1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስአፍሪቃ

የተሻሻሉ የስኳር ድንች እና የለውዝ ዘሮች

ረቡዕ፣ ሰኔ 9 2013

የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በግብርናው ዘርፍ በሚያካሂዳቸው ምርምሮች ለግብርናው ዘርፍ የተለያዩ አስተዋጽኦዎችን ማድረጉ ይነገርለታል። ከሰሞኑም የዚሁ ምርምር ውጤት የሆኑ የስኳር ድንችና የለውዝ ዘሮችን ለአርሶ አደሩ አቅርቧል።

https://p.dw.com/p/3v3Pg
Äthiopien Harrar | Verbessertes Saatgut der Harama Universität
ምስል Mesay Teklu/DW

የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ውጤቶች

ባሳለፍነው ዓመት በተለይ በግብርናው ዘርፍ ብዙ ምርምሮችን ሲያካሂድ የቆየው የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ሁለት አዳዲስ የለውዝ እና አንድ የቦለቄ ዝርያን በማግኘት በሀገር አቀፍ ዝርያ አፅዳቂ ኮሚቴ ስለማፀደቁ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጀማል ዩሱፍ ተናግረዋል። ከዚህ ባለፈ ዩኒቨርሲቲው በቅርቡ በምርምር የተሻሻለ ያለውን የስኳር ድንች ዝርያን ለባቢሌ ወረዳ አካበቢ አርሶ አደሮች አከፋፍሏል። በኦሮሚያ ክልል ሁለት ሚሊየን ያክል ሕጻናት የመቀንጨር ችግር እንዳለባቸው ጥናቶች ማሳየታቸውን የሚናገሩት ተመራማሪዎቹ በንጥረ ነገር የበለፀገ ነው የተባለውን የስኳር ድንች በተለየ መልኩ እንዲመገቡ ለማስቻል ይሰራል ብለዋል።

Äthiopien Harrar | Verbessertes Saatgut der Harama Universität
ምስል Mesay Teklu/DW

በምርምር የተሻሻለው አዲሱ ዝርያም በምሥራቅ ሀረርጌ ዞን ባቢሌ ወረዳ ቢሻን ባቢሌ ገጠር ቀበሌ ለሚገኙ አርሶ አደሮች መሰራጨቱ ተሰምቷል። «እኛም ያደግነው በስኳር ድንች ነው” በሚል ለአካባቢው አዲስ አለመሆኑን የተናገሩት የባቢሌ ወረዳ አስተዳዳሪ ዝርያው የምግብ ዋስትና ችግር ላለበት የወረዳው ኅብረተሰብ ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል። በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የድንች እና ስራስር ተክሎች ተመራማሪ የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዋሱ መሀመድ በበኩላቸው በምርምር ተሻሽሎ የቀረበው የስኳር ድንች ከቀድሞ ስለሚለይበት እና ጠቀሜታው ለDW ገልፀዋል። 

በንጥረ ነገር የበለፀጉ ሰብሎችን በምርምር የማውጣት እና የማስፋፋት ፕሮጀክት አካል የሆነው ይህ ተግባር በአብዛኛው ህብረተሰብ እንዲተገበር እና እንዲስፋፋ ቀጣይ ሥራ ይሰራል ተብሏል። ዩኒቨርሲቲው ሌላኛው በዚህ ዓመት ለአርሶ አደሩ ያከፋፈለው በምርምር የተገኘ አዲስ የለውዝ ዝርያ ነው በለውዝ አምራችነት ለሚታወቀው የምስራቅ አካባቢ ህብረተሰብ መሰራጨቱን የተናገሩት አስተባባሪው ከቀደሙት ዝርያዎች በተለየ ፋይዳ  እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ በሌላ በኩል ግን በለውዝ እና ሌሎችም ሰብሎች ውስጥ ይገኛል ያሉት አፍላቶክሲን የተባለ መርዛማ ንጥረ ነገር በጤና እና በምርት ጥራት ላይ ችግር የሚፈጥር በመሆኑ የሚመለከታቸው ተቋማት በጋራ ሊሰሩበት ይገባል ብለዋል-ዶ/ር አብዲ፡፡

Äthiopien Harrar | Verbessertes Saatgut der Harama Universität
ምስል Mesay Teklu/DW

በግብርና ምርምር ዘርፍ የካበተ የረዥም ዓመታት ልምድ እንዳለው የሚነገርለት ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በየጊዜው ለህብረተሰቡ ጠቀሜታ አላቸው በሚል በምርምር የሚያወጣቸው ዝርያዎች ለአካባቢው ኅብረተሰብም ሆነ ለሌሎች አካባቢዎች ያስገኙት ጠቀሜታ ለየቅል ይሁን እንጂ በርካታ ስለመሆናቸው የሚስማሙቱ ምሁራን ብዙዎች ናቸው ፡፡ ውጤቱን በተጨባጭ ለመመልከት የተቃረቡ የባቢሌ ወረዳ እና ምስራቅ ሀረርጌ አርሶ አደሮች ተስፋ መጣላቸውን ተናግረዋል። ሙሉ ቅንብሩን ከድምጽ ዘገባው ያድምጡ

መሳይ ተክሉ

ሸዋዬ ለገሠ