1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

 የተረሱት ስደተኞች

ሐሙስ፣ ሐምሌ 16 2012

መጠለያ ጣቢያዉ ከሰፈሩት ስደተኞች የኮንቴይነር ቤት ያገኙት 3000 ብቻ ናቸዉ።የተቀሩት 12 ሺዉ እንደነገሩ በተዉሸለሸለ የእንጨት ጎጆ፣ አለያም ድንኳን ዉስጥ ነዉ የሚኖሩት።ሁሉም ያዉ መቼም እንደሰዉ አዉሮጳ ዉስጥ የተረጋጋ ኑሮ መኖር ይመኛሉ።

https://p.dw.com/p/3fpai
Griechenland | EU | Flüchtlingscamp Moria auf Lesbos
ምስል Getty Images/AFP/A. Messinis

የተዘነጉት ስደተኞች በሞሪያ

ሌስቦስ በተባለችዉ የግሪክ ደሴት ላይ በሚገኘዉ ሞሪያ መጠለያ ጣቢያ አሁንም 15000 ስደተኞች እንደሰፈሩ ነዉ።አንዳዶቹ ሶስት ዓመት ያክል መጠለያ ጣቢያዉ ዉስጥ  አስቆጥረዋል።እስካሁን ግን የሚያስታዉሳቸዉ አላገኙም። እነሱም ከሌላዉ ዓለም ተነጥለዉ፣ተረስተዉ ብቻቸዉን እንደቀሩ ነዉ የሚያስቡት።በዚያ ላይ የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭትን ለመከላከል በሚል ወደ ሌላ ሥፍራ እንዳይንቀሳቀሱ በመከልከላቸዉ ከመጠለያ ጣቢያቸዉ የሚወጡበት ሲታመሙ ነዉ። ከተቀረዉ ዓለም ጋር የሚገናኙት ደግሞ በተንቀሳቃሽ ስልክ ብቻ ነዉ።ጋዜጠኞችም አካባቢዉን እንዲጎበኙ አይፈቀድላቸዉም።ግሪክ የሚገኘዉ የዶቸ ቬለ ወኪል ቶማስ ቦርማንም ስደተኞቹን በስልክ እያነጋገረ ከመዘገብ ዉጪ ሌላ አማራጭ የለዉም።የቦርማንን ዘገባ ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል። 

