1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተማሪዎች መመረዝ

ረቡዕ፣ ኅዳር 17 2012

በአዲስ አበባ ከተማ ልደታ ክፍለ-ከተማ «ፍሬ ሕይወት የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት» ውስጥ ዛሬ ተማሪዎች ተመርዘው ወደ ሐኪም ቤቶች መወሰዳቸው ተገለጠ። ከምግብ ጋር የተያያዘ ሳይኾን አልቀረም በተባለ መመረዝ ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች ወደ ሁለት ሐኪም ቤቶች ተወስደው ሕክምና ተደርጎላቸዋል።

https://p.dw.com/p/3Tpq0
Stadtansicht von Addis Abeba Hauptstadt von Aethiopien
ምስል Imago/photothek

ተዝለፍልፈው የወደቁ ተማሪዎችም ነበሩ

ዛሬ ረፋድ በአዲስ አበባ ልደታ ክ.ከ ፍሬ ሕይወት የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት የተከሰተ የተባለ የምግብ መመረዝ በተማሪዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ከተለያዩ አካላት ጠይቀን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ችግሩ እንዴት እንደተከሰተ እና መነሻው ምን እንደሆነ ለማወቅ ህጻናት ተማሪዎቹ ለህክምና ወደተወሰዱባቸው የጥቁር አንበሳ እና የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታሎች በመሄድ ለማጣራት ብንሞክርም ትክክለኛ መረጃ ማግኘት አልቻልንም።

ቀትር 7 ሰዓት ገደማ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተገኝቸ እንደተመለከትኩት ቁጥራቸው በውል ባይታወቅም በርከት ያሉ ወላጆች ፊታቸው ላይ የመረበሽ ስሜት እየታየባቸው ወዲህና ወዲያ ሲሉ ነበር። ጥቂት ቆይቶም የትምህርት ቤት የደንብ ልብሳቸውን የለበሱ ህጻናት ተማሪዎች በተለያዩ 3 ኮስትር የተባሉ እና እስከ 28 ሰዉ የመጫን አቅም ባላቸው ተሽከርካሪዎች እየተሳፉረ ወደ መጡበት ትምህርት ቤት ሲሄዱ ተመልክቻለሁ።

አንድ የሆስፒታሉ የስራ ሃላፊ ስለ ሁኔታው መረጃ እንዲሰጡኝ ጠይቄያቸው ፈቃደኛም ሆነው ወደ ጽ. ቤታቸው ከገባን በኋላ ከአአ ጤና ቢሮ መረጃ በቢሮው በኩል ቢሰጥ ይሻላል የሚል የስልክ መልእክት ስለደረሳቸው ትክክለኛውን ሁኔታ ከሆስፒታሉ ለማግኘት አልተቻለም። የሆነ ሆኖ ግን ጥቂት ተማሪዎች የተመገቡት ምግብ እንደነበር እና ምርመራም እየተደረገ እንደሚገኝ ፣ ከዚሁ መነሻም የሚጠረጥሩት ነገር እንዳለ ፣ ለምርመራ ናሙና ከተወሰደው ምግብ ፍተሻ ፍንጭ እንደሚገኝ ፣ ምግቡን ተመግበው ለህመም ከተዳረጉት ባሻገር ሳይመገቡ የታመሙ ተማሪዎችም መኖራቸውን መደበኛ ባልሆነ የአጭር ደቂቃ ንግግራችን ተነግሮኛል።

ፖሊሶችም በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ ወዲህና ወዲያ ሲሉ ነበር። የተለያዩ ነጭ ጋዋን የለበሱ የሆስፒታሉ ሰራተኞችም የተለያዩ ሰነዶችን ይዘው ሲንቀሳቀሱ ነበር። በሆስፒታሉ በነበረኝ ቆይታ ለህጻናት ተማሪዎች እና ወላጆች ደህንነት ሲባል ፎቶግራፍም ሆነ ተንቀሳቃሽ ምስል እንዳስቀር አልተፈቀደልኝም።

ከሆስፒታሉ እንደወጣሁ በቀጥታ ወደ ሌላኛው ተማሪዎቹ ለህክምና ወደተወሰዱበት ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ደርሼ ከአንድ የጥበቃ ሰራተኛ ጠይቄ እንደተረዳሁት ከረፋዱ 4 ሰዓት እስከ 7 ሰዓት ገደማ ቁጥራቸው በርከት ያለ ተማሪዎችና ወላጆች በአንቡላንስ ተሽከርካሪ ይገቡ እንደነበር ፣ በኋላ የፌዴራል ፖሊሶች ገብተው ውስጥ ባሉት ላይ ጥበቃ ከውጭ በሚገቡት ላይ ክልከላ ያደርጉ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። ይሄው ሰራተኛ ያዩትን ሲናገሩ እንዳንድ ተማሪዎች የማንቀጥቀጥ ሁኔታ ይታይባቸው ነበር። ሆኖም ሆስፒታሉ በደረስንበት ወቅት ተማሪዎቹ ደህንነታቸው ተረጋግጦ በተለያዩ ተሽከርካሪዎች ወደ ትምህርት ቤታቸው
ተመልሰው መወሰዳቸውንና እንደሌሉ ተናግረዋል።

ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የተጣራ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። የአአ ከተማ ከንቲባ ጽ.ቤት አንድ
ባልደረባ ደግሞ ተማሪዎቹን ከሆስፒታል ወደ ትምህርት ቤት አድርሰው ስለመመለሳቸው ተናግረዋል። ፍሬ ህይወት የተባለው የቅድመ መደበኛን ጨምሮ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ የሚያስተምረው ትምህርት ቤት በግቢው ውስጥ ለተማሪዎቹ የምገባ አገልግሎት እንደሚሰጥም ታውቋል።

ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ተስፋለም ወልደየስ