1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተቃዋሚ ፓርቲዎች አስተያያት በአዲሱ ካቢኔ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 12 2010

ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ በትናንትናዉ ዕለት ያዋቀሩት አዲስ ካቢኔ  የለዉጥ ሽታ የሌለዉና የህዝቡን ጥያቄ የሚመልስ አይደለም ሲሉ  አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች አስታወቁ።ተሿሚወቹ  ህዝብን በቅንነት ማገልገል የሚችሉና ከተመደቡበት ቦታ ጋር ተያያዥነት ያለዉ የሙያ ባለቤቶች ሊሆኑ ይገባ ነበርም ብለዋል።

https://p.dw.com/p/2wQFB
Äthiopien Amtseinführung neues Kabinett durch  Premierminister Abiy Ahmed
ምስል Reuters/T. Negeri

opposition Parties oppnion on New Cabinet . - MP3-Stereo



አንዳንዶቹ በበኩላቸዉ ሹመቱ የጠቅላይ ሚንስትሩን አንጻራዊ ነፃነት ያሳየ ነዉ ብለዉታል። ዶክተር ዓብይ አህመድ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ስልጣን ከአቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ  ከተረከቡ በኋላ በመጀመሪያ ቀን በምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር ተቃዋሚ ፓርቲወችን ጨምሮ ብዙዎች የለዉጥ ተስፋ እንደጣሉባቸዉ ሲገልፁ ቆይተዋል። የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ተስፋ ከጣሉ ፓርቲዎች መካከል አንዱ እንደነበር የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙሉጌታ አበበ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።  
በትናንትናዉ ዕለት ጠቅላይ ሚንስትሩ በምክር ቤቱ  ያፀደቁት  የ16 ነባርና አዳዲስ  የካቤኔ አባላት ሹመት ግን አቶ ሙሉጌታን አላስደሰታቸዉም። 
«ብዙ ለዉጥ የታየበት ወይም የለዉጥ ሽታ ያለዉ አይደለም።ያሉትን ነዉ ከአንዱ ወደ አንዱ የማድረግ ነገር ነዉ ፤የታየዉና ።አዲስ የሚባሉትም አዲስ አይደሉም።በምክትልነት የቆዩ በዚያዉ ዉስጥ ያለፉ ናቸዉ።እና ከዚህ ካቢኔ አወቃቀር ላይ ቢያንስ ፖለቲከኛ ያልሆኑ ሀገር ወዳድ የሆኑ የድርጅት አባል ያልሆኑ ለሀገራቸዉ ሊሰሩ የሚችሉና ሙያ ያላቸዉ፤ ባለሙያወችን ያካተተ አደረጃጀት ይኖራል የሚል ነበረ ግምታችን።»
እንደ አቶ ሙሉጌታ የሴቶች ተሳትፎ  በተወሰነ ደረጃ  ከነበረዉ ከፍ ማለቱ  አወንታዊ ነዉ።አጠቃላይ የካቤኔ አወቃቀሩ ግን ከፖለቲካ ወገንተኝነት ይልቅ ሀገር ወዳድ ባለሙያወች ቢካተቱ የተሻለ ለዉጥ ለማምጣት እንደሚረዳ አመልክተዋል።። 
«ለዚች ሀገር ለዉጥ ሊያመጣ የሚችለዉ፤ ስለ ኢንደስትሪ ሙያ ስለ እርሻ ሙያ ያላቸዉ፣ መስራት የሚችሉ፣ ከፖለቲካ ነፃ የሆኑ፣ ለዚች ሀገር የሚያስቡና ይቺ ሀገር የምትፈልጋቸዉና ይችን ሀገር የሚፈልጉ ሰዎች ቢሳተፉበት በዚህ አደረጃጀት መሬት ጠብ የሚል ለዉጥ ሊመጣ ይችል ነበር።» 
