከፋፈሉት መካከል ግምብ አበጁ። ወዲያው ይኸ ድልድይ የክፍፍሉ አካል ሆነ" ሲሉ ይናገራሉ።

ፋራ በቱሪንጊያ ግዛት በኩል የምትገኝ ከተማ ስትሆን በምሥራቅ ጀርመን ውስጥ ነበረች። በሔሰ ግዛት በኩል የምትገኘው ፍሊፕስታይል ከተማ በአንጻሩ የምዕራብ ጀርመን አካል ሆና ቆይታለች።

ማርቲን ሙለር እንደሚሉት ከሁለቱ ከተሞች በቬራ ወንዝ ላይ የተገነባውን ድልድይ ማቋረጥ ለቤተሰብ አባላት ጭምር ሳይቻል ቆይቷል
"የቅርብ ዘመዶቻችን እንኳ መጥተው ሊጠይቁን አይችሉም። ዘመድ መጠየቅ ካለብን ከሁለት እና ከሶስት ሳምንታት በፊት አስቀድመን ፈቃድ መጠየቅ ግዴታችን ነው። እርሱም ቢሆን አብዛኛውን ጊዜ ይከለከላል"
እንዲህ አይነቱ አስገዳጅ ሁኔታ ግን እንደ ኩበሪሽ ላሉ የዘመኑ ሰዎች በቀላሉ ተቀባይነት የሚያገኝ አልነበረም። ከባለቤታቸው ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው በቬራ ወንዝ ላይ በተገነባው ድልድይ ከፊሊፕስታይል ወደ ፋራ ሲሻገሩ ያገኘኋቸው ኩበሪሽ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጀርመንን ለሁለት የከፈላትን ቀዝቃዛው ጦርነት "በአገሬ እንግዳ አድርጎኝ ነበር" ሲሉ ይገልጹታል።
በፊሊፕስታይል ተወልደው ያደጉት ኩበሪሽ ወደ ፋራ እንዳይሻገሩ በቬራ ወንዝ ላይ የተዘጋባቸውን አመታት አምርረው ይጠላሉ። ለዚያም ይመስላል የበርሊን ግንብ ፈርሶ ክልከላው ሲነሳ ድልድይ ለመሻገር ቀዳሚ ለመሆን የሞከሩት።
"ሁሉም ነገር የተፈጠረው ከረዥም አመታት በፊት ነው" ይላሉ ኩበሪሽ።
"አሁን ሁሉም ነገር አልፏል። በውኅደቱ ዕለት ከድልድዩ በተቃራኒ ብቻዬን ቆሜ ነበር። በአካባቢው የነበሩትን ‘ምን ሆናችኋል? ድልድዩ የአንድነት ሆኗል። ኑ ተቀላቀሉ’ እያልኩ ጠራኋቸው። ማንም ከቁብ የቆጠረኝ አልነበረም" ሲሉ ኩነቱን ያስታውሳሉ።
ጀርመን በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ጥቅምት 3 ቀን 1990 ዓም ከተዋሀደች በኋላ በቬራ ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይ በተደጋጋሚ ዕድሳት ተደርጎለታል። ዛሬ ከፋራ ወደ ፍሊፕስታይ አሊያም በተቃራኒው የሚጓዙ እግረኞች እና ሳይክል ጋላቢዎች የሚጠቀሙበት የአንድነት ድልድይ ተብሎ ይጠራል።
ማርቲን ሙለር "ግንቡ ከፈረሰ በኋላ ሁሉም ነገር ወደነበረበት ተመልሷል። እንደ ሌሎች ከተሞች ሆኗል። ወደፈለግንበት መሔድ እንችላለን። የፈለገም መምጣት ይችላል" ሲሉ ተናግረዋል

Brücke der Einheit in Vacha Herr Küberich
ምስል DW/E. Bekeler
Brücke der Einheit in Vacha Bürgermeister Martin Müller
ምስል DW/E. Bekeler
Brücke der Einheit in Vacha
ምስል DW/E. Bekeler

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