1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምርጫ የማይካሄድባቸው የምርጫ ክልሎችና ትችቱ

ዓርብ፣ ግንቦት 27 2013

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና፣የብልጽግና ፓርቲ የተሰራጨው የዐቢይ ድምጽ ከንግግሮቻቸው ተቆርጠው የተቀጠሉ እና ሀሰተኛ መረጃዎች ናቸው ሲሉ አስተባብለዋል። መሐመድ አሰፋ «የስብሰባውን ትክክለኛ ያልተቆራረጠ ቅጂ በሚዲያ ልቀቁና እንመናችሁ»ብለዋል። 

https://p.dw.com/p/3uRK8
Äthiopien l Premierminister Ahmed Abiy
ምስል Amanuel Sileshi/AFP

የተቀነባበረ የተባለው የድምጽ ቅጂና ማስተባበያው

« ከብልጽግና ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አስቸኳይ ስብሰባ ሾልኮ የወጣ ተብሎ ሰሞኑን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰራጨው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ንግግር»በዚህ ሳምንት በርካታ አስተያየቶችን ካስተናገዱት መካከል ግንባር ቀደሙ ነው።የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብሔራዊ ምርጫ በሚካሄድበት ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓም በ26 የምርጫ ክልሎች የፀጥታ ችግርን  ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ድምጽ እንደማይሰጥ ማስታወቁም አነጋጋሪ ነበር። እናስቃኛችኋለን። ከብልጽግና ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ሾልኮ የወጣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ንግግር» በሚል በዚህ ሳምንት መጀመሪያ  ኬሎ ሚድያ በተባለው ድረ ገጽ የተሰራጨው ድምጽ ብዙ አነጋግሯል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናገሩ ተብሎ ከቀረበው ድምጽ ውስጥ «እሞታታለሁ እንጂ ሥልጣን አልሰጥም»፤«ምርጫውን አጨናግፈን የሚፎካከሩ ኃይሎች ተስፋ እንዲቆርጡ ማድረግ» የሚሉት ይገኙበታል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና፣የብልጽግና ፓርቲ የተሰራጨው የዐቢይ ድምጽ ከንግግሮቻቸው ተቆርጠው የተቀጠሉ እና ሀሰተኛ መረጃዎች ናቸው ሲሉ አስተባብለዋል። የመንግሥት መገናኛ ብዙሀንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም በሌላ መድረክ ካደረጉት ንግግር ተወስዶ የተሰራ ሀሰተኛ የድምጽ ቅንበር ነው ሲሉ በማስረጃ አስደግፈው ባጠናቀሯቸው ዘገባዎች አሳይተዋል።ሰኞ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሀን የተሰራጨውን ይህን ድምጽ በሚመለከት በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።ከመካከላቸው ዘለፋ፣ፍረጃና ጽንፍ የያዙና ክብረ ነክ ሃሳቦችን ያካተቱትን በመተው በታረመ አንድበት የቀረቡትን ሃሳቦች እናስቃኛችኋለን ። ሚፍታ ሸምሱ ኡመር  «ሀሳብ የሌላቸው አካላት በተንኮል እና በሴራ መፎካከር ውስጥ በይፋ ገብተዋል ።ይህ ትልቅ ማሳያ ነው»ሲሉ በፌስቡክ አስተያየታቸውን አስፍረዋል።«አንድ ብሂል አለ ሥራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል እንደሚባለው ነው የናንተ ነገር ያሉት ደግሞ  ዮናስ ባህታ ናቸው በፌስቡክ ።አበበ ገብረእየሱስ እንዲህ ሲሉ ለመንግሥት መገናኛ ብዙሀን መልዕክት አስተላልፈዋል።«ውሸት መሆኑን በመረጃ አስደግፋችሁ  መናገራችሁ በጣም ጥሩ ነው ።ወደፊትም እንደዚህ አይነት ዜናዎች ሲወጡ በእንደዚህ አይነት መንገድ ውሸታሞችን ማጋለጥ ይገባል»። መሐመድ አሰፋ ደግሞ «የስብሰባውን ትክክለኛ ያልተቆራረጠ ቅጂ በሚዲያ ልቀቁና እንመናችሁ»ብለዋል። «ኧረ ባካችሁ ሃገርን አታተረማምሱ»ሲሉ ሃሳባቸውን በምሬት የጀመሩት ቅድስት በላይ« ቆይ ሌላ ስራ ጠፍቶ ነው ይሄንን ቁጭ ብላችሁ ስታቀነባብሩ የከረማችሁት ኧረ ምስኪኑ ህዝብ ሰርቶ ይብላበት ሰርቶ አዳሪው ዳቦ ፈላጊው ይኑርበት ይሄንን ህዝብ ተውት ይበቃል!!!!!!»በማለት መልዕክታቸው አጠቃለዋል።ገዛኽኝ ጠበቃ በሚል የፌስቡክ ስም የቀረበ አስተያየት የተጠያቂነትን ጉዳይ ያነሳል« የአብይ ደጋፊ ባልሆንም ይህ አሳሳች መንገድ ስለሆነ ኬሎ ሚዲያ ሊጠየቅ ይገባል።»በማለት ።ዚያድ አር አብዱልም ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል።«ይህን የውሸት ወሬ ብዙዎች የተረዱ ቢሆንም ሌሎች ያልተረዱ ማወቅ ያለባቸው፣ የተሰራጨው ወሬ ፍጹም ውሸት መሆኑን እና በተለያየ መድረክ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩትን በመቀጣጠል የተሰራ መሆኑን ነው። ይህ ድርጊት በህግ የሚያስጠይቅ ወንጀል በመሆኑ የሚመለከተው አካል የድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ የህግ እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል ብለን እንጠብቃለን።ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል።«ሥራ ለሰሪው እሾህ ላጣሪው»ያሉት ደረጀ ታዴ «ወሬ  ዳቦ አይሆንም በሥራ እንስተጋባው በማለት አሳስበዋል።የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ / ቤት ፣ባለፈው ሳምንት በብልጽግና ፓርቲ ስብሰባ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተባለ በማስመሰል የተለቀቀው የድምፅ ፋይል በውሸት የተቀነባበረና  ጠ/ሚኒስትሩ በተለያየ ግዜ የተናገሩትን በመቁረጥና በመቀጠል የተፈጠረ የሀሰት መረጃ መሆኑን ያረጋግጣል ሲል በፌስቡክ አስተባብሏል፡፡ጽህፈት ቤቱ በዚህ የሀሰት መረጃ ዘመን እና ምርጫው እየተቃረበ ባለበት ወቅት ዜጎች፣ አለመግባባትን በመፍጠር ላይ ባተኮሩ ፣በነዚህ አሳሳች የመረጃ ዘመቻ ዓይነቶች እንዳይታለል  ሲል አሳስቧል

