1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብሪታንያ ምክር ቤት የብሪግዚት እቅድን ዉድቅ አደረገ

ረቡዕ፣ ጥር 8 2011

የብሪታንያ ፓርላማ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ ሃገሪቱ ከአዉሮጳ ኅብረት እንድትወጣ የሚስችላትን የዉል ረቂቅ «የብሬግዚት ዕቅድን» በመቃወም ድምፅ ሰጠ። ትናንት ምሽት ምክር ቤቱ በሰጠዉ ድምፅ በ432 ተቃዉሞ እና 202 ድጋፍ በመስጠት የጠ/ሚሯን የብሪግዚት እቅድ ጥሎታል። ሜይ በስልጣን ለመቆየት የመተማመኛ ድምጽ ይሰጥባቸዋልም ተብሎአል።

https://p.dw.com/p/3Bbko
England: Symbolbild Brexit
ምስል Reuters/S. Dawson

የዉሳኔዉ ዉዝግብ ሃገሪቱን እንካይፈፋል አሳስቦአል

ብሪታንያ ሀገሪቱ ከአውሮጳ ሕብረት አባልነትዋ ለመውጣት ሕዝበ ውሳኔ ካካሄደች ወዲህ ከኅብረቱ የምትለያይበት መንገድ ጥቅሞቿን በማይጎዳ መልኩ እንዲሆን የሚለው ሲያነጋግር መክረሙ ይታወቃል።  ድምፅ አሰጣጡ ምናልባትም አይሆንም ይዞ ይመጣል እየተባለ ሲነገርም ነበር። ላለፉት ሁለት ዓመታት ከአውሮጳ ኅብረት ጋር በአንድ ወገን በሌላ በኩል ደግሞ ከሀገራቸው ምክር ቤት ጋር ሲነጋገሩ የከረሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ሜይ፣ ያቀረቡት የብሬግዚት ዕቅድ ዕጣ ፈንታ በምክር ቤቱ አባላት ድምፅ አሰጣጥ ይወሰናል ተብሎ በጉጉት ሲጠበቅ ነበር። ከድምፅ አሰጣጡ ቀደም ሲል የወጡ ዘገባዎች የጠቅላይ ሚኒስትሯ ዕቅድ የፓርላማ አባላቱን ድጋፍ ማግኘቱ አጠራጣሪ ነዉ ሲባል ነበር። ሜይ በበኩላቸው የምክር ቤቱ አባላት ታሪካዊ ስህተት እንዳይፈፅሙ እያሳሰቡ ነበር። የሕግ መምሪያ ምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ጆን በርካው የምክር ቤት አባላቱ ድምፃቸውን ከመስጠታቸው አስቀድሞ ሊሻሻሉ ይገባቸዋል የተባሉ አራት ጉዳዮች ላይ እንዲነጋገሩ እንደሚያደርጉ ለሮይተርስ ገልጸዉም ነበር።  ባለፈው በተሰጠው ሕዝበ ውሳኔ መሠረት ብሪታንያ ከአውሮጳ ሕብረት ልትወጣ 10 ሳምንታት ብቻ ይቀራት ነበር። 

Anti-Brexit banners are seen during a demonstration outside the Houses of Parliament in London
ምስል REUTERS

ብሪታንያ ከአዉሮጳ ኅብረት የምትወጣበት የብሪግዚት ዉልን ለማፅደቅ የተያዘዉ ቀጠሮ ሊራዝም መሆኑ ፍንጮች በሳምንቱ መጀመርያ ላይ ጠቁመዉ ነበር።  የብሪታንያዉ «ዘ ጋርድያን» የተሰኘዉ ጋዜጣ በኢንተርኔት ገፁ፤ ብራስልስ በሚገኘዉ የኅብረቱ ጽ/ቤት አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣንን ጠቅሶ እንዳስነበበዉ፤ መጋቢት 20 ቀን ብሪታንያ ከኅብረቱ ትለያያለች ተብሎ የተያዘዉ ቀጠሮ ምናልባትም በሌላ ቀነ ቀጠሮ መቀየሩ አይቀሬ ነዉ። ለቀኑ መቀየር የተሰጠዉ ምክንያት ደግሞ በብሪታንያዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሪዛ ሜይ የቀረበዉ ብሪታንያ ከኅብረቱ የምትወጣበት ዉል ዝርዝር በብሪታንያ ከፍተኛ ተቃዉሞ ስለገጠመዉ ነዉ። በመሆኑም ብሪታንያ ከኅብረቱ የምትወጣበት የመጀመርያዉ ቀነ-ቀጠሮ ምናልባትም ወደ ሐምሌ ሳይዛወር አይቀርም ተብሎም ነበር። የብሪታንያዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሪዛ ሜይ የብሪታንያ የተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ድምጽ ይሰጥበታል ወይም እየሰጠበት ያለዉ የብሪግዚት ዉል አብላጫ ድምጽን ቢያገኝ የብሪታንያ ጉዞ እንዴት ይሆናል?  ባያገኝስ? በለንደን እና ብረስልስ ከሚገኙት ወኪሎቻችን ጋር ዉሳኔ ሊሰጠዉ አንድ ሰዓት ሲቀረዉ አንደምታዉን ጠይቀን ነበር። 

England Brexit Demonstrationen in London
ምስል Reuters/J. Sibley

 

ገበያዉ ንጉሴ

ሃና ደምሴ

አዜብ ታደሰ