1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያውያን በፈረንሳይዋ ማርሴይ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 18 2011

ከፓሪስ ቀጥላ በስፋት ሁለተኛ ትልቅ ከተማ በሆነችው ማርሴይ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ። ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም በየጊዜው ባህላቸውን ለማስተዋወቅ ጥረት ያደርጋሉ። በጋራም የሚረዳዱበት "ባላገሩ" የተሰኘ ማህበር መስርተዋል።

https://p.dw.com/p/3Mjzg
Frankreich | Marseille | Alter Hafen
ምስል DW/H. Tiruneh

ኢትዮጵያውያን በፈረንሳይዋ ማርሴይ

ሰማያዊ ቀለም የተላበሰው እና ከስሯ ተንጣሎ ከሚገኘው የሚዲትራንያን ባህር ትይዩ፣ አፍሪካን አሻግራ የምትመለከተው የደቡብ ፈረንሳይዋ የንግድ እና የቱሪዝም መናኸሪያ ማርሴይ ከተማ ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬም ድረስ የአፍሪካ እና የአውሮፓ በር መሆኗን ቀጥላለች። ማርሴይ ቅይጥ ከሆኑት ነዋሪዋቿ የባህል ብዙኃንነትን በአንድነት አቻችላ ከማስተናገዷም በላይ የታሪክ፣ የጥንታዊ ስነ ህንጻዎች እና ቤተ መዘክሮች መገኛ ናት። የባህር ዳርቻዋ እና የአየር ንብረቷም ከተቀረው የፈረንሳይ ከተሞች የተለየ ያደርጓታል። 

ከተማይቱ እንደ ጎርጎሮሳዊው በ2013 ዓ.ም. የአውሮፓ የባህል ከተማ ተብላ በአውሮፓ ህብረት ተመርጣ ነበር። የዛሬ ሁለት ዓመት ደግሞ የአውሮፓ የስፖርት ከተማ የሚል ስያሜን አግኝታለች። ኢትዮጵያውያን የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ሁለት የማርሴይ ክዋክብትን ጠንቅቀው ያውቋቸዋል። አንደኛው የቀድሞ የማንችስተር ዩናይትድ ተጨዋች ኤሪክ ካንቶና ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የቀድሞው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አምበል እና የአሁኑ የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ ዚነዲን ዚዳን ናቸው። 

Frankreich | Marseille | Alter Hafen
ምስል DW/H. Tiruneh

በኢትዮጵያ ሐረር ቤት ቀልሶ ይኖር የነበረው ዕውቁ ገጣሚ አርተር ራምቦ ህይወቱ ያለፈው በማርሴይ ከተማ ነው። የሐረር ጠቅላይ ገዢ የነበሩት ራስ መኮንንም በአንድ ወቅት ወደ ማርሴይ ጎራ ማለታቸውን ታሪክ ያወሳል። ልዑሉ ወደ ከተማይቱ በመጡበት ወቅት ያደረጉት ተግባር እስካሁንም ድረስ ስማቸው ከማርሴይ ጋር ተያይዞ እንዲነሳ አድርጎታል። በከተማዋ በሚገኝ ጉብታ ስፍራ ላይ የተገነባው እና በጎርጎሮሳዊው 1864 ዓ. ም. ግንባታው የተጠናቀቀው "እመቤታችን" ወይም "ኖተርዳም ደላጋር" ተብሎ ለሚታወቀው ትልቅ ካቴድራል በስጦታ ያበረከቱት መስቀል ነው ስማቸውን ከፍ ያደረገው።  

እውቁ ደራሲ ስብሃት ገብረእግዚያብሔር በበኩሉ ማርሴይን እና ጎረቤት ከተማ የሆነችውን ኤክስ ፕሮቫንስን ለኢትዮጵያውያን በምናብ አስተዋውቋል። ስብሃት "ትኩሳት" የተሰኘው መጽሀፉን መቼት ያደረገው በሁለቱ ከተሞች ነው። በዚህም በዚያም ከኢትዮጵያ ጋር ቁርኝት ባላት ማርሴይ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ። ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም በየጊዜው ባህላቸውን ለማስተዋወቅ ጥረት ያደርጋሉ። በጋራም የሚረዳዱበት "ባላገሩ"የተሰኘ ማህበር መስርተዋል። አፍሪካን እና አውሮፓን በድልድይነት ታገናኛለች ወደምትባለው ማርሴይ የኢትዮጵያ አየር መንገድም በቅርቡ በረራ ጀምሯል።  

መሉ ዝግጅቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ሃይማኖት ጥሩነህ 

ተስፋለም ወልደየስ