የኦሮሞ ፌደራሊስት  ኮንግረንስ ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ በበኩላቸዉ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር አቅምና ችሎታ ያላቸዉ ወጣት መሪ መሆናቸዉ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ከተመረጡበት የፖለቲካ ድርጅት አካሄድ አንጻር ግን የአሁኑ ካቤኔ ምስረታም ይሁን ሌሎች ተግባራት «የህዝብን ጥያቄ  ይመልሳል» የሚል እምነት እንደሌላቸዉ ይናገራሉ።
«ኢህአዴግ እንግዲህ ልማታዊ መንግስት ነዉ።ልማታዊ መንግስት ደግሞ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚከተል መንግስት ነዉ።እና ዶክተር አብይ ይህን ለማስፈፀም ነዉ የተመረጠ።ኢህአዴግ ነዉ ያስመረጣቸዉ።ስለዚህ ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ዉስጥ ወጣት የሆነ ለዚያ ብቁ የትምህርት ዝግጅትና ችሎታ ያለዉ ሰዉ ነዉ።ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ህዝብ ለሚጠይቃቸዉ  መሰረታዊ የሆኑ ጥያቄወች ለመመለስ ገና በጥያቄ ምልክት ዉስጥ ነዉ ያለዉ ። ከሰዎች ጋር ከባለስልጣናት ጋ ሳይሆን ችግሩ ከስርዓቱ ነዉ።»በማለት ነዉ የገለፁት።
አቶ ሙላቱ፤ በአሁኑ ወቅት  ጠቅላይ ሚንስትሩ ከካቢኔ ሽግሽግ  ይልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳና የቀሩትን ታሳሪዎች እንዲፈቱ ቢያደርጉ ለዉጡ «የሚታይ»  ይሆን ነበር ነዉ ያሉት። ሌላዉ ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ የአረና ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት አቶ አንዶም ገ/ስላሴ ናቸዉ።እሳቸዉ እንደሚሉት  አዲሱ  ጠቅላይ ሚንስትር  ተሿሚወችን ከመምረጥ አንፃር  ከቀደሙት ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ የተሻለ ነፃነት እንዳላቸዉ  አስተዉለዋል።ያም ሆኖ ግን  ሰዎችን ከመለዋወጥ ባለፈ የህብረተሰቡን ጥያቄ  መመለስ የአዲሱ ካቢኔ ስራ ሊሆን ይገባዋል ሲሉ ነዉ የገለፁት። 
«በተለያዩ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ የሚያሰሟቸዉ ንግግሮች ጥሩ ናቸዉ።የሚያነሳሱ ናቸዉ።ይህን ንግግር ወደተግባር መሬት ወርዶ ህብረተሰቡን ማገልገል ሲችልነዉ ለዉጥ መጣ የሚባለዉ።እንጅ የህወሃት ቦታ በኦህዴድ መያዙ በራሱ ለህዝብ ጥያቄ በቂ ምላሽ ሊሆን አይችልም።ግን በተወሰነ መልኩ የበኢአዴግ የነበረዉን ፉክክር ሊቀንሰዉ ይችላል።የህወሃት የበላይነት አለ ለሚባለዉ ጥያቄ መልስ ሊሆን ይችላል ዞሮ ዞሮ ግን የህብረተሰቡን ጥያቄዎች መመለስ ከጠቅላይ ሚንስትሩ አዲስ ካቤኔ ይጠበቃል።» 

Äthiopien Amtseinführung neues Kabinett durch  Premierminister Abiy Ahmed
ምስል Reuters/T. Negeri
Äthiopien Parlament Hailemariam Desalegn
ምስል DW/Y. G. Egziabher

ጠቅላይ ሚንስትሩ ስልጣን ከተረከቡ ካለፉት ጥቂት ሳምንታት ወዲህ በኢትዮጵያ ሶማሌ፣በአምቦ፣በመቀሌና በአዲስ አበባ ከተሞች ህብረተሰቡን ያነጋገሩ ሲሆን በዛሬዉ ዕለትም  ጎንደርን ጎብኝተዉ  ወደ ባህር ዳር ማምራታቸዉ ታዉቋል።

 

 

ፀሐይ ጫኔ

ነጋሽ መሀመድ