1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቦረና ድርቅ፤ ተፈናቃዮችና አማርኛ ለአፍሪቃ ኅብረት

ዓርብ፣ የካቲት 17 2015

የቦረና ድርቅ ብርቱ ሥጋት ደቅኗል። ከኦሮሚያ ክልል የአማራ ተፈናቃዮች በገፍ ወደ ብርዳማዋ ደብረ ብርሃን እየገቡ ነው። ከተማዪቱ ከአቅሜ በላይ ነው በሚል ተፈናቃዮችን መቀበል ማቆሟም ተገልጧል። አንዳንድ እስረኞች ተፈትተዋል። አማርኛ ቋንቋ በአፍሪቃ ኅብረት ጥቅም ላይ እንዲውል ኒጄሪያዊት የፊልም ባለሞያ እና ጋዜጠኛ ጥረት እያደረገች ነው።

https://p.dw.com/p/4NuIO
Äthiopien | Oromia | Getreidelieferung
ምስል Office of the PM of Ethiopia

የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ቅኝት፦ በድምፅ

የቦረና ድርቅ ነዋሪዎችን በረሐብ እየቀጠፈ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የቀንድ ከብቶችን በመግደል ብርቱ ሥጋት ደቅኗል። ከኦሮሚያ ክልል የአማራ ተፈናቃዮች በገፍ ወደ ብርዳማዋ ደብረ ብርሃን እየገቡ ነው። ከተማዪቱ ከአቅሜ በላይ ነው በሚል ተፈናቃዮችን መቀበል ማቆሟም ተገልጧል። አማርኛ ቋንቋ በአፍሪቃ ኅብረት ጥቅም ላይ እንዲውል ኒጄሪያዊት የፊልም ባለሞያ እና ጋዜጠኛ ጥረት እያደረገች ነው። በእነዚህ ዐራት ጉዳዮች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰጡ አስተያየቶችን አሰባስበናል።  

በደቡባዊ ኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ብርቱ እና ተከታታይ የድርቅ አደጋ ከባድ ሥጋት ደቅኗል። አንዳንድ ቦታዎች ላይ ከረሐቡ ጋር በተያያዘ የሰው ልጆች ሕይወት እየተቀጠፈ መሆኑም ተዘግቧል። በተለይ ቦረና ዞን ውስጥ በድርቁ የተነሳ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከብቶች ማለቃቸው ተነግሯል። የቀሩትም ሥጋ እና አጥንታቸው ቆዳቸው ላይ ተጣብቆ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች በስፋት ተሰራጭተዋል። 

«አባት አላችሁ? እናትስ?» ሲሉ የሚጠይቁት ኪያ ገብረወልድ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ናቸው። «አባቶች እናቶች ህፃናቶች በረሃብ ወድቀው ሲታዩ ስሜቱን አስበሃል? ለአንድ ደቂቃ ውሃ ጠምቶህ ፋታ አሳጥቶህ ያውቃል? እርቦህ ለደቂቃ መታገስ አቅቶህ ያውቃል?» በማለት የድርቅ አደጋ ለተጋረጠባቸው የቦረና ነዋሪዎች ትኩረት ይሰጥ ብለዋል። 

 Draught in South Nation Nationalities & Peoples Region
በድርቅ የተጠቁ የደቡብ ክልል አካባቢዎችምስል SNNPR

መሰንበት አሰፋ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ በበኩላቸው፦ «ትኩረት ለቦረና» ሲሉ ጽሑፋቸውን ይጀምራሉ። «ዕሚታየው ነገር እጅግ በጣም ልብ ይሰብራል! እንደ ሃገር የሚከሰቱ ችግሮችን በጋራ ካልመከትን አንድነታችን ዋጋ የለውም! የሕዝብን ችግር በጋራ መመከት የሁሉም ኃላፊነት ነው። አንድ ብሄራዊ የገንዘብ ማሰባሰቢያ አካውንት ቢኖር ጥሩ ነው» ብለዋል። እሪ በከንቱ በሚል ስም የትዊተር ተጠቃሚ፦ «ኦነግን የሚያስታጥቁና የሚያበሉት ግን ምነው ለቦረና አልደርስ አሉ» ሲሉ ጠይቀዋል። ድርቁ በደቡብ እና በሶማሌ ክልልም የከፋ መሆኑ ተገልጧል።በተጠቀሱት አካባቢዎች ከመልካም አስተዳደር እጦት፤ ሙስና እና የፖለቲካ ቀውስ ባሻገር ለአምስት እና ለስድስት የዝናብ ወራት የዝናቡ መጥፋት ችግሩን እንዳባባሰውም ይነገራል።

ማሚላ መሶፍ ሙና የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ «ደቡብ ክልል ውስጥ ኮንሶ ማኅበረሰቡም በረሀብ እየተጎዱ ነው! ማኅበረሰቡ ሰሚ አጣ እንደ?» ሲሉ ጽፈዋል። «ወንድምች አህቶች እየሞቱ ነዉ። ከብቶች እየሞቱ ነዉ ርዳታ በደቡብ ክልል ዛላ ወረዳ መላ ወረዳ ሕዝብ አቤቱታ» ሲሉ የጻፉት ደግሞ ይርዳው አየለ አስፋው ናቸው፤ ፌስቡክ ላይ።