Logo Prosperity Party Ethiopia

የብልጽግና ፓርቲም በፌስቡክ ባወጣው መግለጫ የሃሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ህዝቡን ለማደናገር የሚደረግ ሙከራ ተቀባይነት የሌለው ተራ ተግባር ነው ሲል አጣጥሏል።የፓርቲው የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ ባወጡት መግለጫ  የተሰራጨው መረጃ « ሙሉ በሙሉ ሃሰትና የፓርቲው ፕሬዝዳንት በተለያየ መድረክ ላይ ካደረጉት ንግግሮች ተቆራርጦ የተፈበረከ ነው ፤ማለታቸው በፌስቡክ ተገልጿል።አለማውም ህዝቡን ማደናገርና ህዝብና መንግስት መካከል ያለመተማመን  ብሎም ውጥረትና ያለመረጋጋት እንዲፈጠር ማድረግ ነው ያሉት ዶ/ር ቢቂላ ተግባሩንም ተቀባይነት የሌለው ሃላፊነት በማይሰማቸው አካላት የሚሰራጭ ብለውታል፡፡ሃላፊው መሰል የሃሰት መረጃዎችን ማሰራጨት፣ባለፉት ቅርብ አመታት እየተለመደ መጥተዋል  ሲሉ ገልጸው  ህዝቡ መሰረት ከሌላቸውና ምንጫቸው ካልታወቀ መረጃ እንዲጠበቅና መረጃዎችን በጥንቃቄ እንዲመርጥ አሳስበዋል፡፡