ጥርት ካለዉ የበጋ ሰማይ የሚፈልቀዉ  የፀኃይ ጨረር፣ በተንጣለለዉ ባሕር ዉኃ ላይ ይነሰነሳል።የፀይዋን ጨረር የሚዉጠዉ ዉኃ በፋንታዉ በነፋስ እየተገፋ ጉች ካለችዉ ደሴት ጥጋጥጋት ይላተማል።ኦሚድ አሊዛድ በሰፊዉ ትልቅ ባሕር ላይ ነቁጣ ከምታክለዉ መጠለያ ጣቢያዉ አሻግሮ የተፈጥሮን ትርዒት ሲመለከት ስደተኝነቱን ረስቶ እንደ ፈላስፋ ይቃጣዋል።እንዳዴ ደግሞ እንደ ሐገር ጎብኚ የባሕሩን ጠርዝ ተክትሎ ወዲያ ወዲሕ ማለት ያምረዋል።
ሁለቱንም አይደለም።ወደ ባሕሩ መጠጋትም  አይችልም።ስደተኛ ነዉ።የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭትን ለመከላከል በሚል እንደ ሁሉም ስደተኛ ከመጠለያ ጣቢያዉ እንዳይወጣ ከተከለከለ አራት ወሩ።
«የክልከላዉ ጊዜ ይራዘም ይሆናል።አይራዘምም ይሆናል።እዚሕ ላለነዉ ሰዎች ግን በጣም አስቸጋሪ ነዉ።ከመጠለያ ጣቢያዉ መዉጣት አለመቻል በጣም ያስፈራል።ሁሉንም ሰዉ ያስጨንቃል።»
ብዙዎቹ ከተቀረዉ ዓለም ተነጥለዉ፣ የታገቱ ያክል ነዉ የሚሰማቸዉ።
«አንዳዶቹ ሁለት እና ሶስት ዓመት ሆኗቸዋል።ሞሪያ ተረስታለች።እዚሕ ያሉት ሰዎችም ተረስተዋል።»
ሌሎቹ ዓለም እንዲያስታዉሳቸዉ በኢንተርኔት የርዳት ጥሪ እያደረጉ ነዉ። እንደ እሳቸዉ «ሐሎ፣ የአፍቃኒስታን ዜጎች ነን።እዚሕ ድንኳን ዉስጥ ሶስት ሴቶች እና የሰባት ዓመት ሴት ልጄ እንኖራለን።መጠለያ ጣቢያ ዉስጥ በየምሽቱ ሰዎች ይጣላሉ።አንዳዴ ጠበኞች በጩቤ ይወጋጋሉ።ሰላም አይሰማንም።ሞሪያ የምድር ላይ ሲዖል ነዉ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዲረዳን እንጠይቃለን።እርዱን።»
እርግጥ ነዉ ከዚሕ ቀደም ደሴቲቱ ላይ ሰፍረዉ ከነበሩት ስደተኞች 5000ዉ ወደ ሌላ መጠለያ ጣቢያ ተዛዉረዋል።የተቀሩት 15ሺዉ ግን እንደ ሴትዮዋ ሁሉ ዛሬም ርዳታ ይማፀናሉ። ሰሚ ማግኘታቸዉ ያጠራጥራል።በተለይ አዉሮጳ «ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎናል» ባይ ናቸዉ።
መጠለያ ጣቢያዉ ከሰፈሩት ስደተኞች የኮንቴይነር ቤት ያገኙት 3000 ብቻ ናቸዉ።የተቀሩት 12 ሺዉ እንደነገሩ በተዉሸለሸለ የእንጨት ጎጆ፣ አለያም ድንኳን ዉስጥ ነዉ የሚኖሩት።ሁሉም ያዉ መቼም እንደሰዉ አዉሮጳ ዉስጥ የተረጋጋ ኑሮ መኖር ይመኛሉ።
እስካሁን ከዚያ መጠለያ ጣቢያ ወጥተዉ ጀርመን፣ ፊንላንድ ወይም ፖርቱጋል የገቡት ግን ወላጅ ወይም አሳዳጊ የሌላቸዉ ለአካለ መጠን ያልደረሱ 120 ልጆች ብቻ ናቸዉ።ሌሎች አዋቂ ያላጀባቸዉ በመቶ የሚቆጠሩ ልጆች ግን አሁንም እዚያዉ ናቸዉ።ልጆቹ ብቻቸዉን ይሁኑ ከወላጆቻቸዉ ጋር ትምሕርት አያዉቅም።መሠረታዊ እንክብካቤም ቅንጦት ነዉ።በተለይ በዚሕ በበጋዉ ሙቀት ትናንሽ ጎጆ ወይም ድንኳን ዉስጥ ተፋፍገዉ መኖር ግዳቸዉ።
«ሙቀቱ በጣም ከባድ ነዉ።ሌት ተቀን ከልጅ ጋር ድንኳን ዉስጥ መቀመጥ በጣም ይሰለቻል።ከዉጪዉ ይልቅ ድንኳን በጣም ይሞቃል።»
ይላል ኦሚድ አሊዛድ።አፍቃናዊ ነዉ።ባለቤቱን እና ትንሽ ወንድ ልጁን አስከትሎ ከዚያ ከተገለለ ደሴት የደረሰዉ ባለፈዉ ሕዳር ነበር።ለተገን ጥያቄዉ ቃለ መጠየቅ ሊደረግለት የተቀጠረዉ ለመጪዉ ዓመት ነሐሴ ነዉ።ከ13 ወር በኋላ።
                               
«ቀጠሮዬ ነሐሴ 2021 ነዉ።መጠበቅ አለበኝ።ምን ምርጫ አለኝ።»
ምንም።

Bonn Demo #Wir haben Platz
ምስል DW Greek
Griechenland | EU | Flüchtlingscamp Moria auf Lesbos
ምስል Getty Images/AFP/A. Messinis

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