ናይስዊዝ ካን በሚል የፌስ ቡክ ተጠቃሚ፦ «ቦረና እየተራበ፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በኢትዮጵያ ተፈናቀለው እያሉ...ስንት ሕዘብ ከወለጋ ተፈናቅሎ ባለበት ሀገር ሚሊየን ረሃብተኛና ተፈናቃይ ያላት ሌሎችን የምትረዳ ብቸኛ ሀገር የኛው ጉድ» በማለት ጽፈዋል። ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ስንዴ ወደ ውጭ ሃገር መላክ (ኤክስፖርት ማድረግ) ጀመርኩ ከማለቱ ጋር የሚያያዝ ነው። «ስንዴ ተርፎን ኤክስፖርት እያደረግን ነው እየተባለ ባለበት ስአት ውኃ ጠይቀህ ወተት የሚያጠጣህ የቦረና ሕዝብ ግን በድርቅ ምክንያት እንደ ቅጠል እየረገፈ ይገኛል» ሲሉ ኤዶም ኢትዮ በፌስቡክ ጽፈዋል።  

«በጣም ያሳዝናል። ቦረና ፈጣሪ በምሕረቱ ይድረስላችሁ፤ ግን እኮ ስንዴ ኤክስፖርት ይደረጋል።»  የሀብታሙ አሠፋ መልእክት ነው። ይማም ሞሐመድ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ባቀረቡት በቀጣዩ ባለሁለት መስመር ስንኝ ወደ ሌሎች ርእሰ ጉዳዮች እንሻገር። የይማም የፌስቡክ አጭር እና እምቅ ስንኝ ከስሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ውጭ ሊልክ መጋዘን ውስጥ ያከማቸው ስንዴ ኩንታሎች ተከምረው ይታያሉ።

Südostäthiopien | Dürre in Borena
ቦረና በድርቅ ምክንያት የሞቱ የቀንድ ከብቶች መሬት ላይ አጽማቸው ይታያልምስል Seyoum Getu/DW

ከዚህ ምስል በታች ሥጋና አጥንታቸው ከቆዳቸው ጋር የተጣበቁ የቀንድ ከብቶች ተረፍርፈው፤ አንድ እጅግ ከሰውነት ጎዳና የወጡ አዛውንት ምርኩዝ እና ጫማቸው አጠገብ ቀና በማለት እና በመውደቅ መሀል በክርናቸው የደረቀ መሬቱን ተደግፈው ይታያሉ። ስንኙ እንዲህ ይላል፦ 

«ኬንያ ገባሽ አሉ አንች ያገሬ ስንዴ
ከተራብነው በላይ ተርበዋል እንዴ?»

ከኦሮሚያ ክልል ከታጣቂዎች ግድያ እና ዝርፊያ የተረፉ በርካታ ተፈናቃዮች ወደ አማራ ክልልበተለይም ወደ ብርዳማዋ የደብረ ብርሃን ከተማ እየጎረፉ ነው። የከተማዪቱ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ሥጋቱ ከፍተኛ መሆኑን ዐሳውቋል። በጽሕፈት ቤቱ የስነ ሕዝብ ባለሞያ እና የተፈናቃዮች አስተባባሪ ኮሚቴ አባል አቶ አንተነህ ገብረእግዚአብሔር «የምግብ አቅርቦት እጥረቱ የከፋ በመሆኑ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋም ስጋት» አላቸው ሲል የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ጽ/ቤት በፌስቡክ ገጹ ጽፏል። «የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር በተፈናቃዮች ብዛት ምክንያት አዲስ ተመዝጋቢዎችን እንደማይቀበል አስታወቀ» ሲል ደግሞ ኢትዮጵያን ኢንሳይደር ረቡዕ በድረ ገጽ አትቷል። 

ወንድወሰን የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ፦ « [ደብረ ብርሃን]ውስጥ ባሉ መጠለያ ጣቢያዎች የተጠለሉት ሰዎቸ ቁጥር 28 ሺህ ደርሷል» ሲል የመገናኛ አውታሮችን መረጃ አጣቅሰው ጽፈዋል። «በየቀኑ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተፈናቃይ ወደ ከተማዋ እየገባ» መሆኑን የጠቆመው የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር «በቂ መጠለያና ምግብ ባለመኖሩ ምክንያት ተፈናቃዮችን ለመቀበል እየተቸገርን በመሆኑ በክልሉ መንግስትም እንደሀገርም መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል» ሲል አሳስቧል።

Äthiopien I Binnenflüchtlinge in Gojjam
ተፈናቃዮች በአማራ ክልል፦ ምስል ከክምችትምስል Alemnew Mekonnen/DW