Äthiopien Birtukan Mideksa UDJ Partei
ምስል Yohannes Geberegziabher/DW

ምርጫ ቦርድ በስድስተኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ በ26 የምርጫ ክልሎች ምርጫ እንደማይካሄድ ማስታወቁ ሌላው ሰሞኑን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ያነጋገረ ጉዳይ ነበር ።ቦርዱ በዚህ ሳምንት ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ በቤንሻንጉል ጉሙዝ በኦሮምያ በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል በሚገኙ 26የምርጫ ክልሎች ምርጫ እንደማይካሄድ አስታውቋል።በነዚህ ቦታዎች ምርጫ የማይካሄደውም በፀጥታ ችግር ፣የመራጮች ምዝገባ ባለመጀመሩ፣የመራጮች ምዝገባ ተጀምሮ በመቋረጡና የመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ አቤቱታ በመቅረቡ ምክንያት እንደሆነ አስታውቋል። በሶማሌ ክልልም በ14 የምርጫ ክልሎች ድምጽ የመስጠት ሂደት ላይ አለ የተባለውን ችግር እያጣራ መሆኑንም ገልጿል።

አንድነን ይበጃል በሚል የፌስቡክ ስም  ከምርጫ በፊት ሀገራዊ እርቅ ይቅደም ሲባል ሀገሩ ሰላም ነው ምርጫ ማካሄድ ይቻላል አላቹሁ፣ አሁን ደሞ በተወሰነ ቦታ ችግር ስላለ በአንዳንድ ቦታዎች ድምፅ አይሰጥም። አስቲ በጥሞና አስረዱን።የሚል ጥያቄ ቀርቧል። «ይህ ሁሉ የምርጫ ክልል ካልመረጠ ምርጫዉ ምርጫ ነዉ እንበል ወይስ? ሲል የሚጠይቀው ዋናው ነገር ጤና በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረ ሃሳብ ነው። ናቲ ጎበዜም ይጠይቃሉ።«የእነዚህን ሁሉ ቦታዎች ሰላም ያልጠበቀ መንግስት እንዴት ይወዳደራል ሲሉ«ሁሉ ሰላም የሌለበት ሀገር ሆነ ሰለዚህ የት ሀገር ነው ምርጫ የሚካሄደው ለማንኛውም የዜጎች ሰለም ይቅደም፣ ገበሬ ይመለስ ወደርሻ  ያሉት ደግሞ መሱድ መሀመድ  ናቸው

ኡስማን ከዲር «ወይ ምኑን ተካዬደ ተዳያ ሲሉ ዘሌ አየለ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ምርጫ መቆም አለበት

ሲሉ የበኩላቸው ሃሳብ ሰጥተዋል።ታዲያ በዚህ ሁሉ ቦታ ላይ ምርጫ የማይካሄድ ከሆነ የኢትዮጵያ ምርጫ ነው የሚባለው ወይስ፣ በከፊል ኢትዮጵያ የሚካሄድ ምርጫ ? ያሉትደግሞ ኤልያስ እያሱ  ናቸው

እንዲህም በተቆራረጠ መንገድ ምርጫ አለ እንዴ በማለት የጠየቁት  ሀብቴ ተሾመ

ምርጫ የማይካቸሄድባቸው አካባቢዎች ሰላማቸው ከምርጫ ጋር ተያይዞ ነው ወይስ በእነዚህ አካባቢወች ሰላም የመስስከበር ተግባሩ መንግስት አይመለከተውም ይህ ደግሞ የኑረዲን መሀመድ አስተያየት ነው።

አብውቃው ደባልቀው  «እንደተባለ ከሆነ ፣አብዛኛው ቦታ ማለት ይቻላል ምርጫ የማይካሄድበት ነው።ታዲያ ምርጫውን አቁሞ ሰላሙ ላይ መስራት እና ሁሉም ቦታ ላይ ፍፁም ሰላም ማረግ አይሻልም ብለዋል። ምርጫ ቦርድ ምርጫው የማይካሄድባቸውን ቦታዎች የመለየት ስራ መስራቱ ጥሩ ነው ነወ።ለምሳሌ በጉራፋርዳ ወረዳ ካሉት ቀበሌዎች በከፊሉ በሰላም እጦት ምክንያትሰዎች ቀዬ አቸውን ለቀው ተሰደዋል። ልክ እንደ ምርጫ ቦርድ ሁሉ መንግስት ለተፈናቀሉት ዜጎችም  የመፍትሄ ውሳኔ ቢሰጥ የሚለው የማስረሻ አራጌ አስተያየት ነው

ኂሩት መለሰ