1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስአፍሪቃ

የተሸላሚዎቹ ወጣቶች ሥራ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 28 2014

የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ግብርናን በማዘመን ዘርፍ ኢትዮጵያን ወክለው የተወዳደሩ እና ያሸነፉ የአራት ወጣቶችን ስራ ያስቃኘናል። ወጣቶቹ እንዴት ነው ግብርናውን ማዘመን የሚሹት? ኬንያ ላይ በተዘጋጀው ውድድር ላይስ ምን ይዘው ቀረቡ?

https://p.dw.com/p/4AuqN
Boaz Berhanu gewinnt Preis in Kenia
ምስል privat

የተሸላሚዎቹ ወጣቶች ሥራ

የ27 ዓመቱ ቦኤዝ ብርሃኑ ጅማ ዩንቨርስቲ ውስጥ የኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ መምህር ነው ። ከዚህም ሌላ ባለፉት አራት አመታት ግብርና ላይ መሠረት ያደረጉ ጀማሪ ድርጅቶችን ወይም Startup የሚባሉትን በማማከር እና አብሮ በመመስረት አሳልፏል።  ወጣቱ መምህር አብሮ ከመሠረተው ጀማሪ ድርጅት አንዱ Omishtu-joy ይባላል። የዚህንም ድርጅት ሀሳብ ይዞ ነው በቅርቡ ኬንያ ላይ በተካሄደው ውድድር ላይ የተካፈለው። « የኬንያው ፕሮግራም Sankalp Africa Summit ይባላል። አላማው አፍሪቃ ውስጥ ያሉ ግብርናን መሠረት ያደረጉ የፈጠራ ስራዎችን አወዳድረው ወደ ቢዝነስ መግባት እንዲችሉ ፈንድ መስጠት ነው።» ሲል ቦኤዝ ያብራራል።  በዚህም ውድድር ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት የአፍሪቃ ሀገራት የመጨረሻው ውድድር ላይ ደርሰው አሸንፈዋል።
በዚህ ውድድር ድርጅቱን ወክሎ መሳተፍ የሚችለው ግን አንድ ሰው ብቻ ስለነበር  ቦኤዝ ብቻውን ነው ወደ ኬንያ ተጉዞ ባለሙያዎች እና ዳኞች በተገኙበት የድርጅታቸውን አላማ ያስተዋወቀው። ድርጅቱን የመሠረቱት በጠቅላላ አራት ወጣቶች ናቸው። ቦኤዝ ከድርጅቱ ስያሜ አንስቶ ወጣቶቹ በምን መልኩ ግብርናን ለማዘመን ቆርጠው እንደተነሱ ገልጾልናል። «Omishtu ማለት በኦሮምኛ አምራች ማለት ነው።  joy ከእንግሊዘኛው የተወሰደ ነው፦ ደስታ። ስለዚህ «የአምራች ደስታ» የሚሰራ ድርጅት ነው። ይህም ድርጅት አፈር ላይ የተለያዩ ምርመራዎችን ያደርጋል።» ይላል ቦኤዝ።

ተጋቡ አብረሃም የ Omishtu-joyን ከመሠረቱት ሌላኛው ሲሆን በአሁኑ ሰዓት የድርጅቱ ስራ አስኪያጅም ነው። ኬንያ ላይ የተካሄደውን ውድድር «ማሸነፋችን እጥፍ ድል ነው» የሚለው ተጋቡ ድርጅቱን እሱ እና ጓደኞቹ የዩንቨርስቲ ተማሪ ሆነው ነው ሀሳቡን ያመነጩት።  ያኔ በአራት ሰዎች የተጀመረው ሀሳብ ዛሬ 10 ያህል አባላት ወይም ሰራተኞች  አሉት።

የተማሪዎቹ አማካሪ የነበረው እና ተባባሪ መስራች ቦኤዝ እንደሚለው በርካታ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች የመመረቂያ ፕሮጀክታቸውን ከተመረቁ በኋላ ሲያስቀጥሉ አይታይም። አሁን ላይ ግን እነሱን እያዩ ሌሎች ተማሪዎችም ሀሳባቸውን መተግበር ጀምረዋል።የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ የሆነው ተጋቡ 25 ዓመቱ ነው። በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ የምርምር ተቋማት በግብርናው ዘርፍ ላይ ልምድ ካካበቱ ምሁራን እና ሌሎችም ጋር አብረው እየሰሩ እንደሆነ ገልፆልናል።  
ወጣቶቹ የሰሯት የግብርና ማዘመኛ መሣሪያ ፤ ለመረመረችው አፈር የትኛው ሰብል ተስማሚ እንደሆነ ብቻ ሳይሆን መጠቆም የምትችለው ቦኤዝ እንደሚለው ሌላም ችግር ትፈታለች።« ገበሬው ለምሳሌ ቡና ትከል ብላው እሱ ግን ሙዝ ከሆነ ማምረት የሚፈልገው መሣሪያዋ ሙዝን ለማምረት የትኛውን ማዳበሪያ መጠቀም እንዳለበት ትነግረዋለች። » 
የአፈር መመርመሪያ መሣሪያውን እስካሁን አርሲ እና ደብረ ብርሃን አካባቢ ሞክረን ጥሩ ውጤት መዝግበናል የሚለው ቦኤዝ ከልምድ ይልቅ በሳይንሳዊ ጥናት ላይ ተመርኩዞ መዝራት ገበሬውን ትርፋማ እንደሚያደርግ ይናገራል። አርሲ አካባቢ ዝንጅብል መትከል ጥሩ እንደሆነ እና ደብረ ብርሃን አካባቢ ፖም መትከል ጥሩ እንደሆነ በጥናት ሊደርሱበት ችለዋል። 

ተጋቡ አብረሃም የ Omishtu-joy ድርጅት ስራ አስኪያጅም
ምስል privat

ወጣቶች ኬንያ ድረስ ሄደው በተወዳደሩበት ሃሳብ የ 25 ሺ ዶላር ተሸላሚ ሆነው። ከገንዘብም በላይ « እዛ ያገኘነው ኔትዎርክ» ከምንም በላይ ነው ይላል። ቦኤዝ። የወጣቶቹ የወደፊት አላማ ትልቅ ነው። ተጋቡ እንደሚለው በዚህ በጎርጎሮሲያኑ ዓመት በፈንድሬዚንግ 300 ሺ ዶላል የማሰባሰብ እቅድ አላቸው። ያገኙት የ 25 ሺ ዶላል ሽልማት የዚህ አንዱ አካል ነው። 

ተጋቡ ሌሎች ወጣቶች ከእነሱ ብዙ መማር እንደሚችሉ እና ካላቸው ነገር ተነስተው ወደ ስራ እንዲገቡ ይመክራል።« ይህንን ስራ ስንጀምር 2000 ብር አንሶን ከሰው ተበድረናል። ይህ ግን ዛሬ በሚሊዮን የሚቆጠር ፈንድራይዝ ከማድረግ አልከለከለንም። » ሲል ሌሎች ወጣቶችን ያበረታታል። 


ልደት አበበ

ነጋሽ መሐመድ