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የባለፈው ችግር ጋር በተገናኘ ከታሰሩ በርካታ ምእመናን መካከል ታዋቂው ሰባኪ ምሕረተአብ አሰፋን ጨምሮ አንዳንዶች ከእስር መፈታታቸው የማኅበራዊ መገናኛ አውታር መነጋገሪያ ሆኗል።  የተወሰኑት ለመፈታታቸው ደስታቸውን የገለጡ በርካቶች ናቸው። ግዮናዊት ናኒ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ፦ «በእነ መምህር ምህረተአብ አሰፋ እና በነ ፌቨን ክስ ስር የተካተቱት እህት ወንድሞቻችን እና ጋዜጠኛ ዮሴፍ ተፈተዋል። በአዋሽ ዐርባ ከተጋዙት የተወሠኑ ቢፈቱም ብዙዎች ገና አልወጡም። ተመስገን ነዉ» በማለት ጽፈዋል። 

ያሬድ ዘሪሁን በፌስቡክ ገጻቸው፦ «እንቁ የኦርቶዶክስ ልጃችን ነው እግዚአብሔር ይመስገን ማወቅ ያለብን ጥፋተኛ ሆኖ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ጎን መቆሙን ስለጠሉ ብቻ ነው» ብለዋል። «ታዋቂ ያልሆነ በርካታ የሰ/ት/ቤት ወጣቶች ታስረው ያለ ጠያቂ ወደ አዋሽ የተጋዙና በሰቆቃ ላይ ያሉ አሉና እነሱ ላይ እንበርታ» በማለት የጻፉት ደግሞ ወንድወሰን ሠይፉ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ናቸው።  

«ወደ አዋሽ አርባ ታፍሰዉ የተወሰዱ ወገኖቻችን ጉዳይ አስጨንቆኛል። የምታውቁ ካለችሁ ስለ እግዚአብሔር ንገሩኝ» ያሉት ደግሞ ቴዎድሮስ ጌታሁን ናቸው በፌስቡክ ጽሑፋቸው። «የኔም የቤተሰብ ሰዉ ከተወሰዱት ውስጥ ነዉ። ሄደን መጠየቅን እንኳን ተነፍገናል። ምን አለ ስለሚያለቅሱ እናቶች ብሎ እግዚአብሔር በቸርነቱ መልካሙን ሁሉ ባሰማን» ሲሉም አክለው ጽፈዋል። በርካታ አስተያየት ሰጪዎች ስለተፈቱት ለፈጣሪ ምሥጋና በማቅረብ ሌሎችም በፍጥነት እንዲፈቱ ጠይቀዋል። 

ኒዤሪያዊቷ የፊልም ባለሞያ እና ጋዜጠኛ ራህመቱ ኪዬታ የአማርኛ ቋንቋ ከአፍሪቃ ኅብረት ቋንቋዎች አንዱ እንዲሁን የጀመረችውን ዘመቻ ከሰሞኑ አጠናክራ ቀጥላለች። የዛሬ አምስት ዓመት ግድም ቤልጂየም ውስጥ በአንድ የፊልም ፌስቲቫል ላይ ራሕመቱን አግኝተናት በዚሁ ጉዳይ ላይ በዶይቸ ቬለ ሠፋ ያለ ዘገባ አቅርበን ነበር። በአፍሪቃ የመሪዎች ጉባኤ ወቅት አዲስ አበባ ተገኝታ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠችው ራህመቱ፦ «አማርኛ ቋንቋን የኢትጵያውያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪቃውያን ብሎም የዓለም ቋንቋ ማድረግ እንደሚገባ» መግለጧን የተለያዩ የሀገር ውስጥ መገናኛ አውታሮች ዘግበዋል። ብዙዎች የራሕመቱ ሐሳብ እውን እንዲሆን ምኞታቸውን በመግለጥ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ዐስታውቀዋል። የነገድ እና የጎሣ ፖለቲካ አቀንቃኝ የሆኑ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ተቃውሞዋቸውን ገልጠዋል። ተቃውሞዎቹ ወደ ስድብ እና ማጥላላት ያዘነበሉ ስለሆነ ትተናቸዋል። ኤክሶዶስ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ፦ «ይሄ በጎ ዜና ለሁሉም ይድረስ» ሲሉ ጽፈዋል። ጌታቸው የተባሉ ሌላ አስተያየት ሰጪ ደግሞ፦ «ድንቅ፤ እንዴት ያለ እጹብ ድንቅ አሳብ ነው» ሲሉ በእንግሊዝኛ ጽፈዋል። ቀጠል አድርገውም «እናመሰግናለን። በዚሁ ቀጥዪበት። አሳቡን መደገፋችንን እንቀጥላለን» ብለዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Niederlande Amsterdam - Rahmatou Keita "The wedding Ring" in World Cinema Amsterdam 2017
ኒዤሪያዊቷ የፊልም ባለሞያ በስተቀኝ በኩል ሻሽ ያሰረችው አምስተርዳም፤ ሆላንድምስል DW/M. Sileshi

ኂሩት መለሰ