1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተከታዩን ትውልድ አቅም ማጠናከር

ዓርብ፣ ጥር 7 2013

ጥቂት ወጣቶች የወጣቱ በማኅበራዊ መገናኛ ጎራ እየለየ መጨቃጨቅ በዝቶ ቢመለከቱ "Empower The Next Generation" የተባለ ሀገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በመመስረት ወጣቶች በውስጣቸው ያለውን አቅም አውጥተው ራእያቸውን መኖር እንዲችሉ የሚያግዙ ስልጠናዎችን የሚሰጥ፣ የሚያነቃቃና የሚያበረታታ ሁኔታና ዕድልን መፍጠር ችለዋል።

https://p.dw.com/p/3nz8Q
Äthiopen ENG Empowering the next Generation
ምስል Solomon Muchie/DW

የተከታዩን ትውልድ አቅም ማጠናከር


ከምታደርገው ይልቅ የምታስበው እጅጉን ወሳኝ ነው የሚሉት መርህ በተለይም ለወጣቶች የላቀ ወሳኝና ጠቃሚ ነው። ወጣቶች ራሳቸውን ፈልገው ካገኙ ተዓምር የተባሉ ግኝቶችን መፍጠራቸው አይቀርም። ግን ደግሞ ራስን ፈልጎ ማግኘት እንዲሁ ቀላል ተግባር እና ሀሳብ አይደለም። ለዚህም ነው ሰዎች አካባቢ እና ዓለምን የሚያዩበት መነፅር የሚወልዳቸው አመለካከቶች ዝንባሌ እና ልምምዶች በወጣትነት ጊዜ ብዙ መልክ ያላቸው ሆነው የሚገኙት።
ወጣትነት በሰው ልጅ ዕድሜ ውስጥ የስኬትም ሆነ የውድቀት ማብሪያ ማጥፊያ ነው። ወጣትነት እንደ ቤት ይታነፃል። ይሠራልም። እንደ ብርጭቆ ከወደቀ ለመጠገን በሚያስቸግር ሁኔታም ሊሰበር ይችላል። አቀበት ቁልቁለቱ ፣ መውጣት መውረዱም የሚበዛበት ጊዜ ነው።
ኢትዮጵያ የወጣት ሀገር ነች። ብዙ ወጣቶች የሚኖሩባት ሀገር መሆኗ ይታወቃል። ሆኖም አብዛኛው ወጣት የመማር ዕድል ካለማግኘቱ ባሻገር ዕድሉን ያገኙትም የትምህርት ሥርዓትና አሰለጣጠኑ ሥራ መፈለግን ፣ ቤተሰብም ያንን የሚያበረታታ በመሆኑ ብዙዎች በጠበቁት አልገኝ ሲሉ ለከባድ የመንፈስ ስብራት ፣ ለደባል ሱስ ለበሽታ ይጋለጣሉ። ይህ ጉዳይ ያሳሰባቸው ጥቂት ወጣቶች የወጣቱ በማኅበራዊ መገናኛ ጎራ እየለየ መጨቃጨቅ በዝቶ ቢመለከቱ ‘የተከታዩን ትውልድ አቅም ማጠናከር‘ "Empower The Next Generation" የተባለ ሀገር በቀል

Logo ENG Ethiopia

መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በመመስረት ወጣቶች በውስጣቸው ያለውን አቅም አውጥተው ራእያቸውን መኖር እንዲችሉ የሚያግዙ ስልጠናዎችን የሚሰጥ፣ የሚያነቃቃና የሚያበረታታ ሁኔታና ዕድልን መፍጠር ችለዋል። መስራቾቹ እንደሚሉት እየተስተዋለ ያለው ከፍተኛ የወጣቶች ብክነት ይህንን ግብረ ሠናይ ድርጅት ለማቋቋም ምክንያት ሆኗቸዋል።
ከአንድ ዓመት በፊት የተቋቋመው ይሄው ተቋም የወጣትነትን እንዲያው በዋል ፈሰስነትን ለመቅረፍና የሀገር አለኝታ የሚሆን ወጣት የመኮትኮት ራእይ ይዟል። ለወጣት ተማሪዎች የተለያዩ አጋዥ ቁሳቁሶችንም በመለገስ በሰብእናቸው የተሻሉ ይሆኑ ዘንድ ጥረት ያደርጋል። በዲላ እና በጅማ እንዲህ ያሉ ስልጠናዎችን ሰጥቷል። ከስልጠናው የተሳተፉ ሁለት ወጣቶች በሕይወታቸው ውስጥ በነገሮች ላይ ራሳቸው ወሳኝ የመሆን ችሎታንና ልምምድን በማዳበር በውስጣቸው ይፈጠር የነበረን የመሸነፍና ያለመችል ስሜትም አሸንፈው ነገን አሻግሮ ማየት እንደሚቻል ጠንከር ያለ የስነ ልቦና ዝግጅት ልምምድ መጀመራቸውን ነግረውናል። ነገን ዛሬ መሥራት የጥቂቶችና የብልሆች ችሎታ መሆኑ አይካድም ። ወጣቶች ይህንን እውን ማድረግ እንዲችሉ ማገዝ ደግሞ የዚህ ሀገር በቀል ድርጅት ትልቅ ግብ ሆኖ ተቀምጧል። እንዲህ ግብረገብነት ላይ ራእይን ለመኖር ማገዝ የሚችሉ እንቅስቃሴዎች አሁን አሁን ፈተና ተጋርጦባቸዋል። ወጣቶች ማስመሰል፣ መፍራት ፣ ራሳቸውን መሸሽ ውስጥ ሲገቡ ይስተዋላል። ይህ ችግር ውጤቱ በሂደት የሚስተዋል ቢሆንም ከወዲሁ በሥርዓት ካልተመራ አደገኛ ይሆናል።

ሰሎሞን ሙጬ 

ኂሩት መለሰ